በደረሰ አስፋው
በምትኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ ሴቶችን ወደ ህልማቸው እና ወደ ነፍሳቸው ጥሪ እንዳይሄዱ ሊከለክሉ የሚችሉ የተለያዩ አመለካከቶች ወይም አስተሳሰቦች ቢኖሩም፤ እሷ ግን ጫናዎችን ጥሳ በመውጣት ህልሟን ማሳካት ችላለች፡፡ በዚህም ‘እኔ መስራት የምፈልገው ይሄን ነው፤ መስራት የምፈልገውም በዚህ መንገድ ነው’ በማለት በጨቅላ ህጻናት ሀኪምነት ላለፉት 14 ዓመታት አገልግላለች፡፡
በቤት ውስጥ የስራ ጫና፤ በማህበረሰቡ ውስጥ ደግሞ መገፋት ቢኖርም እነዚህን ሁሉ ተቋቁማ ዛሬ ላይ በምትወደው ስራ በመሰማራቷ ደስተኛ እንደሆነች ነው የምትገልጸው፡፡ መስራት ወደምትፈልገው የሙያ ዘርፍ በማተኮርም በማህበረሰቡ ውስጥ ያበረከተችው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አስተሳሰብን ተገዳድራ በስራ ከመሰማራት በተጨማሪ ቤተሰብ መስርታ የሁለት ልጆች እናት በመሆኗም ደስተኛ እንደሆነች ታነሳለች።
በሀዋሳ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ሲስተር ፍሬህይወት ሙርሼ በዲፕሎማ የጀመረው የነርሲንግ ስራዋም አድጎ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በተመሳሳይ ሙያ አግኝታለች፡፡ የተጓዘችበትን መንገድ ወደ ኋላ መለስ ብላ ስታስታውስ እዚህ ለመድረስ ቀላል የማይባሉ መሰናክሎችን ማለፏን ነው የምታወሳን፡፡
የህክምና ስራ ህይወትን የሚያህል የገዘፈ ሀላፊነትን በመሸከም የሚሰራ በመሆኑም ልዩ አክብሮት አላት፡፡ ወደ ሙያው ስትገባም ካጋጠማት ሁለት አማራጮች ውስጥ ህክምናን መምረጧም ከዚህ የመነጨ እንደሆነ ነው የጠቆመችን፡፡ ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት አደራ ተሸክማ የምትሰራው ሙያ በመሆኑ ስራው አስቸጋሪና ተግዳሮት ያለው ቢሆንም እንኳ በሀላፊነት ስሜት መስራት ይገባል ነው ያለችው፡፡
ሲስተር ፍሬህይወት ሙርሼ ተወልዳ ያደገችው ሀዋሳ እንደመሆኑ ትምህርቷንም በሀዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ትቅደም አንደኛ ደረጃ እና በአዲስ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማረችው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ማጠቃላያ ፈተናን ጥሩ ውጤት በማምጣቷ ሀዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ3 ዓመታት ከተከታተለች በኋላ በነርስ ሙያ በዲፕሎማ ተመረቀች፡፡
ከሙያ ስልጠና በኋላ በሀዋሳ አዳሬ እና አላሙራ ጤና ጣቢያዎች አገልግላለች፡፡ አሁን ደግሞ በአዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል በጨቅላ ህጻናት ክፍል እያገለገለች ትገኛለች፡፡ አቅምን በትምህርት እያጎለበቱ መሄድ ለሙያዋ መጎልበት አስፈላጊ መሆኑን የተረዳችው ሲስተር ፍሬህይወት ከስራው ጎን ለጎን በመማር በ2009 ዓ.ም ከሪፍት ቫሌ ኮሌጅ በማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃለች፡፡
“በማህበረሰቡ ካለው ባህላዊ ተጽእኖ አኳያ ሴትነት ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ነው፡፡ ችግሩ ከቤተሰብ ይጀምርና በማህበረሰቡም ጎልቶ ይታያል፡፡ ለመማር እንኳ እንደ ወንዶች እኩል መብት ያለው አይደለም፡፡ እድል ከሷ ጋር የሆነላት ሴትም ብትሆን በቤት ውስጥ ያለው የስራ ጫና የታሰበውን ለማሳካት የሚፈታተን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለተጽእኖዎች ባለመንበርከክ ካሰብኩት ደረጃ ላይ መድረስ ችያለሁ”
በቤት ውስጥ የሚያጋጥመውን የስራ ጫናን ለመቀነስ በትምህርት ቤት ያላትን ጊዜ በአግባቡ ትጠቀም እንደነበርም ነው የምታስታውሰው፡፡ በቤትም ውስጥ ሴት ነኝ፤ አልችልም የሚለውን አስተሳሰብ ከአእምሮዋ በማውጣት እችላለሁ የሚለውን ጥንካሬ በመላበስ ለዛሬው መብቃቷንም ታነሳለች፡፡ “ሴት ነኝ ብዬ ወደ ኋላ ከሚጎትቱ ጎጂ ባህሎች እራሴን ተጋላጭ አለማድረጌ እንደጠቀመኝ እገነዘባለሁ፡፡
ይህ ተጽእኖ ቤተሰብ መስርታና ልጆች አፍርታም ቢሆን ጫናው ከፍተኛ ነው። ይሁን እንጂ ስራ እና ቤት የየቅል ናቸው የምትለው ሲስተር ፍሬህይወት ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀም የቤቷንም ሆነ የተሸከመችበትን የህክምና ሙያ ኃላፊነት ሳትበድል እንደምትሰራ ታነሳለች፡፡ “ሴት በመሆናችን ብቻ የሚደርሱ በርካታ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለውጤት ለመድረስ የሚከለክል ነገር የለም፡፡”
በስራው ለመሰማራት የቻለችው በሙያው ከነበራት የውስጥ ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ታነሳለች፡፡ ይህ ሲባል ግን አርአያ የሚሆኑ ሰዎችም በጎ ተጽእኖ ማሳደራቸው እንደማይቀር ነው የተናገረችው፡፡ ስራቸውን የሚወዱና የሚያከብሩ፣ የሰውን ህይወት ለማትረፍ ዕለት ዕለት ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ፣ ሙያቸውን የሚያከብሩ የስራ ባልደረቦቿን መመልከቱም ይበልጥ ስራውን እንድትወድ እንዳደረጋት አልሸሸገችም፡፡
“ትምህርቴን እንዳጠናቀኩ ሁለት የስልጠና ማስታወቂያዎች ወጡ፡፡ የመምህርት እና የህክምና ስልጠና ነበር፡፡ ካለኝ የውስጥ ፍላጎት መነሻም የህክምናውን ዘርፍ በመምረጥ ውድድሩን አልፌ ወደ ማሰልጠኛ መግባት ቻልኩ ነው ያለችው”
በሙያዋ ተሰማርታ ህዝብን ማገልገል ከጀመረች 14 ዓመታትን ማስቆጠሯን የምትገልጸው ሲስተር ፍሬህይወት በነዚህም አመታት ደስተኛ የስራ ጊዜ ስለማሳለፏ ነው የተናገረችው፡፡ የራስ ተነሳሽነቱ እንዳለ ሁሉ ከሷ ጀርባ የቤተሰቧ በተለይም የአባቷ ድጋፍና አይዞሽ ባይነትም እዚህ ለመድረሷ አግዟታል። “ይሁን እንጂ እኔ ብርቱ ማንነትን ባልላበስ ደግሞ እዚህም ባልደረስኩ ነበር” ትላለች፡፡
ሲስተር ፍሬህይወት የህክምና ሙያ ከበአል ጋር ሲገጣጠሙ ፈታኝ የሚባለው ጊዜ እንደሆነ ታነሳለች፡፡ በዓል ከእናትነት፣ ሴትነት እና ሙያ ጋር ሲገናኙ ጫናው ከፍተኛ መሆኑ እንደማይቀር የማይካድ ሀቅ እንደሆነ በመጠቆም፡፡ ይሁን እንጂ በዓልን በማክበር ከሚገኘው ደስታ ይልቅ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ማትረፉ ደግሞ የሚያስገኘው የመንፈስ እርካታ በምንም የሚተመን ባለመሆኑ አጋጣሚው ሲፈጠር ለሥራዋ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ነው የተናገረችው፡፡
“የህይወቱን አደራ ለሰጠኝ ማህበረሰብ የምሰጠው አገልግሎት ቀዳሚው ሊሆን ይገባል፡፡ ቀን ሙሉ አለያም ሙሉ ሌሊት አዳርም በስራ ላይ የምንሆንበት አጋጣሚም አለ፡፡ ቢሆንላቸው ህሙማንም በቤታቸው በአሉን የሚያሳልፉ ናቸው፡፡ በአጋጣሚ ግን ለህመም ተጋለጡ፡፡ እነዚህ አካላት ደግሞ በህይወት የመኖራቸው እጣ ፈንታ ያለው በእኔና በሌሎች ባለሙያዎች በመሆኑ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የበአል ቀንም ቢሆን ስራውን ደስተኛ ሆነን የመስራታችን ሚስጥርም ከዚህ የመነጨ ነው” ትላለች፡፡
አሁን እየሰራችበት ያለው ሙያ የጨቅላ ህጻናት እንክብካቤ ላይ ነው፡፡ ይህ ክፍል ህጻናት ከምንም በላይ ትኩረት የሚፈልጉበት ነው፡፡ በስራ ላይ ለአፍታም ቢሆን ከፊታቸው ፈቀቅ የማይባልበት ስፍራ በመሆኑ በቤት ሆኖም እረፍት የሚሰጥ እንዳልሆነም ታነሳለች፡፡ እንቅልፍ በአይኗ ዝር ሳይል አብራቸው ታድራለች ደግሞም ትውላለች። በዚህም የበርካታ ጨቅላ ህጻናትን በህይወት የመኖር ተስፋቸው በማለምለም በምታበረክተው ስራዋ ፍጹም ደስታ እንደሚሰማት ነው የተናገረችው፡፡
በርካታ በጽኑ የታመሙና ጊዜያቸው ሳይደርስ የተወለዱ ጨቅላ ህጻናት ጭምር በዚሁ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እናት ለዘጠኝ ወር አርግዛ ደክማ ያገኘችውን ህጻን ህይወት በማስቀጠል ታቅፋ ወደ ቤቷ ስትመለስ የሚሰማው ደስታ ከወላጅ እናት ባልተናነሰ መልኩ ለህክምና ባለሙያው የሚሰጠው ደስታ የተለየ ነው፡፡ እነዚህን ህጻናት ተንከባክቦ በህይወት እንዲቀጥሉ ማድረጉ በዋዛ የሚገኝ ሳይሆን ብዙ ዋጋ የተከፈለበት በመሆኑ ስራው አስደሳች እንጂ የሚያስከፋ ወይም የሚያማርር አይደለም ስትል ታስረዳለች፡፡
ከመምህር አባት አብራክ የተገኘችው ሲስተር ፍሬህይወት በወላጅ አባቷ በስነ-ምግባር ታንጻ እንድታድግ እንደጠቀማት ትገልጻለች፡፡ ብርቱ ከሆኑ አባቷ ብርታትን ተላብሳለች፡፡ ርህራሄ ካላቸው አባቷ ርህራሄን ለብሳለች፡፡ ሀላፊነትን መሸከም ከሚችል ትከሻቸው ልምድ ቀስማበታለች፡፡ ይህ ኃላፊነትን፣ አደራንና ብርታትን የመሸከም አቅምን ከወላጅ አባቷ በመውረሷ ዛሬ ላይ ጥንቃቄ የሚፈልገውን የህጻናት ህክምና ለመስራት አግዟታል፡፡
“ይህን በጎ ተጽእኖ ከቤተሰቤ ተላብሼ ማደጌ በህክምናው ዘርፍ ጠቀሜታ ማሰደሩ አልቀረም፡፡ ያለፍኩባቸው የስራ ቆይታና ልምድም የተሻለ ባለሙያ እንድሆን አግዞኛል። በተመሳሳይ የስራ ባልደረቦቼ ውስጥ ተነግሮ የማያልቅ በርካታ የህይወት ተሞክሮ በኔ ላይ በበጎነት የሚገለጹ ልምድ የቀሰምኩበት ነው። የስራ ተነሳሽነትን የሚያጎለብቱ ሰዎች ጋር መስራትም ጥቅሙ ብዙ ነው” ትላለች፡፡
ሲስተር ፍሬህይወት ወደ ፊት አሁን የምትሰራበትን የጨቅላ ህጻናት እንክብካቤ ሙያን ወደ ተሻለ ሙያ ለማሳደግ ነው እቅዷ፡፡ ስራው አድካሚና በኃላፊነት ስሜት የሚሰራ ቢሆንም ከዚህ ሙያ ግን ለመሸሽ አሰባ እንደማታውቅ ታነሳለች፡፡ ይህንንም በትምህርት በማሳደግ የተሻለ የህዝብ አገልጋይ ለመሆን ነው ሀሳቧ፡፡ ማንኛውም ባለሙያ ሙያውን ዓለም አቀፍ በሚባል ደረጃ ማሳደግ ይፈልጋል፡፡ እኔም ሙያውን ለመሸሽ ሳይሆን በዚሁ እውቀቴን በማሳደግ የነገ ተስፋ የሆኑትን ህጻናት ህይወት የማለምለም ሀሳብ ነው ያለኝ፡፡ ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያከበረ የጤና አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነትን ተሸክሜ ነው ምንሰራው፡፡ ህጻናት ፍቅር የሚያሲዙ ናቸው፡፡ ከነሱ ከመለየት ይልቅ የሙያ አቅምን አሳድጎ ጥሩ አገልጋይ መሆን ነው ምርጫዬ” ስትልም ከሙያው የመሸሽ ፍላጎት እንደሌላት ታስረዳለች፡፡
ሲስተር ፍሬህይወት በኢትዮጵያ ላሉ ሴቶች ምክር አለኝ ትላለች፡፡ በዛሬው ወቅት የባልን እጅ ብቻ እያዩ ለመኖር የሚቻልበት ጊዜ አለመሆኑን ታነሳለች፡፡ በትምህርት አቅማቸውን ማሳደግ ባይችሉም እንኳ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተሰማርተው እራሳቸውን መደገፍ ይገባቸዋል ነው የምትለው፡፡ ሁሌ የባልን እጅ ማየት ሳይሆን ባልንም በመደገፍ ከጓዳ መውጣት አለባቸው፡፡ በአንድ እጅ ብቻ ማጨብጨብ እንደማይቻል ሁሉ በአንድ ሰው ስራ ብቻ ኑሮን ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ስራ ችግርን ለማሸነፍ ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ በቤት ውስጥ በመመካከር እራስን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል መልዕክቷ ነው፡፡
More Stories
“ትልቅ ዓላማ ይዞ መነሳት ከሁሉም ይበልጣል” – ወጣት ነፃነት ምትኩ
“የሳሙና ተብሎ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር” – አቶ ደረጀ ሞገስ
“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ