ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቅን ምክንያት በማድረግ የይርጋጨፌ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር በጋራ በመሆን የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቅን ምክንያት በማድረግ የይርጋጨፌ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር በጋራ በመሆን የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ

በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር በጋራ በመሆን “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል ነው የድጋፍ ሰልፉ የተካሄደው።

‎በድጋፍ ሰልፉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን፤ ግድባችን ከውስጥም ሆነ ከውጪ ሀይሎች ሲደርስበት የነበረውን ጫና በመቋቋም አይችሉም የተባለውን ፕሮጀክት በህብረት ሆነን ማጠናቀቅ በመቻላችን እንኳን ደስ አለን ሲሉ ተናግረዋል።

‎የባህር በር ጥያቄ ቅንጦት አይደለም ያሉት አቶ ታደለ፤ ቀጣይ ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ዜጎች ከመንግስት ጎን በመሆን የተለመደውን ትብብር ሊያደርጉ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

‎ሌላኛው በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የይርጋጨፌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ፤ የፀጥታው ምክር ቤት ጫና ሲያሳድርብን በአንድነት ተቋቁመን በመንግስታችን ግንባር ቀደም አስተባባሪነት መጨረስ ችለናል ብለዋል።

‎በወረዳውም ሆነ በከተማው እየተከናወኑ ያሉትን የልማት ስራዎች በአንድነት መንፈስ አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

‎በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተሳተፉት መካከል አቶ ክፍለ ጅክሶ እና አቶ አክሊሉ መኩሪያ፤ በግድቡ መጠናቀቅ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው ለቀጣይ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከመንግስት ጎን እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

‎በበድጋፍ ሰልፉ ላይ የተለያዩ መፈክሮች የተሰሙ ሲሆን “ከግድብ ወደ ወደብ”፣ “ግድባችን የአንድነታችን አርማ ነው”፣ “አባይ ዳግማዊ የአድዋ ድል ነው”፣ “ግድቡ የአንድነታችን እና የአብሮነታችን አርማ ነው”፣ “የባህር በሩንም በአንድነት እናሳካለን” የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።

ዘጋቢ: ‎ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን