የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን ዶክተር ዘላለም ታፈሰ ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስነ ምግብ ትምህርት ክፍል በመምህርነት፣ በተመራማሪነትና በስራ ክፍል ኃላፊነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በስነ ምግብ ሙያ የዶክትሬት ድግሪ ያላቸው ሲሆን በዘርፉ ከ15 አመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ በቆይታችን በበዓላት ወቅት ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት ምን መምሰል እንዳለበትና ተያያዥ ጉዳዮችን እንስተን ለእናንተ ለአንባቢያን በሚመጥን መልኩ አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
በመለሠች ዘለቀ
ንጋት፡- በመጀመሪያ ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ዘላለም፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- የሰው ልጅ ከምግብ ማግኘት ያለባቸው አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ዘላለም፡- የሰው ልጅ ራሱን የቻለ ንጥረ ነገሮችን ይፈልጋል፡፡ እነዚህም በዕድሜ ክልል፣ በጾታ እና በጤና ሁኔታ የሚፈልጋቸው ንጥረ ነገሮች በጣም ይለያያሉ፡፡ ንጥረ ምግብ የምንላቸውን በስድስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ እነሱም ፕሮቲን፣ ካርቦ ሀይድሬት፣ ቫይታሚን፣ ሚኔራል፣ ውሃ፣ ፋት እና ፋይበር ናቸው፡፡ ካርቦሃይድሬትስ የሰውነታችን ዋነኛ የኃይል ምንጭ ነው። ይህም በፍራፍሬ፣ በአትክልት፣ ዳቦ፣ ሩዝ እና ጥራጥሬዎች ውስጥ ይገኛል፡፡
ፕሮቲኖች ለሰውነት እድገት እና እራስን ለመጠገን አስፈላጊ ናቸው፡፡ በዋነኛነት በስጋ፣ በአሳ፣ በእንቁላል፣ በወተት ተዋጽኦዎች፣ ጥራጥሬዎች እና ለውዝ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ስብ ለአእምሮ ጤና፣ ጉልበት፣ የተወሰኑ ቫይታሚኖችን ለመምጠጥ እና ለቆዳ፣ ለፀጉር እንዲሁም ለመገጣጠሚያዎች ጤና ያስፈልጋል። የስብ ምንጭ ከሆኑት መካከል ዘይት፣ ቅቤ፣ አቮካዶ እና የሰባ ዓሳ ይገኙበታል።
ሰውነት በደንብ እንዲሠራ ቫይታሚኖች እና ማዕድናት አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነዚህም በተለያዩ ምግቦች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ወተት እና ስጋን ጨምሮ ምንጮች ናቸው፡፡
ውሃ ለጤና በጣም አስፈላጊ ንጥረ ነገር ነው፡፡ ለምግብ መፈጨት፣ ምግብን ለመምጠጥ እና ከሰውነት ውስጥ ቆሻሻን ለማስወገድ ይረዳል።
እነዚህን ንጥረ ነገሮች በተመጣጠነ መልኩ በእድሜ ክልል፣ በጾታና በሁኔታዎች በመወሰን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው እነዚያን የንጥረ ምግብ አይነቶችን በተገቢ ሁኔታ ማግኘት አለበት፡፡
ንጋት፡- ጤናማ አመጋገብ ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር ዘላለም፡- ጤናማ አመጋገብ ማለት፡- ንጽህናው የተጠበቀ፣ ሰውነታችን የሚፈልጋቸውን ንጥረ ነገሮች ያሟላ፣ በበቂ ሁኔታ አንድ ሰው ሲያገኝ ጤናማ አመጋገብ ተመግቧል ማለት ይቻላል፡፡
ጤናማ ህይወት ለማግኘት በሚደረገው ጥረት አመጋገብ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የተመጣጠነ አመጋገብ የጥሩ ጤና የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ ጤናማ ክብደትን እና የአኗኗር ዘይቤን ለመጠበቅ ወይም ለማግኘት ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው አስፈላጊ ነው።
የተመጣጠነ አመጋገብ ሰውነት ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲሠራ የሚያስፈልጉትን ንጥረ ነገሮች ያቀርባል፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ከሌለ ሰውነት ለበሽታ፣ ለድካም እና ለዝቅተኛ አፈፃፀም በጣም የተጋለጠ ነው፡፡
የተመጣጠነ አመጋገብ ለሰውነት በትክክል እንዲሰራ የሚያስፈልጉትን ንጥረ ነገሮች ይሰጠዋል፡፡ ከአመጋገብ ተገቢውን የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት፣ አብዛኛውን የቀን ካሎሪን በሚከተሉት ውስጥ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
የተመጣጠነ አመጋገብ ለጤናማ እድገት እና እንቅስቃሴ የሚያስፈልጉትን ሁሉንም አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች ትክክለኛ መጠን ይይዛል። የተመጣጠነ አመጋገብ ጤናማ የሰውነት ክብደትን ለማግኘት እና ለመጠበቅ የተለያዩ አይነት ምግቦችን በትክክለኛው መጠን እንዲሁም ትክክለኛውን ምግብ እና መጠጥ መውሰድን ያጠቃልላል።
ንጋት፡- ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ስርዓትስ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ዘላለም፡- ምግብ ማለት ማንኛውም የሚበላና የሚጠጣ ነገር ሁሉ ምግብ ብለን ነው የምንወስደው። ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ማለት በበቂ ሁኔታ ስውነታችን እንደየዕድሜያችንና ጾታችን የሚፈልገውን የምግብ ይዘቶችን ያላሟላ ከመጠን ያለፈ ወይም ከመጠን ያነሰ አመጋገብ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ይባላል። ከዚህም ባሻገር ሰዎች በአመጋገብ ላይ የሚሰሯቸው ጉልህ ስህተቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንደኛው ንጥረ ነገር በጣም የበዛበት፣ ነገር ግን ሌሎች ንጥረ ነገሮች ያነሱበት ከሆነ እንዲሁም ሰውነታችን የማይፈልጋቸውን ንጥረ ነገሮች ስንጠቀም ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ልንለው እንችላለን፡፡
ንጋት፡- የአንድ ሰው ጤንነት በአመጋገብ ላይ ሊወሰን ይችላል?
ዶክተር ዘላለም፡- በትክክል፡፡ የአንድ ሰው ጤንነት ከሚወሰንባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው አመጋገባችን ነው። ምክንያቱም አመጋገባችን ሰውነታችንን ለመገንባት፣ ከበሽታ ለመከላከል፣ ለጤናማ እድገት እና ለአካዊና ለአእምሯዊ ጤንነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡
ንጋት፡- በበዓል ወቅት ጤናማ አመጋገብን እንዴት መከተል እንችላለን?
ዶክተር ዘላለም፡- አንድ ሰው ጤናማ አመጋገብ ተከትሏል ለማለት ከላይ ከተጠቀሱት የንጥረ ምግብ ይዘቶች ውስጥ በተመጣጠነ ሁኔታ ማግኘት መቻል አለበት፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን በበዓላት ወቅት የእንስሳት ተዋጽኦ ስጋ፣ በተለይ ደግሞ ጮማነት የበዘባቸው ምግቦች፣ ቅቤና ወተት፣ በብዛት በተመሳሳይ ጊዜ የመጠቀም ልምድ አለን፡፡ እነዚያ ነገሮች ለሰውነታችን ከሚሰጡት ጠቀሜታ በተቃራኒ መልኩ ጤናችንን ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ነገሮች አመጣጥነን መጠቀም መቻል አለብን፡፡
በበዓላት ወቅት ከወትሮው በተለየ መልኩ የተለያዩ የምግብና መጠጥ ዓይነቶችን መመገብ የተለመደ ነው፡፡ የበዓላት ወቅት አመጋገብ በተለያየ ሁኔታ ጤና የሚነሳ ወይም ላልተጠበቀ አደጋና ሕይወት ማለፍ ሊዳርግ ይችላል፡፡
በአብዛኛው የበዓል ሰሞን አመጋገብ ብዙዎችን ለተለያዩ ችግሮች ሲጥል ይስተዋላል። ለዚህ ምክንያቶቹ ደግሞ ከመጠን በላይ መመገብ፣ ስጋና የእንስሳት ተዋጽዖን ማዘውተር እና ብዛት ያላቸው የአልኮል መጠጦች መውሰድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ጤናማ የበዓል አመጋገብን በመከተል ጤናን መጠበቅ ያስፈልጋል።
ንጋት፡- ይህን ለመከላከል ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ዶክተር ዘላለም፡- የአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን የበዓል አመጋገብ ተመሳሳይ ነው። የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ማለትም ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ እና መሰል ምግቦችን መመገብ የተለመደ ነው። ይህ ደግሞ ጨጓራ በአንድ ጊዜ ለመቀበል ይቸገርና ለሕመም ይዳርጋል። ለበዓል ቅባት የበዛበት ምግብ ማዘጋጀት የተለመደ ቢሆንም፣ መጥኖ መሥራት ተገቢ በመሆኑ ጤናን ለመጠበቅ ሠውነትን ቀስ በቀስ አለማምዶ መመገብ ያስፈልጋል።
የእንስሳት ተዋጽኦ የበዛባቸው ምግቦች ሰውነታችን በ24 ሰኣት ውስጥ ሊፈልግ ከሚችለው በላይ ስለሆነ ሆድ ከመሙላት ባለፈ ጥቅም የለውም፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እነዚህ ቅባት የበዛባቸው ምግቦች ሰውነታችን ላይ ላይድኑ የሚችሉ በሽታዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
ማንም ሰው ጤናማ አመጋገብን መከተል ለዘላቂ ጤንነት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ በበዓላት አካባቢ እነዚህ ነገሮችን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በበዓል ወቅት ማኅበረሰቡ የሚመገባቸው የእንስሳት ተዋጽዖዎች በተፈጥሯቸው ከፍተኛ ቅባት አላቸው። በዚህም ጨጓራ ከለመደው ሥርዓት የወጣ አመጋገብ ማለትም ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ስንጀምር ሆድ መንፋት፣ ማቃጠል፣ ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና መሰል ሕመሞች ያስከትላል።
ንጋት፡- በበዓል ወቅት በተለምዶ አልኮል መጠጦችን አብዝቶ መጠጣት የተለመደ ነው። ይህስ እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ዘላለም፡- አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከእነዚህ ቅባት ከበዛባቸው ምግቦች በተጨማሪ አልኮል ነክ ነገሮችን በብዛት ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም በበዓል ወቅት ሰዎች አልኮልን በብዛት ይጠቀማሉ። ምክንያታቸው ደግሞ የምግብ መፍጨትን ያፈጥናል በሚልና በበዓል ወቅት እንደ መዝናኛ ስለሚቆጠር ነው። ነገር ግን፣ አልኮል አብዝቶ መውሰድ ጉበት በመጉዳት ቅድሚያውን ቦታ ይወስዳል። በበዓል ሰሞን ስጋን እና አልኮልን በአንድ ላይ መውሰድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ይህም ጤናማ ካልሆኑ አመጋገብ ውስጥ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
የእንስሳት ተዋጽኦ ምግቦች፣ ጮማና ቅቤ ጋር አልኮል በብዛት መጠቀም ጤናችንን በጣም ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችንና መጠጦችን አዘውትሮ መውሰድ ለልብ ድካም፣ ለስኳር፣ ለካንሰርና ለመሳሰሉት በሽታዎች ያጋልጣል።
ንጋት፡- አራት ነጫጭ ነገሮች፤ /ጨው፣ ጮማ፣ ስኳርና ቅባት/ ለጤና ጠንቅ ናቸው ይባላል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ዶክተር ዘላለም፡- ጨው፣ ጮማ፣ ስኳርና ቅባት የአለም ጤና ድርጅት ከወሰነው መጠን በላይ ከተወሰደ ሰውነታችንን ሊጎዱ ይችላሉ። ይህም ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ የእድሜ ልክ በሽታዎች ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ለስኳር፣ ለካንሰር፣ ለደም ግፊት፣ ለልብ፣ ለኩላሊት እና መሰል በሽታዎች የመጋለጥ እድሉን ከፍ ያደርጋል፡፡
በአብዛኛው የሚመከረው የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ምግቦችን በነጫጭ ስጋ መተካት መቻል አለብን፡፡ ማለትም በአሳ እና ዶሮ ስጋ ላይ ብናተኩር ይመረጣል፡፡
ንጋት፡- ጥሬ ስጋን በብዛት መመገብ የሚያስከትለው የጤና ጉዳት እንዴት ይለጻል?
ዶክተር ዘላለም፡- ጥሬ ስጋ ለሰውነታችን ያለው ጠቀሜታ ብዙ ነው፡፡ ጥሬ ስጋ ጥቅምም ጉዳትም አለው፡፡ በመጠኑ ከወሰድን ከስጋ ማግኘት የምንችለውን ንጥረ ነገር በአግባቡ እንድናገኝ ይረዳል። ለምሳሌ ስጋ በሚበስልበት ጊዜ የሚጠፉ ቫይታሚኖች አሉ፡፡ እነዚያን ቫይታሚኖች በተገቢው መልኩ ለማግኘት ያስችለናል። ነገር ግን ስጋን ሳይበስል መመገብ ለኢንፌክሽን ከማጋለጡም በላይ ለአንጀት ጥገኛ ትላትሎች የመጋለጥ እድሉን ያሰፋል። በመሆኑም አብስለን ብንመገብ ጥሩ ነው ስናበስለው ግን እሳት ሳይበዛበት መሆን አለበት፡፡ ጥሬ ስጋ በሳይንስ የተወገዘ አይደለም፡፡
ንጋት፡- በመጨረሻ በበዓል ወቅት ጤናማ አመጋገብን እንዴት መከተል እንዳለብን የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ዶክተር ዘላለም፡- በዓላት በሚደርሱበት ወቅት የደስታ ስሜቶች አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ተለያይተው ቆይተው የተነፋፈቁ ሰዎች በበዓል ይገናኛሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ መጠራራትና መገባበዝ ይበዛል፡፡ በዚህ ጊዜ ብሉልኝ ጠጡልኝ የሚባሉ አስገዳጅ ነገሮች ይኖራሉ፡፡
በተቻለ መጠን በተመጠነ መልኩ ብንመገብ በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ዶሮ በተለምዶ በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ተፈላጊ የሆነ ምግብ ነው፡፡ ይህንን ስንመገብ ብዙ ቅመማ ቅመምና ቅባት የበዛበት ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ ስጋና እንቁላል አለ፡፡ ይህም በፕሮቲን የበለጸገ በመሆኑ መጥነን መመገብ መቻል አለብን፡፡ ለምሳሌ ከዶሮ ስጋ ጋር አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን፣ ብንጠቀም ጥሩ ነው፡፡
በ24 ሰዓታት ውስጥ ከሁሉም የምግብ ክፍሎች ማለትም ከጥራጥሬ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ከእንስሳት ተዋጽኦ የተሰባጠረ ጤናማ አመጋገብን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የምግብ መጠንን በመቀነስና የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ አለመጠቀም በበዓል ወቅት የሚከሰቱ ሕመሞችን ለማስወገድ ይረዳል።
ንጋት፡- ስለሰጡኝ ሙያዊ ማብራሪያ በድጋሚ አመሰግናለሁ
ዶክተር ዘላለም፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
“ትልቅ ዓላማ ይዞ መነሳት ከሁሉም ይበልጣል” – ወጣት ነፃነት ምትኩ
“የሳሙና ተብሎ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር” – አቶ ደረጀ ሞገስ
“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ