“ሴት ልጅ አልችልም ካለች እራሷን ጓዳ ቀብራ ነው የምትቀረው” – ወይዘሮ ህይወት ሽፈራው

በደረሰ አስፋው

ስልታዊ በሆነ መልኩ አቅደው ነው የሚሰሩት፡፡ በስራቸው ይሳካል የሚለውን የስነ- ልቦና ዝግጅት በማድረጋቸውም ስኬታማ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር እራስን ማላመድ መቻልም ስራቸውን በአግባቡ ለመምራት አግዟቸዋል፡፡ ለአዳዲስ ነገሮች ክፍት የሆነ ጭንቅላት መኖር በምንሰራው ስራ ስኬታማ እንድንሆን ይረዳናል ያሉ ሲሆን አዲስ ነገር ለመፍጠርም ጉጉ እንደሆኑም ነው የተናገሩት።

በእርግጥ ስኬት በቀላሉ አይመጣም። የመብራት አምፖልን የፈጠረው ቶማስ ኤዲሰን የፈጠራ ስራው የበርካታ መቶ ያልተሳኩ ሙከራዎች ውጤት ነው። በቃለ ምልልሱ ላይ “ከሁሉም ሙከራዎችህ በኋላ ምን ተሰማህ?” ተብሎ ተጠየቀ። የእሱ ምላሽ ጥሩ ነበር፣ “አልተሳካልኝም፣ አምፖሉን ላለመፍጠር በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገዶችን ተማርኩ” እያንዳንዱን “ሽንፈት” እንደ ትምህርት ተመልክቷል። ከዚያ ትምህርት የማይሰራውን ተማረ እና በምትኩ ሊሰራ ችሏል።

የዛሬው የእቱ መለኛ ባለታሪካችንም ስኬትን በመሻት በብዙ የስራ መስኮች ተሰማርተዋል። ወደ ውጭ ሀገር ተሰደዋል፡፡ በሻይ ቡና ስራም ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡ በተዘጋጁ የህጻናት አልባሳት ንግድና በሌሎችም እንዲሁ፡፡ በነዚህ የስራ መስኮች ብዙ ልምዶችን የቀሰሙበት ነበር። ሽንፈትን ሳይሆን ታታሪነትን አጎልብተውበታል። በጥረት ስኬት ሊመጣ እንደሚችል ተገንዝበዋል። ለዛሬውም ስኬታቸው መንገድ ከፍቶላቸዋል። ለስኬት የማይናወጥ ውሳኔ አስፈላጊ መሆኑንም አስተምሯቸዋል፡፡

ለለውጥ የተዘጋጀ አስተሳሰብ ያለው ሰው ግቡን ከመምታቱ የሚያግደው ምንም ነገር የለም ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ በስራ ላይ የሚያጋጥሙ አሉታዊ ሀሳቦችን በአዎንታዊዎቹ መተካት ይገባል። አዎንታዊ አስተሳሰቦችን ማጎልበት ከተቻለ እንቅፋቶችንም መሻገር ይቻላል በማለት። የተስፋ መቁረጥ ስሜት ራዕይን እንዳያግድ መፍቀድ አይገባም ባይ ናቸው፡፡

ጄሲ ፔኒ (የጄሲ ፔኒ መስራች) “ለስኬት 1 በመቶ መነሳሳት፣ 99 በመቶ ደግሞ ላብ ነው” ሲል ይገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ህይወት ሽፈራውም ይህን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ እውነተኛ ስኬት የሚገኘው ከስራ ነው። በህይወት ግብህ ላይ ካልሰራህ በጭራሽ ስኬታማ አትሆንም በማለት።

ወ/ሮ ህይወት ሽፈራው የተወለዱት በኦሮሚያ ክልል አቦምሳ መርቲ ጆጂ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ትምህርታቸውንም በወለንጭቲ ቦሰት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 9ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ስደትን እንደ አማራጭ በማድረግ ወደ ኩዌይት ሄዱ፡፡ በስደት ህይወትም ለ6 ዓመታት ቆይተዋል፡፡

ከስደት መልስ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ታቦር ክፍል ከተማ ፋራ ቀበሌ ትዳር መስርተው መኖር ጀመሩ፡፡ የትዳር ህይወት አለስራ የሚዋጥላቸው አልሆነም፡፡ እጅን አጣጥፎ በቤት መቀመጥ ትርጉም የሌለው ህይወት እንደሆነ ተገነዘቡ፡፡

በአረብ ሀገር የስራ ቆይታ ያጠራቀሟትን አነስተኛ ጥሪት በመያዝ በ50 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የተዘጋጁ የልጆች አልባሳት ንግድ ላይ ተሰማሩ። ይሁን እንጂ ስራው ባሰቡት ልክ አዋጭ ሆኖ አላጋኙትም፡፡ በዚህ ስራም ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ አልዘለቁም፡፡

በጥናት ላይ ተመሰረተ የስራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት መወጠን ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም አማራጭ ያደረጉት የስራ ዘርፍ የወተት ከብት እርባታ ነው፡፡ በከተማ ግብርና በ2 የወተት ላሞች ወደ እንስሳት እርባታው ዘርፍ ተሰማሩ። በወቅታዊ ገበያውም አንድ የወተት ላም በ150 ሺህ ብር ይሸጥ እንደነበር ነው የሚያስታውሱት፡፡ ዛሬ ላይ ይህ ስራቸው አድጎ የኑሯቸው መተዳደሪያ ነው፡፡ ለአካባቢያቸው ብሎም ለከተማው የወተት ምንጭ ሆነዋል፡፡ ይስተዋል የነበረውን የወተት ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠንን በመቅረፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በሁለት ላሞች የጀመሩት ስራም ዛሬ ላይ አድጎ ቁጥራቸው 14 ላሞች ደርሰዋል፡፡ ከነዚህም በቀን ከ120 እስከ 130 ሊትር ወተት ያመርታሉ።

ይህንንም ሊትሩን በ65 ብር ከአካባቢው የተረፈውን ለተረካቢዎች ያስረክባሉ። ወቅታዊ ገበያውን ከማረጋጋት አኳያ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት በሚል በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚያስረክቡም ነው የተናገሩት፡፡

ወ/ሮ ህይወት ባቋቋሙት የወተት ከብት እርባታ ለ3 ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ሰራተኞችም ከትንሹ ከ1 ሺህ 500 እስከ ትልቁ 3 ሺህ 500 ብር ተከፋይ እንደሆኑ ነው የገለጹት፡፡ የእንስሳቶችን ጤንነት የሚከታተል የጤና ባለሙያም በቋሚነት ስለመቅጠራቸውም ተናግረዋል፡፡

በማንኛውም ስራ አልጋ በአልጋ የሆነ ነገር የለም የሚሉት ወ/ሮ ህይወት በአላማ ጸንቶ ስራን በትጋት መፈጸም ለውጤት እንደሚያበቃ ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በእንስሳት እርባታው የላሞች መታመም አለፍ ሲልም መሞት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በዚህ ግን ተስፋ መቁረጥ አይገባም ባይ ናቸው፡፡ ችግር እንደሚያጋጥም አስቀድሞ መወሰንና ከችግሩ ለመውጣት ግን አፋጣኝ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን መከተልም እንደሚገባ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

የእንስሳት እርባታ ያልተቋረጠ ክትትልን እንደሚፈልግ የገለጹት ወ/ሮ ህይወት ንጽህናቸውን መጠበቅ ለጤንነታቸው አስፈላጊ ነገር ነው። “ካለባለቤቱ አይነድም እሳቱ” እንደተባለው ነውና ሰራተኛ አለ፤ ሀኪም አለ ተብሎ ከእንስሳቱ እግር ስራ እንደማይለዩ ነው የተናገሩት፡፡ በዚህም በርካታ ጥቅሞች እንዳገኙበትና ሊደርስባቸው የሚችለውን ኪሳራ መታደግ እንደቻሉ ነው የሚገልጹት፡፡

ወ/ሮ ህይወት ከአልባሳት ንግድ ወደ እንስሳት ንግዱ ለመሸጋገር ያነሳሳዎት ምንድነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ሲመልሱ፡-

“ቀደም ብዬ የልብስ ንግዱን ሳቋርጥ በጥናት ነበር፡፡ የልጆች ወተት ለመግዛት የወተት መሸጫ ቦታዎችን እቃኝ ነበር። የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ይስተዋል ነበር፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ወተት ለማግኘትም ፈተና ነበር፡፡ በወተት ከብት እርባታ መሰማራት ቢቻል ስራው አዋጭ መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡ ጥራቱ የተጠበቀ ወተት ለልጆች ማቅረብም እንደሚቻል ተገነዘብኩ፡፡ እነዚህና ሌሎች ምክንያቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ስራው ለመሰማራት ቻልኩ፡፡ ይህም ስራ ዛሬ ላይ ውጤታማ ሴት አድርጎኛል” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ወ/ሮ ህይወት አንድ ስራ ሲጀመር የተትረፈረፈ መነሻ ካፒታል የግድ አስፈላጊ ነው የሚል አመለካከት የላቸውም፡፡ ይልቁንም የአስተሳሰብ ልዕልናን እና የይቻላል መንፈስን ይዞ ወደ ስራ መሰማራት ቀዳሚው ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ነው የሚገልጹት፡፡ በዚህም የሚልቀውን ሀብት መፍጠር ይቻላል፤ የታሰበውንም ስኬት ማረጋገጥ ይቻላል ነው የሚሉት፡፡ እሳቸው ወደ ስራው ሲሰማሩ የጀመሩበት መነሻ ካፒታል ጥቂት እንደነበር በማስታወስ፡፡

ለስኬት ስደት አማራጭ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ አስተሳሰብን ካሳመኑ በሀገር ውስጥም ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ከልምዳቸው በመነሳት ይናገራሉ፡፡ በ6 ዓመታት የስደት ህይወታቸው ጊዜያቸውን ከማባከን በዘለለ ጥቅም ያገኙበት አለመሆኑን በመግለጽ፡፡ የባእድ ሀገር ስደት የብዙዎች ህይወት የሚቀጠፍበት አጋጣሚ በመኖሩ ስራን ሳያማርጡ መስራት ከተቻለ በሀገርና በወገን መካከል ሰርቶ መክበር እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህም የመንግስትም ድጋፍ ለውጤት እንደሚያበቃ ጠቁመው እሳቸውም የቤተሰባቸው አይዞሽ ባይነት እንደረዳቸው ነው የተናገሩት፡፡

የራሳቸው ተነሳሽነት ቀዳሚውን ስፍራ ቢይዝም የባለቤታቸውና የወንድሞቻቸው አይዞሽ ባይነትም ጉልበት እንደሆናቸው ይናገራሉ፡፡ ሴት ልጅ የዓላማ ጽናት ኖሯት ከሰራች ውጤታማ እንደምትሆን ነው የተናገሩት፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ አልችልም ሳይሆን እችላለሁ የሚለውን የስነ- ልቦናን ጥንካሬ ተላብሰው ማደጋቸውም ለስኬት እንዳበቃቸውም ይገልጻሉ፡፡

ሌሎች ሴቶችም አልችልም የሚለውን አስተሳሰብ ከውስጣቸው ሊያወጡ እንደሚገባ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡ “ሴት ልጅ አልችልም ካለች እራሷን ጓዳ ቀብራ ነው የምትቀረው” የሚለውን ሀሳብ በመሰንዘር፡፡

“የህይወትን ስኬት ለመጎናጸፍ ብዙ ስራ ሞክሬያለሁ፡፡ አስከፊውን ስደትንም ቀምሸዋለሁ። የመንገድ ዳር ሻይ ቡና ስራንም ሞክሬያለሁ፡፡ የልጆች አልባሳት ንግድንም እንዲሁ፡፡ በሁሉም ስራዎች አልችልም ሳይሆን አንድ ቀን ስኬታማ እሆናለሁ የሚል እምነት ነበረኝ፤ አሁን ይህ ሀሳቤ እውን ሆኖ ወደ ስኬት ጎዳና እየተንደረደርኩ ነው። በዚህም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ህይወት ወደ ፊት አሁን የጀመሩትን የወተት ከብት እርባታ ለማስፋፋት ነው ዕቅዳቸው። ወደ ትልቅ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በማሸጋገር ለበርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ በር ለመክፈት ነው ያሰቡት፡፡ ለዚህም በዝግጅት ላይ እንዳሉ በመጠቆም፡፡

በቅርቡ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በታቦር ክፍለ ከተማ በከተማ ግብርና ሞዴል ተብለው የምስክር ወረቀት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ካፒታላቸውም ወደ 6.5 ሚሊዮን ብር መድረሱን ነው የተናገሩት፡፡ ይህም የኦዲት ሂሳብ ሪፖርት ተደርጎ የተረጋገጠ መሆኑን በመጠቆም፡፡ አሁን ያለበት ወቅታዊ የወተት ላም ዋጋ እስከ 250 ሺህ ብር እንደሚሸጥም ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ስራ መሰማራታቸው ሀብት ፈጥረውበታል፡፡ የመኖሪያ ቤት ባለቤት አድርጓቸዋል፡፡ በተጨማሪም የመኪና ባለቤት እንዳደረጋቸውም ነው የገለጹት፡፡ ስራው ተግዳሮት እንዳለው ሁሉ ጠንክሮ ለሚሰራ ሰው አዋጭ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ዘርፉ ገና ያልተነካ (ያልተሰራበት) በመሆኑ ዕድሉንም ለመጠቀም ከተለምዶ አሰራር በመውጣት በዘመናዊ መልኩ ለመስራት ያላቸው ሀሳብ የተለየ ነው፡፡

ወ/ሮ ህይወት ሌሎች ሴቶች ከጓዳ ሊወጡ የሚገባ ወቅት ቢኖር አሁን እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ሴቶች ታታሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰርተውም መቆጠብ አለባቸው ባይ ናቸው፡፡ እሳቸው የሚያገኙትን ገንዘብ የሚያባክኑ ቢሆኑ ኖሮ ውጤት እንደማያገኙ ገልጸው ሌሎችም ስራን ሳይንቁ መስራትና ያገኙትንም ለታለመለት ዓላማ ብቻ ማዋል ይገባቸዋል ይላሉ፡፡

ዛሬ ላይ ልጆቻቸውን ያስተምራሉ፡፡ ሌሎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውንም ያስተምራሉ። ይህን ቤተሰብ ደግፈው ለቁም ነገር ለማድረስም የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ ለዚህም ቢሆን የወተት ከብት እርባታ ስራው ለእሳቸው የገቢ ምንጫቸው ነው፡፡ ባለቤታቸው ለሚሰሩት የንግድ ስራም እጅ ሲያጥራቸው ወ/ሮ ህይወት ጉድለታቸውን የሚሞሉ ናቸው፡፡ ይህ ተደጋግፎ መኖርም ቤተሰቡን ጭምር ደስተኛ እንዳደረጋቸው ነው የሚገልጹት፡፡

የእርባታ ስራቸው ተግዳሮት ያለበት እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ እሱም የቦታ ጥበት ነው፡፡ አሁን ላይ እየሰሩ ያሉት የመኖሪያ ቤት ግቢያቸውን ለሁለት በመክፈል ነው፡፡ የቦታ ጥበቱ ባይገድባቸው የት ይደርሱ እንደነበር ሲያስቡትም ቁጭት ይፈጥርባቸዋል፡፡ ካጋጠማቸው የቦታ ጥበት የተነሳ በቅርቡ ካሏቸው ከብቶች ላይ ለመሸጥ ስለመገደዳቸው ነው የተናገሩት፡፡ በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ያጋጠማቸውን የቦታ ጥበት ቢቀርፍላቸው እራሳቸውንም ጠቅመው ለሌሎችም መትረፍ እንደሚችሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡ እኛም መልዕክቱ ለሚመለከተው አካል ይድረስ ለማለት እንወዳለን፡፡