በደረጀ ጥላሁን
በኢትዮጵያ መንግስትና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ እና የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚተገበረው ሥራ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ይሰኛል፡፡
በኘሮግራሙ በከተማና በገጠር የቤተሰብ የምግብ ክፍተትን በመሙላትና ኑሯቸው እንዲቀየር የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡
በፕሮግራሙ በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ። ከነዚህም መካከል የተራቆቱ መሬቶችን እንዲያገግሙና መልሰው ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ፤ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንሰሳት ማድለብ፣ በወተት ላም እርባታና በሌሎችም የስራ መስኮች በመሰማራት ከድህነት እንዲወጡ የማድረግ ሥራ ይሰራል፡፡ ከዚህ አኳያ በሲዳማ ክልል በከተሞች ሴፍቲኔት ኘሮግራም የተከናወኑ ተግባራትን እናስቃኛለን፡፡
የሲዳማ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔትና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ዶንቃ የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሪት እንዲያፈሩና ህይወታቸው እንዲቀየር የማድረግ ዓላማን ያነገበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም በሲዳማ ክልል በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ሀዋሳና ይርጋለም ከተሞች ላይ በመተግበር ከ22 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንደሚሉት የከተሞች ሴፍቲኔት ሥራዎች በአራት ተከፍለው የሚከወኑ ናቸው፡፡ በአካባቢ ህብረተሰብ ተሳትፎ የሚሰሩት አንደኛው ሲሆን በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በችግኝ ዝግጅትና እንክብካቤ እንዲሁም አነስተኛ የመሰረተ ልማት ሥራ ላይ የሚሳተፉ ናቸው። በዚህ ፕሮግራም 14 ሺህ 490 ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ያሉት ቀጥታ ተረጂዎች ናቸው፡፡ በተለይ አቅመ ደካማ የሆኑ፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያን የህብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ይካተታሉ፡፡ እነዚህም በፕሮጀክት አተገባበር መመሪያ መሠረት የተመለመሉ ሲሆን 6 ሺህ 510 የቀጥታ ተረጂዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በሶስተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሆኑት ደግሞ ወጣቶች ሲሆኑ 1ሺህ 782 ወጣቶች በሁለት ዙር ለስድስት ወር በቴክኒክና ሞያ ተቋማት ሥልጠና ተሰጥቷቸው ከድርጅት፣ ካምፓኒዎች እና ፋብሪካዎች ጋር በመገናኘት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ከነዚህም 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ከ10ኛ ክፍል በታች የሆኑ፣ ጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ፣ ከ1ኛ ደረጃ ጀምሮ ትምህርት ያቋረጡ ወጣቶች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
በአራተኛ ደረጃ በከተማ ያሉ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ሲሆን ወሳኝና ቁልፍ ትኩረት ነው፡፡ ከሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመቀናጀት የሚሰራ ነው፡፡ ከሥራና ክህሎት ጋር በመቀናጀትም ይሰራል፡፡ ለዚህም የስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተገመገመና አቅጣጫ በመስጠት እየተሰራበት ነው፡፡
በከተሞች 599 ዜጎችን ከጎዳና በማንሳት ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ መደረጉን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው የእርባታ ላሞች፣ በግና ፍየል፣ የቡና መፍጫ ማሽን፣ እንዲሁም አቅማቸው በሚችለው ሥራ እንዲሰማሩ ግንዛቤ በማስጨበጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው፡፡
የአካባቢ ሥራ የሚሰሩ ዜጎች የሚመረቁ ሲሆን በመመሪያው መሠረት ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠዋል፡፡ በሥራ የሚቆዩት ለሶስት ዓመት ብቻ ነው፡፡ በነዚህ ጊዜያት ከሚያገኙት 20 በመቶውን እንዲቆጥቡ በማድረግ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች ላይ ያሉ ሰፋፊ ለእርሻ የሚሆኑ መሬቶችን በመጠቀም የከተማ ግብርና /የዶሮ እርባታ፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት/ እንዲሁም በችግኝ ማፍላትና ሌሎችም ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ገቢ ያገኛሉ፡፡ በሚያገኙት ገንዘብ አነስተኛ ሱቅ በመክፈት ጥሪት እንዲያስቀምጡ ይደረጋል፡፡ ይህን ገንዘብ ተመርቅው ሲወጡ ያጠራቀሙትን 20 በመቶ ይዘው ከአለም ባንክ የሚሰጣቸውን 600 ዶላር ከ30 ሺህ ብር በላይ /ግራንት ፈንድ/ ይዘው እንደሚወጡ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ልጆቻቸው እንዳይጎዱ የጤና መድህን ዋስትና እንዲታቀፉ ማድረግ እና ወደ ኋላ እንዳይመለሱ አስፈላጊ ሥልጠና ይሠጣል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ባንክ ሰነድ የተቀመጠ አቅጣጫ አለ፡፡ ከቲቪቲ ኮሌጆች ጋር በጋራ በመስራት በሰለጠኑት ሞያ መሠረት እንዲሰማሩ ይደረጋል፡፡ ወደ ሥራ እድል ፈጠራ መምሪያዎች በማስተላለፍ ሼድ ይሰጣቸዋል። መሥሪያና መሸጫ ቦታ በመስጠት ራሳቸውን መምራት ይጀምራሉ፡፡
በዚህ ዓመት 10 ሺህ 935 ተመርቀው ይወጣሉ፡፡ ለነዚህም ከአለም ባንክ የመጣው 137 ሚሊዮን 199 ሺህ 518 ብር የተሰጠ ሲሆን ብሩን ወስደው በርካቶች የራሳቸውን ሥራ ጀምረዋል፡፡ ይህንኑ ሥራ የአለም ባንክ ተወካዮች መጥተው እውቅና የሰጡ ሲሆን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር ሥራውን በማየት እንደተሞክሮ የታየ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በሁለት ከተሞች ብቻ የተጀመረውን ኘሮግራም ለማስፋት ከፌደራል ጋር እየተነጋገርን ነው ያሉት አቶ ታሪኩ ሰባቱ የሪፎርም ከተሞች በሴፍትኔት መታቀፍ አለባቸው የሚል ሀሳብ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተጠቃሚውን ቁጥር እና በጀት የሚጨምረው የዓለም ባንክ ነው፡፡ በበጀቱ መነሻ በሀገራችን ያሉ በሴፍቲኔት የታቀፉ ከተሞች በሚሰጠው ኮታ መሰረት የሚወሰን ሲሆን ከዚህ አኳያ የኛ ኃላፊነት መመልመል እና ተጨማሪ የሚረዱ ሰዎችን በተመለከተ መረጃ ማቅረብ ነው ብለዋል።
ዜጎችን ከተረጂነት መንፈስ ለማላቀቅ እንዲቻል በየከተሞች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን አቅም ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በየከተሞቹ መስሪያና መሸጫ ሼዶች ተዘጋጅተው ሥራ ተፈጥሮ፤ በተለይ አቅመ ደካማ ለሆኑት ከሴፍቲኔት ሌላ መንግስታዊ ያልሆኑና ረጂ ድርጅች ተሳትፈው እንዲቋቋሙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንደሚሉት ሀዋሳ ከተማ ላይ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ 40 ሺህ የሚሆኑ ተመርቀው የወጡ መኖራቸውን ጠቁመው ወደ ኋላ እንዳይመለሱ እና ለሌላው የሥራ እድል እንዲፈጥሩ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በከተማው በተለይ የእንጨት ሥራ ላይ በርካቶች የተሳተፉ ሲሆን እነሱም ሌላ ሰው ቀጥረው እየሰሩ ነው። በከተማ ግብርና ወተት፣ ከብት እርባታ ላይ የተሳተፉ ብዙ ሲሆኑ ሌላውን እንዲያስተምሩና የራሳቸውን ኢኮኖሚ እንዲያሳድጉ እየተሰራ ነው፡፡
ተመርቀው የወጡትን በባለሞያዎች አማካይነት የክትትልና ድጋፍ ሥራ በመስራት አሁን ያሉበትን ደረጃ የማየት፣ ካፒታላቸው ምን ያህል እንደደረሰ፤ እንዲሁም ማትረፍ መክሰራቸው እየታየ የድጋፍ ሥራ እንደሚሰራም አቶ ታሪኩ ገልጸዋል፡፡
በቢሮው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ የኑሮ ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ በቀለ ዳዊት በበኩላቸው የሴፍቲኔት ፕሮግራም በከተሞች የሚስተዋለውን ሥራ አጥነት እና ድህነት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
በከተሞች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመለየት ምልመላ ሲካሄድ የከፋ ድህነት ውስጥ ያሉትን በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት ከህብረተሰቡ ውስጥ በተመረጡ ሰዎች አማካይነት ምልመላ ይደረጋል። በዚህ መሠረት ከሀይማኖት ተቋማት፣ አረጋዊያን እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች በፍትሀዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑት እንደሚለዩ ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡
አቶ በቀለ እንደሚሉት የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ዜጎች የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፈው የራሳቸውን ገቢ እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ አስችሏቸዋል። በተያያዘም ለተጠቃሚዎች የሚከፈለው ክፍያ ከምንም ንኪኪ ነፃ መሆኑንና በየወሩ የሚከፈለው ገንዘብ ከፌደራል ወደ ክልል ከዚያም ወደ ከተሞቹ ስለሚወርድ ለሥራ አመቺ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሴፍትኔት ሥራው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚሰራ መሆኑን የጠቆሙት ቡድን መሪው አንዳንዴ የኔ ሥራ አይደለም በሚል ወደ ኋላ የሚሉ መኖራቸውን ጠቅሰው ይህ ደግሞ የሥራ መጓተትን የሚያስከትል በመሆኑ ሥራውን በመቀናጀት መሥራት እና የሴፍት ኔት ተጠቃሚዎችን ሕይወት መቀየር ይኖርብናል ብለዋል፡፡
More Stories
“ትልቅ ዓላማ ይዞ መነሳት ከሁሉም ይበልጣል” – ወጣት ነፃነት ምትኩ
“የሳሙና ተብሎ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር” – አቶ ደረጀ ሞገስ
“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ