በቀን ከ300 ኩንታል በላይ የካሳቫ ምርት በዘመናዊ መንገድ ማምረት ይችላል የተባለው ቤልሳም አግሮ ኢንዱስትሪ በአርባምንጭ ማዕከል ተመርቆ ተከፍቷል።
በፋብርካውና በእርሻው ከ100 በላይ ለአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተጠቁሟል።
በቦታው ተገኝተው መርቀው የከፈቱት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ኃላፊ እና ልዩ አማካሪ አቶ ማሄ ቦዳ እንዳሉት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በግሉ ዘርፍና በመንግስት ከፍተኛ ጥረት የምታደርገው በሀገር በቀል ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ተጠቃሚነትን ማሳደግ ላይ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኃላፊ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ እንደገለጹት፤ ቤልሰም አግሮ ኢንዱስትሪ የካሳቫ ምርትን በዘመናዊ መንገድ በፋብሪካው በማቀነባበር ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለአካባቢው ህብረተሰብ ተደራሽ ያደርጋል።
አክለውም ከ120 እስከ 150 ለአካባቢው ህብረተሰብ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።
የቤልሰም ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም ማራ በበኩላቸው፤ ይህ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር የሚያስችለውን የካሳባ ሥራሥርን በዘመናዊ መንገድ አቀነባብሮ ወደ ማህበረሰቡ ተደራሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የቤልሰም አግሮ ኢንዱስትሪ መሥራችና ባለቤት አቶ አቤል ዘሚካኤል እንዳሉት፤ ጥራቱን የጠበቀ የካሳቫ ምርትን በዘመናዊ መንገድ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
በሀገር በቀል ዕውቀት የታወቀውን የአካባቢውን እምቅ አቅም አጉልቶ በማሳየት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት ለማሳለጥ ከተሰጠው ትኩረት አንፃር ቤልሳም አግሮ ኢንዱስትሪ ሊጫወት የሚችለው ገንቢ ሚና ቀላል አይደለም ተብሏል።
ኮርፖሬሽኑ አልምቶ ከሚያስተዳድረው በአርባምንጭ ከተማ ሲቀላ አነስተኛና መካከለኛ የኢንዱስትሪ ክላስተር ማዕከል በሚገኘው ማቀነባበሪያ ሼድ ውስጥ ለማምረትና በዘርፉ ደማቅ አሻራ ለማሳረፍ ዝግጅቱን አጠናቋል።
በቤልሰም ኢንዱስትሪ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ሊዲያ አደሎ እና ሕዝቅኤል ምትኬ በሰጡት አስተያየት፤ በዘርፉ ገብተው ክህሎትና ልምድ ከመቅሰም ባለፈ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በቤልሰም አግሮ ኢንዱስትሪ ምረቃ የኮርፖሬሽኑ ቦርድ አባላት፣ የማኔጅመንት አባላት፣ የጋሞ ዞንና የአርባምንጭ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ: ሰለሞን አላሶ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በሩብ ዓመቱ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለመጀመሪያ ዙር ያሰለጠናቸውን ምልምሎች እያስመረቀ ነው
የፍትህ አስተዳድር ስርዓቱ ብቃትንና ሥነ-ምግባርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፍትህ ቢሮ አሳሰበ