በአንዱዓለም ሰለሞን
እ.ኤ.አ በ1974 መካሄድ የጀመረው የበርሊን ማራቶን፣ በተለያዩ ጊዜያት የዓለም ክብረ ወሰኖች የተሻሻሉበት ነው፡፡ ዘንድሮ ሀምሳ ዓመታትን በሚያስቆጥረው በዚህ ውድድር፣ በተለይም ከቅርብ ዓመታት በኋላ የኬንያ እና ኢትዮጵያ አትሌቶች ውጤታማ ሆነውበታል፡፡
በውድድሩ ጅማሮ የምዕራብ ጀርመን አትሌቶች፣ በተለይም ደግሞ በወንዶቹ ምድብ የበላይነታቸውን አሳይተዋል፤ ከ1974 እስከ 1980 ባሉት የውድድር ጊዜያት በወንዶች በተከታታይ በማሸነፍ፡፡
የአፍሪካዊያን ድል የሚጀምረው በ1987 ሲሆን የድሉ ባለቤት ደግሞ ታንዛኒያዊው፣ ሱሌይማን ንያምቢ ነበር፡፡ አትሌቱ በቀጣዩ ዓመት በተደረገው ውድድርም ያሸነፈ ሲሆን፣ በ1989 ደግሞ ሌላኛው ታንዛኒያዊ አትሌት፣ አልፍሬዶ ሻሀንጋ ውድድሩን በቀዳሚነት ለመፈጸም ችሏል፡፡
በ1995 ደግሞ ኬንያዊው አትሌት፣ ሳሚ ሌሊ የውድድሩ አሸናፊ ሆነ፡፡ ይህም የኬንያዊያን አትሌቶችን አሸናፊነት ያበሰረ ሆኖ፣ ከ1999 እስከ 2005 በተካሄዱት ውድድሮች በተከታታይ ለማሸነፍ ችለዋል፡፡
ከዚያ ቀጥሎ፣ ድሉ ወደ ኢትዮጵያ የዞረ ሲሆን ሀይሌ ገብረ ስላሴ፣ ከ2006 እስከ 2009 ለተከታታይ አራት ዓመታት በበርሊን ጎዳናዎች ደምቆ ታይቷል፤ በሁለቱ ውድድሮች የዓለምን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር፡፡
ከ1999 እስከ 2003፣ ለ24 ዓመታት ኬንያዊያን እና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊ በሆኑበት በዚህ ውድድር፣ ከሀይሌ ገ/ስላሴ የድል ዘመናት በኋላ፣ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት (ከ2009-2015) ኬንያዊያን አትሌቶች ውድድሩን በበላይነት ተቆጣጥረውታል፡፡ ቀነኒሳ በቀለ በ2016 እና 2019፣ እንዲሁም ጉዬ አዱላ በ2021 ከማሸነፋቸው ውጪ በሌሎቹ ውድድሮች ባለድል ሆነዋል፡፡
ወደ ሴቶቹ ምድብ ስንመጣ፣ ልክ እንደ ወንዶቹ ሁሉ፣ በውድድሩ ጅማሮ የምዕራብ ጀርመን አትሌቶች የበላይነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ከ1974 እስከ 1981 ባሉት 9 ተከታታይ ዓመታት ጀርመናዊያን አትሌቶች ያሸነፉ ሲሆን ጁታ ቮን ሀሴ (በ1974 እና 1979)፣ ዑርሱላ ብላስቼኬ (በ1976 እና 1978) ሁለት ሁለት ጊዜ ባለ ድል ሆነዋል፡፡
አፍሪካዊያን ወደ አሸናፊነት የመጡት በ1999 ኬንያዊቷ አትሌት፣ ቴጋላ ላውሮፔ አሸናፊ በሆነችበት ውድድር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት (ከ2000 እስከ 2006) ጃፓናዊያን አትሌቶች የበላይነቱን ይዘው ሲቆዩ፣ አትሌት ታካሀሺ ናኦኮ ደግሞ ሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ችላለች፡፡
በ2006 ኢትጵያዊቷ አትሌት ጌጤ ዋሚ 2:21:34 በመግባት በውድድሩ አሸንፋለች። በዓመቱ በተካሄደው ውድድርም፣ 2:23:17 በመግባት ዳግም ባለ ድል ሆናለች፡፡
ከዚህ በኋላ፣ በ2008 አንድ የጀርመን አትሌት (ኢሪና ሚኪቴንኮ) ጣልቃ ከመግባቷ በስተቀር፣ በቀጣዮቹ 14 ዓመታት የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች የድሉ ባለቤት ለመሆን ችለዋል፡፡
አትሌት አፀደ ሀብታሙ፣ በ2009፣ አበሩ ከበደ በ2010፣ 2012 እና 2016፣ ትርፌ ጸጋዬ፣ በ2014፣ አሸቴ በከሬ፣ በ2019፣ ጎይቲቶም ገ/ ስላሴ በ2021፣ እንዲሁም ትዕግስት አሰፋ፣ በ2022 እና 2023፣ ከኢትዮጵያ የውድድሩ አሸናፊዎች ናቸው፡፡
በበርሊን ማራቶን፣ በወንዶች 9፣ በሴቶች 3 ጊዜ የዓለም ክብረ ወሰን ተሻሽሏል። በወንዶቹ ከተሻሻሉት ሪከርዶች ውስጥ ስድስቱ በኬንያዊያን አትሌቶች የተሰበሩ ሲሆን፣ በ2003 ፖል ቲርጋት፣ በ2011 ፓትሪክ ማካዑ፣ በ2023፣ ዊልሰን ኪፕሳንግ፣ በ2014፣ ዴኒስ ኪሚቶ፣ በ2018 እና 2022 ኢልዊድ ኪፕቾጌ በውድድሩ መድረክ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆኑ አትሌቶች ናቸው፡፡
የተቀሩትን ሪከርዶች፣ በ1998፣ ብራዚላዊው ሮናልዶ ዳ ኮስታ፣ 2፡06:05 በመግባት ሲያሻሽል፣ 4 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ የሆነው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ደግሞ፣ በ2007 እና በ2008 ሪከርዱን መስበር ችሏል፡፡
ሀይሌ ገ/ስላሴ በ2007፣ በ34 ዓመቱ ሪከርዱን ሲያሻሽል የገባበት ሰዓት 2:4:26 ነበር፡፡ ምንም እንኳ፣ በወቅቱ በበርሊን የነበረው የዓየር ጸባይ ምቹ ያልነበረና ንፋሳማና ዝናባማ ቢሆንም፣ ጀግናው አትሌት ግን ከመነሻው እስከ መጨረሻው ከፊት በመምራት ውድድሩን አጠናቋል፡፡
ሀይሌ ገ/ ስላሴ በወቅቱ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያት፡-
“ውድድሩን 2:03 ለመፈጸም ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ በእርግጥ ያ ሊሆን አልቻለም፤ ያም ሆኖ ይህም ቢሆን ተዓምር ነው” በማለት ተናግሯል፡፡
ልክ ኬንያዊው፣ ፖል ቲርጋት ከአራት ዓመታት በፊት እንዳደረገው ሁሉ፣ ሀይሌ ገ/ ስላሴም የሁለተኛው አጋማሽ ሰዓቱ ከመጀመሪያው በተሻለ የፈጠነ ነበር፡፡ ሁለተኛውን አጋማሽ ለመሮጥ 61 ደቂቃ ከ57 ሰከንዶች ነበር የፈጀበት፡፡
ዝነኛው አትሌት፣ ውድድሩን ካጠናቀቀ፣ ከሰላሳ ደቂቃዎች በኋላ ሁለት ወሳኝ የስልክ ጥሪዎች ደርሰውት ነበር፤ የመጀመሪያው ከባለቤቱ ዓለም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ ከጓደኛው ፓል ቲርጋት፡፡ በስልክ ልውውጣቸው ወቅትም፣ ሀይሌ እየሳቀ ለቲርጋት እንዲህ አለው፡-
“ይቅርታ ፖል፣ በቀጣዩ ዓመት ሞክር፡፡”
በ2008፣ በ35 ዓመቱ ለማራቶን ውድድር ዳግም በበርሊን የተገኘው ሀይሌ ገ/ስላሴ፣ የራሱን ሪከርድ በ27 ሰከንዶች በማሻሻልና 2:3:59 በመግባት ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ክብረ ወሰንን ለማሻሻል ችሏል፡፡
ሙቀቱ በውድድሩ ጅማሮ 48፣ በፍጻሜው 55 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሆነበት ጸሀያማው የበርሊኑ እለተ ሰንበት፣ ሀይሌ ሌላ ታሪክ ለመስራት ችሏል፤ ምንም እንኳ በጤና እክል ምክንያት ለአንድ ሳምንት ያህል ከልምምድ ርቆ በመቆየቱ ይህ ይሆናል ብሎ እንዳልገመተ በወቅቱ ቢናገርም፡-
“በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ጥሩ ነበር፡፡ ለሳምንት ልምምድ ስላላደረኩ ጥርጣሬ ነበረኝ፡፡ ያም ሆኖ በመጨረሻ ሁሉም ነገር ጥሩ ሆኗል” በማለት፡፡
በእርግጥም ሀይሌ ገብረ ስላሴ በታዳጊነቱ፣ ገና ሩጫ በጀመረበት ወቅት ማራቶን መሮጥ ይመኝ ነበር፡፡ ይህን የልጅነት ምኞቱንም በዚህ መልኩ በደማቁ ጻፈው፡፡ የዚያን ጊዜም፣ “ህልሜ እውን ሆነ” በማለት ተናገረ፡፡
በሴቶቹ ምድብ፣ ጀርመናዊቷ አትሌት ክሪስታ ቫህሌንሴክ፣ በ1977፣ ኬንያዊቷ ቴጋላ ላውሮፔ በ1999፣ እንዲሁም ጃፓናዊቷ ናኦኮ ታካሻሺ፣ በ2001 የዓለምን ክብረ ወሰን ያሻሻሉ አትሌቶች ናቸው፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው