በፈረኦን ደበበ
አሁን አሁን በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች ለመኖር የሚመኟት ሀገር ነች አሜሪካ፡፡ ይጓጉላታል፤ ውጣ ውረዶችንም አልፈው ለመግባት ይመርጧታል፡፡ ምንም እንኳን በስደተኞች ላይ ያለው አስተያየት በተቀባይ ሀገራት በኩል አመርቂ ባይሆንም፡፡
ስደተኞቹ ለሚደርስባቸው ችግርና ጫና ግን እጅ አልሰጡም፡፡ የዕለት ተዕለት ህይወታቸውን ያሳምርልኛል በሚሉ ሥራዎች ተጠምደዋል እንጂ፡፡ ከጥቃቅንና አነስተኛ ጀምረው በሁሉም የልማት ሥራዎች ተሳትፏቸውን ቀጥለውበታል፡፡
አፍሪካ ኒውስ የተባለው የመረጃ ምንጭ ያወጣው ዘገባም ስደተኞች ምን ያህል ለሀገሪቱ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ያሳያል፡፡ በተለይ በግብርና ዘርፍ መሠማራታቸው ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች እንዲተርፉ እንዳስቻላቸውም አመልክቷል፡፡
“በአሜሪካ የሚኖሩ ስደተኞች ህይወታቸውን ለማቃናት ግብርና ይጀምራሉ” ብሎ በሰጠው ርዕስ ሥር ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሄዱ ዜጎችን የጠቀሰ ሲሆን የተሠማሩበት ሥራ የገቢ ምንጫቸው እንደሆነም አስታውቋል፡፡
አሁን እየተካሄደ ካለው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውድድር አንጻር ትልቅ ትርጉም ያዘለው ይህ ተግባር በስደተኞች ላይ የሚሰነዘሩ የተለያዩ ነቀፌታዎችን ለማስቀረት ሁሉ የሚረዳ ሲሆን እየደረሰባቸው ያለው የኑሮ ምስቅልቅል ለማስቀረትም ይረዳል፡፡
ያነጋገሯቸው ስደተኞች ከቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ እና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ እንደመጡ ያስታወቀው አፍሪካ ኒውስ መጀመሪያ በጦርነትና ፖለቲካዊ ጭቆና ምክንያት ሀገራቸውን ለመልቀቅ መገደዳቸውንም ነው የገለጸው፡፡
ከእነዚህ ስደተኞች አብዛኞቹ በአሁኑ ጊዜ የጓሮ አትክልቶችን በመሸጥ ኑሯቸውን እንደሚደጉሙና ይህ ሙያ በትውልድ ሀገራቸው ከለመዱበት ህይወት ጋርም እንደሚተሳሰር አውስቶ ውጤቱን ለማግኘት በፍጥነት የሚያድጉና ትንሽ ክብካቤ የሚፈልጉ ዘሮች መምረጣቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡
ካሮት፣ ድንች፣ ጐመን፣ ቃሌ፣ ኮላርድ ግሪንና እንዲሁም ስኳሽ የተባሉት ዝሪያዎችን መርጠው እያመረቱ እንደመሆናቸው፡፡
ከአርሶ አደሮቹ መካከል አስሊ ዩሱፍ አንዱ ናቸው፡፡ ድንች፣ ካሮትና ሌሎች የእህል ዓይነቶችን አምርተው አየሰበሰቡ መሆናቸውን የተናገሩት ሶማሊያዊው ስደተኛ ህይወታቸውን ለማሻሻል እየተጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የእነሱ ሌላው አስደናቂ የህይወት ገጽታ አነስተኛ የሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን መጀመራቸው ሲሆን ይህም ምርታቸውን ለአካባቢው ገበያ ወይም ላደጉበት ማህበረሰብ አባላት መሸጥ አስችሏቸዋል፡፡ ከዚህ ረገድ ግብርናው እራሳቸውን በገንዘብ ከማስቻል ባለፈ በውጭ ሀገር ደረጃ አመርቂ ኑሮ እንዲኖሩ ማስቻሉም ነው የተነገረው፡፡
አዲሱ የአሜሪካ ዘላቂ ግብርና ፕሮጀክት ዳይሬክተር የሆኑት ቶም ማጊም ለዜና ምንጮች በሰጡት አስተያየት የአርሶ አደሮቹን አበርክቶ አድንቀዋል፤ ሠፊ ሀገራዊ ጠቀሜታ መኖሩን በማመልከት፡፡
አርሶ አደሮቹ እራሳቸውን የቻሉ የንግድ ባለቤቶች እንደሆኑና ከድርጅታቸው ጋር በመተባበር ምርታቸውን ቀጥታ ማቅረብ መቻላቸውንም አብራርተዋል፤ እንቅስቃሴያቸው በዓላማ ላይ የተመሠረተና ከማህበረሰቡ ጋር ለመቀላቀል እንደሚረዳም በማመልከት።
የአሜሪካንን ህልም ለማሳካት ጠቃሚ ነው በተባለለት በዚህ ሥራ ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ ሌላ ሥማቸው ያልተገለጸ አርሶ አደርም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በግብይቱ ላይ ጠንካራ ውድድር ያለና አስቸጋሪ ብለው ሀሳባቸውን የሰጡት አርሶ አደሩ ሥራው የሚያስገኝላቸውን ጥቅም ግን አወድሰዋል፡፡
ለሽያጭ እና ኑሮ መደጎሚያ የሚሆን በቂ ምርት እያመረቱ መሆናቸውን የገለጹት እኚሁ አርሶ አደር በአሜሪካን ሀገር ላገኙት የሥራ ዕድልና ህይወትን ማሻሻል እንዲችሉ ለተፈጠረው ምቹ አጋጣሚ ሁሉ አመስግነዋል፡፡
ይህንን ሀሳብ ከዲጃ አሊው የተባሉ ሌላ ሶማሊያዊት ሲያጠናክሩም ደስታ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ የራሳቸው ሥራ እንዳገኙና በዚህም እንደተደሰቱ የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዋ ግብርና ያስገኘላቸው ትሩፋቶችንም ተናግረዋል።
በገንዘብ እራሳችንን ከመደጎም ባለፈ ከአሜሪካ ማህበረሰብ ጋር ለመዋኽድ፤ አቅም ለማግኘትና በአዲሱ ሀገር አዲስ ህይወት ለመጀመርም ረድቶናል ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ የዓለም ህዝቦችና በተለይ ተቀባይ ሀገራትን ያስጨነቀው ስደተኝነት እየተስፋፋ የሚገኝ ክስተት ነው፡፡ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ደግሞ አባባሽ ምክንያቶች ሲሆኑ መፈናቀልና ለህይወት መጥፋትም ዳርጓቸዋል፡፡
እነዚህ አሳዛኝ እንቅፋቶችን አልፈው ወደ ባዕድ ሀገር ሲደርሱም ኑሮው አልጋ በአልጋ ሆኖ አይጠብቃቸውም፡፡ በማያውቁት ሀገር ኑሮን ለማቃናት ሲባል የሚያደርጉት ጥረት ሁል ጊዜ ያሳስባቸዋልና፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ባለ ታሪኮች እነዚህ ሁሉ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ኑሯቸውን አሀዱ ብለው የጀመሩ ናቸው፡፡ አነስተኛ ውጪ የሚፈልግና ከህይወት ልምዳቸው ጋር የሚጣጣመውን ዘርፍ መርጠው ተንቀሳቅሰዋል፡፡
የምግብ እህልን ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ እያቀረቡ ከአሜሪካ ማህበረሰብ ጋርም ቅርርብ ፈጥረዋል፡፡ የአሜሪካንን ህልም ለማሳካት ተዘጋጅተዋል ተብለው ክብርና ሙገሳም እያገኙ ያሉት እነዚህ የማህበረሰብ አባላት በተነሱበት ማህበረሰብ ላይ የሚነሱ ነቀፍፌታዎችን ለማስወገድም አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
More Stories
“ትልቅ ዓላማ ይዞ መነሳት ከሁሉም ይበልጣል” – ወጣት ነፃነት ምትኩ
“የሳሙና ተብሎ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር” – አቶ ደረጀ ሞገስ
“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ