የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋትና ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን መከተል ለምርትና ምርታማነት ድርሻ እንዳለው በመገንዘብ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ገልጿል።
አርሶ አደር አሰፋ ወጣሜ እና ታሪኩ ልጁ በወረዳው የወጊዳና ቆቄ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ በማሳቸው ቡና፣ እንሰት፣ ቦሎቄ፣ ድንች የመሳሰሉትን በማምረት ከራሳቸው አልፎ ለገበያ በማቅርብ ተጠቃሚ በመሆን ኑሮን ለማረጋጋት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለሙያ ባደረገው ድጋፍና ክትትል ከተለመደው አስተራረስ ዘዴ በመላቀቅ ዘመናዊውን ዘዴ በመከተላቸው የምርቱን መጠን ከፍ እንዲያደርጉ እንዳስቻላቸው ጠቁመው፤ ሁሉም ይህንን ፈለግ በመከተል ቢያርሱ በአጭር ጊዜ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለዋል።
በወረዳው ግብርና ጽ/ቤት የምግብ ዋስትና ቡድን መሪ አቶ ካሳሁን ታደሰ፤ በወረዳው 15 ቀበሌያት ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም መታቀፋቸውን ገልፀው ከእነዚህ ቀበሌያት መካከል በሐሩ፣ ሐራንጃና ቱትቲ ያሉ ጥሩ ተሞክሮዎችን በማስፋት አርሶ አደሮች ከተረጅነት ተላቀው በምግብ ዋስትና ራሳቸውን እንዲችሉ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በወረዳው ከዚህ ቀደም በተሠራ ሥራ በርካታ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከሴፍቲኔት ፕሮግራም ወጥተው ራሳቸውን ወደመቻል መድረሳቸውን የገለጹት አቶ ካሳሁን፤ በቀጣይም የኢኮኖሚ አቅም ያሳደጉ አርሶና አርብቶ አደሮችን ለማስመረቅ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ጅክሶ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋትና ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን መከተል ለምርትና ምርታማነት ድርሻ እንዳለው በመገንዘብ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
አርሶ አደሩ በየጊዜው በሚያገኘው ግንዛቤ በመስመር የመዝራት ልምድ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ከዚህ ቀደም የነበረው አነስተኛ የምርት መጠን አሁን ላይ ከፍ እያለ በመምጣቱ የምግብ ዋስትና እያረጋገጡ ያሉ አርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ ነው ብለዋል።
ለምርታማነት የሚረዱ ማዳበሪያ፣ ዩሪያና ዳፕ አቅርቦት ጎን ለጎን አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ኮምፖስት አዘጋጅተው እንዲጠቀሙ የማድረግ ተግባር በባለሙያዎች እየተሠራ መሆኑን አቶ ክፍሌ አስረድተዋል።
አርሶ አደሮች የመንግስትንና የሌሎች አካላትን እርዳታ ከመጠበቅ ወጥተው እንዲሠሩና ለሌሎች እንዲተርፉ ኃላፊው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የእንሰት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከ69 ሺህ 1 መቶ በላይ ሄክታር ማሳ በእንሰት መሸፈን መቻሉን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የዳዉሮ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ
ግራሃም ፖተር የሲዊዲን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሾሙ
የፌደሬሽን ምክር ቤት እና ተጠሪ ተቋማት በካፋ ዞን ሺሺንዳ ከተማ አስተዳደር ለአቅመ-ደካሞች ያስገነቧቸውን መኖሪያ ቤቶች እያስረከቡ ነው