ብሄራዊ ቴያትር ከክልሉ 12 ዞኖች ለተውጣጡ ባለ ተሰጥኦዎች ምልመላ በአርባምንጭ ከተማ አካሄደ

ብሄራዊ ቴያትር ከክልሉ 12 ዞኖች ለተውጣጡ ባለ ተሰጥኦዎች ምልመላ በአርባምንጭ ከተማ አካሄደ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ብሔራዊ ቴአትር ለብሔራዊ ጥበብ መዳረሻ” በሚል መሪ ቃል ብሄራዊ ቴያትር ከክልሉ 12 ዞኖች ለተውጣጡ ባለ ተሰጥኦዎች ምልመላ በአርባምንጭ ከተማ አካሂዷል።

‎በምልመላው ማለፋቸውን ያረጋገጡት ባለተሰጥኦዎች ባገኙት እድል መደሰታቸውን ገልጸው የደቡብ ኢትዮጵያን ክልል እምቅ ጸጋ ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ በመድረኩ እንዳሉት፣ ቢሮዉ ባህላዊ የኪነ -ጥበብ ሀብቶችን ማልማትና ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነዉ።

‎ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋና ቱባ ማንነት ለማስተዋወቅ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ለመመልመል የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቴያትር በአርባምንጭ መገኘቱን ጠቁመዋል።

‎በክልሉ ከሚገኙ 32 ብሔረሰቦች የተወጣጡ ተሳታፊዎች በዉዝዋዜ፣ ድምፅና ትወና ዘርፍ ተወዳድረው የበለጠ የከወኑ ለብሔራዊ ቴአትር መመመረጠቸውን አቶ ታሪኩ አውስተዋል።

‎የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ባርክ ታደሰ ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበርካታ ቱባ ዕሴቶች ባለቤት መሆኑን አስረድተው ሃገሪቱን በአለም መድረክ ማስተዋወቅ የሚችሉ ልዩ ባለ ተሰጥኦዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል

‎በኢትዮጲያ ብሔራዊ ቴአትር የጥበባት ምዘናና ስልጠና ዋና አስተባባሪ አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ ፤ ኢትዮጲያን ከሚያስተዋዋውቁ በርካታ እሴቶች መካከል የኪነ-ጥበብ አንዱ እንደሆነ ገልፀዋል ።

‎ይህንን አውን ለማድረግ የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቴአትር ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ከደቡብ ኢትዮጲያ ክልል የድምጽ ፣ የውዝዋዜና የትወና ባለተሰጥኦዎች መመልመላቸውን ጠቁመዋል።

‎የኢትዮጲያ ብሔራዊ የቴአትር በሰጠው እድል ተወዳድረው ማለፋቸውን ያረጋገጡ ባለተሰጥኦዎች ባገኙት አድል መደሰታቸውን ገልጸው የወከሉትን ብሔርና የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል እምቅ ጸጋን ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።

‎ዘጋቢ ፡ አሰግድ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን