ጥራት ያለውን ትምህርት ለዜጎች ለማድረስ እየተጉ ያሉትን ባለድርሻዎች ማበረታታት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ፋይዳው የጎላ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለፀ

‎”የትምህርት ጥራትና የተማሪዎችን ውጤት እናሻሽላለን” በሚል መሪ ቃል በ2017 ትምህርት ዘመን የተሻለ አስተዋጽኦ ላበረከቱ መምህራንና የጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎች የዕውቅና ሽልማት መርሃ-ግብር በጌዴኦ ዞን የወናጎ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት አካሂዷል፡፡

‎በመድረኩ የወናጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ እጅጉ እንደገለፁት፤ በሥራ አፈፃፀም ግንባር ቀደም የሆኑትን መምህራንና የጽ/ቤቱን ባለሙያዎች ለማበረታታትና ከወትሮው በላቀ ደረጃ በሥራ እንዲተጉ ታስቦ የተዘጋጀ የዕውቅና ሽልማት መርሃ-ግብር ነው፡፡

‎ባለፉት ጊዜያት በትምህርት ዘርፍ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን አቶ አበበ ገልፀዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ‎አቶ ዘማች ክፍሌ፤ ጥራት ያለውን ትምህርት ለዜጎች ለማድረስ እየተጉ ያሉትን ባለድርሻዎች ማበረታታት የትምህርትን ስብራት ለመጠገን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‎ጥሩ ሰነ ምግባር የተላበሰ ፍሬያማ ትውልድ ለመፍጠር አሁን ላይ ዋጋ በመክፈል በቅንነትና በታማኝነት የሚሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አቶ ዘማች አሳስበዋል፡፡

‎‎የትምህርት ለውጥ የሚመጣው በአንድ ጀንበር ባለመሆኑ የትምህርት ሥራችን ዋነኛ ተዋናዮች የትኛውንም ዋጋ በመክፈል ጥራት ያለውን ትምህርት ለዜጎች የማድረስ ሥራ በብቃትና ትጋት መሥራት እንደሚገባቸው አቶ ዘማች አክለዋል።

‎አሁን ላይ ትልቅ ደረጃ ደርሰው ሀገርንና ህዝብን እያገለገሉ ያሉትን ምሁራን ያፈሩ መምህራን መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ በቀጣይም የትምህርትን ሥራ ለማሳለጥ የተዘጋጀ የዕውቅናና ሽልማት ፕሮግራም ማዘጋጀታቸውን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መኮንን ጪጩ አስታውቀዋል፡፡

‎የትምህርት ባለሙያዎች በቀጣይ የትምህርት ሥራ ወቅት ያላቸውን እውቀትና ጉልበት ሳይሰስቱ በቅንነትና በታማኝነት ተማሪውን በመቅረፅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ መኮንን አሳስበዋል።

‎በመርሃ-ግብሩ ማጠቃለያ በ2017 በጀት ዓመት በትምህርት ሥራ ላይ የተሻለ አስተዋፅኦ ላበረከቱ መምህራንና የጽ/ቤቱ ባለሙያዎች የዕውቅናና የሽልማት ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

‎ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን