በመሐሪ አድነው
ዛሬ ላይ ከስኬት የደረሱ ሰዎች ሕይወታቸው የኋሊት ሲመረመር ስኬታቸው በዋዛ እንዳልተገኘ እንገነዘባለን፡፡ የትኛውም ስኬታማ ሰው የሕይወትን ዳገትና ቁልቁለት በትዕግስት አልፎ ነው ደረስኩበት ከሚለው ከፍታ ላይ የሚደርሰው፡፡
ሕይወት ነገ ብሩህ ትሆን ዘንድ የግድ ዛሬ ላይ የሚገጥምን ከባባድ ፈተናዎች በጽናት ማለፍን ትጠይቃለች፡፡ አለበለዚያ በሚገጥሙ ተግዳሮቶች ተሸንፈው እጅ ለሚሰጡ ሰዎች መራራ መልኳን እንካችሁ ማለቷ አይቀርም። ለችግሮች እጅ የሚሰጡ ሰዎች ደግሞ ስኬትን ሳይሆን የሽንፈትን ጽዋ ተጎንጭተው ዕድሜያቸውን ሁሉ ከሰው በታች ሆነው ለመኖር ይገደዳሉ፡፡
በዛሬ የችያለሁ አምዳችን ድንገት በሕይወቷ የገጠማትን ፈተና በጽናት አልፋ ለስኬት የበቃች እንስት ናት፡፡
ቅድስት ጥዑም ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በምስራቁ የሀገራችን ክፍል፥ በሐረር ከተማ ነው፡፡ ገና የሦስት አመት ህፃን ሳለች ነበር ለአይነ ስውርነት የተዳረገችው፡፡ እንዳስፈለጋት ተንቀሳቅሳ ቦርቃ በማደጊያ ዕድሜዋ የደረሰባት የዓይን ጉዳት ለቤተሰቦቿ ጭንቅ ነበር፡፡
እሷም ቢሆን በፍንድቅድቅና ባማረው የለጋነት አካሏ ይህን እክል ማስተናገዷ ለዕድገቷ አደጋ ነበር፡፡ ይህን የተገነዘቡት ቤተሰቦቿ አርፈው መቀመጥ አልቻሉም፡፡ መፍትሄ ብለው ያሰቡት በቂ ህክምና እንድታገኝ ነበር፡፡
መፍትሄ ያመጣል ብለው ያሰቡትን በርካታ የህክምና መንገዶችን ሞከሩ፡፡ ጠብ የሚል ውጤት ግን ጠፋ፡፡ ደጋግመው ሞከሩ የተለወጠ ነገር ሊገኝ አልቻለም፡፡ ከሁሉም የከፋው ይህን ከባዱን ፈተና ይጋፈጡ የነበረው እናቷ መሆናቸው ነው፡፡
ቅድስት የሁለት ወር ጨቅላ ህፃን እያለች ነበር ወላጅ አባቷን በሞት ያጣችው፡፡ ሆኖም ግን መንፈሰ ጠንካራ እናት ስለነበሯት እርሷንም አበርትተዋታል፡፡
የዓይኗ ጉዳይ መፍትሄ እንደሌለው የተገነዘቡት እናቷ ልጃቸው እንደ ማንኛውም ዓይናማ ልጅ ትምህርቷን ተምራ ለቁምነገር መብቃት እንደምትችል ራሳቸውን አሳመኑ። የወደፊት ሕይወቷ እንዲደላደል ፈጣሪዋን እየተማጸኑ አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርጉላትም ጀመር፡፡
ይህን ጊዜ ቅድስት የልጅነት ጊዜ በዓይኗ መጎዳት ፈተና ቢገጥመውም በፈጣሪ እገዛና በእናቷ ብርታት መቃናት ጀመረ፡፡
ቅድስትም ብትሆን ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ከፍተኛ የትምህርት ፍላጐት አደረባት። ለማንበብ ያላት ፍላጐትም እንደዚያው ከፍ ያለ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በደረሰባት የአይነ ስውርነት ጉዳት ማንበብ ባትችልም፡፡
የልጃቸውን ጽኑ የቀለም ፍላጐት የተገነዘቡት እናት ጊዜ ሳያጠፉ ትምህርት ቤት አስገቧት፡፡ በቤት ውስጥ የሚያነቡላትንም ሰው ቀጠሩላት፡፡ በዚህ አላበቃም፡፡ የልጃቸው የትምህርት ፍላጐት እንዳይጨነግፍ ሙሉ መፅሐፍትን በካሴት ቀርፀው እያዳመጠች እንድትማር አደረጓት፡፡
የቅድስት የትውልድ ከተማ የሐረር ህዝብ ልበ ቀና፣ አዛኝና ተባባሪ በመሆኑ ከእናቷ ጋር አንድ ላይ እንደ ቤተሠብ እንዳሳደጓት ትናገራለች፡፡ ይህ ለእሷም ሆነ ለሚጨነቁላት እናቷ የተለየ አጋጣሚ ነበር፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ግን ወደ ሻሸመኔ መጥታ ለመማር ተገደደች፡፡ በሻሸመኔ አይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ተምራ አጠናቀቀች፡፡
ከዚያም ወደ ትውልድ ከተማዋ ሐረር ተመለሰች፡፡ ወደ ሐረር ከተመለሰች በኋላም ከመለስተኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ በዚያው ተከታተለች፡፡
ወደ ሐረር በተመለሰች ጊዜ ትልቁ ማነቆ የሆነባት የአይነስውራን የብሬል መፅሐፍት እጥረት ነበር፡፡ በዚያም ነው እናቷ ካሴት እየገዙ ጓደኞቿ ደግሞ ትላልቅ ይዘት ያላቸውን የሁለተኛ ደረጃ መፅሐፍትንም እያነበቡ በካሴት ቀርፀው የሚሰጧት፡፡
ነገር ግን በዘመኑ የነበረው የቴፕ ካሴት ክር ይነክስ ነበር፡፡ ሌላ ካሴት ተገዝቶ በጓደኞቿ ተነቦ ማስቀረፅ በራሱ ትልቅ ፈተና እንደነበርም ታስታውሳለች፡፡
በዚህ አይነት ሁኔታ እስከ 11ኛ ክፍል የተማረች ሲሆን በመሃል የብሬል መፅሐፍ ታትሞ በመምጣቱ የተሰማት ደስታ ወደር አልነበረውም፡፡
የአይነ ስውራን ማህበር አሳትሞ የላከው የብሬል መፅሐፍ ወደ እጇ ሲገባ ሌሊቱን ሙሉ ስታነብ ማደሯን ነው የነገረችን፡፡ ምክንያቱም ዳብሶ የማንበብ እድል ማግኘቷ ጉዳይ ብርቅ ሆኖባት ስለነበረ ነው፡፡
“ሐረር ስማር ጓደኞቼ ሁሉ አይናማዎች ነበሩ፤ እንደዚያም ሆኖ አካል ጉዳተኛ መሆኔን ሳላውቅ ነበር ያደኩት፡፡ ልዩነት እንዳለኝ የተገነዘብኩት ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ነው” ትላለች፡፡
የብሬል መፅሐፍ አግኝታ ብትደሰትም ተግዳሮቱ በሌላ መልኩ ቀጠለና ክፍል ውስጥ ከአይናማዎች ጋር የምትማር እንደመሆኑ በብሬል ስትፅፍ ቀጭ ቀጭ የሚል ድምፅ ያሰማል፡፡ እንደረባሽ ተማሪ ተቆጥራ ከክፍል እንድትወጣ የተደረገችበት ጊዜ እንደነበር ታስታውሳለች፤ ይህ የሚሆነው ከግንዛቤ ችግር እንደሆነም በማመልከት፡፡
ቅድስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በሐረር አጠናቅቃ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባትን ውጤት በማምጣት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባች። የመጀመሪያ ድግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህርት ክፍል በጥሩ ውጤት አጠናቅቃም ተመረቀች፡፡
የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ በውጤት በኩል ስኬታማ የሚባል ቢሆንም እንደ አይነስውርነቷ የገጠሟት ተግዳሮቶች አልጠፉም፡፡ ተግዳሮቶቹን በመቋቋም ታልመው የነበረውን ውጤታማነት የመጀመሪያ ድግሪ በማግኘት አሳክታዋለች፡፡
በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር በአቃቤ ህግ ባለሙያነት እየሠራች ትገኛለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች የህግ ባለሙያዎች ማህበር አባልም ነች፡፡
ማህበሩ የሚሰጣቸው አገልግሎቶችን ስትገልጽ ለአካል ጉዳተኛ ወገኖችና ቤተሠቦታቸው የህግ ምክር አገልግሎትና አቅም ለሌላቸው ደግሞ በፍርድ ቤት ጠበቃ መድቦ እንዲከራከሩላቸው ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለማህበሩ አባላት ግንዛቤ ይፈጥራል፡፡
ማንኛውም አካል ጉዳተኛ ለሚደርስበት በደል ድጋፍ በማድረግ ማህበሩ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዛሬ ላይ ቅድስት በስራዋ ደስተኛ ነች። በልጅነቷ የገጠማት የዓይን እክል ጎትቶ ከዓላማዋ አላደናቀፋትም፡፡ ይልቅስ በእናቷ አይዞሽ ባይነት እና በፈጣሪዋ እገዛ የሚገጥሟትን መሰናክሎች ሁሉ በጽናት አልፋ ለሌሎች አርዓያ የሚሆን የሕይወት ጉዞ ላይ ተገኝታለች፡፡
ሕይወት በፈተና የታጀበች ብትሆንም ፍሬዋ እንዲያምር ተስፋና ጽናት ትሻለች፡፡ ተስፋና ጽናቱ የሚመጣው ደግሞ ከግለሰቦች ያልተቋረጠ ጥረት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የጠበቃ ቅድስት ጥዑም ታሪክ ሕያው ምስክር ነው፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው