የሴቶች 1500 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ከሰዓታት በኋላ ይካሄዳል

የሴቶች 1500 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ከሰዓታት በኋላ ይካሄዳል

በቶኪዮ እየተካሄደ በሚገኝው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሴቶች 1500 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ዛሬ ቀን ከ10:05 ጀምሮ ይካሄዳል።

በርቀቱ አትሌት ፍሬወይኒ ሃይሉ ኢትዮጵያን በብቸኝነት ወክላ ትወዳደራለች።

አትሌት ፍሬወይኒ ሃይሉ በ1500 ሜትር 3 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ከ16 ማይክሮሴኮንድ ያስመዘገበችው የግሏ ፈጣን ሰዓቷ ነው።

አትሌቷ ለዛሬው ፍጻሜ የደረሰችው የሁለት ዙር ማጣሪያዋን በብቃት በመወጣቷ መሆኑ ይታወቃል።

ፍሬወይኒ ሃይሉ እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ ኢውጅን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1 ሺህ 500 ሜትር ፍጻሜ ተወዳድራ አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።

የ24 አመቷ አትሌት ፍሬወይኒ በ1500 ሜትር በአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ2024 ግላስጎው ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ለሃገሯ ያስገኘችበት ትልቁ ስኬቷ ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ታሪክ በ1500 ሜትር በሁለቱም ፆታ ወርቅ ያሸነፈችው 1 ጊዜ ብቻ ነው።

እሱም በሴቶች በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ አማካኝነት እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 ቤጂንግ ላይ በተካሄደው ሻምፒዮና ላይ መሆኑ አይዘነጋም።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ