ቀይ ባህርና አሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ
አቶ በዛብህ ቡሾ ይባላሉ፡፡ ትውልድና ዕድገታቸው በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ደቂያ ቀበሌ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው አከባቢ ተከታትለዋል፡፡ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ደግሞ ወላጅ አባታቸው በማለፋቸውና የሚረዳቸው ባለመኖሩ ወንድሞቻቸው ወዳሉበት ጅማ ከተማ በማቅናት ሔርማታ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡
እስከ 10ኛ ክፍል በዚያው ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል፡፡
ታዲያ 10ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁ ብሄራዊ ወትድርና ጥሪ ሲመጣ ዕድሜያቸው የደረሱ ሁሉ እንዲዘምቱ መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡
እርሳቸውም የአንደኛ ዙር ዘማች በመሆን ጥሪውን ተቀብለው ወደ ውትድርናው ዓለም ተቀላቀሉ፡፡
ጦላይ የወታደር ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠናቸውን የተከታተሉት የያኔው ወጣት ዘማች የሆኑት በዛብህ፥ ከዚያም አዋሽ አርባ የውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ተኳሽ የመሆን የ9 ወራት ስልጠናቸውን ወስደዋል፡፡
ከስልጠናው ማግስት በሐረር አድርገው ጅግጅጋን አቋርጠው ደግ-ሀቡር፣ ቀብሪድሃር፣ ዋርደር፣ ወልዋልና ገላዲን የተባሉ ጠረፋማ አከባቢዎች ጭምር ለ 3 ዓመታት በውትድርና ለእናት ሀገራቸው ያገለገሉባቸው አከባቢዎች ናቸው፡፡ ከዚህም በማስቀጠል በክብር መመለስ ችለዋል፡፡
በ1981 ዓመተ-ምህረት ዳግም ጥሪ መደረጉን ተከትሎ ፤ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ወደ ኤርትራ ገቡ፡፡
በኤርትራ ደቀ-መሓሪ በምትባል አከባቢ ውግያ ላይ በነበሩበት ወቅት የደርግ ሰራዊት መፍረሱን የሚያስታውሱት አቶ በዛብህ፥ በብዙ መከራ ከኤርትራ ወደ ትግራይ ማለፋቸውን ይናገራሉ፡፡
ለ16 ቀናት በእግር ተጉዘው ትግራይን አቋርጠው ከኤርትራ ጎንደር መግባታቸውን የሚናገሩት አቶ በዛብህ “የኢትዮጵያ ህዝብ በየደረስንበት የሚበላውን የሚጠጣውን እያቀመሰን ጉዟችንን ቀጠልን” ይላሉ፡፡
ለአንድ ወር ያክል ጎንደር ባስጠጓቸው ሰዎች ቤት ቆይተው ወደ ቤተሰቦቻቸው (ወንድሞቻቸው ወዳሉበት ጅማ ከተማ) መመለሳቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በኃላ ነው እንግዲህ በ1984 ያቋረጡትን የ11ኛ ክፍል ትምህርት ቀጥለው በ1985 የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በጅማ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቅቀው ወደ ቦንጋ በመመለስ የመምህርነት ስልጠና ለመውሰድ ተወዳድረው በማለፋቸው አርባ ምንጭ በመሄድ ስልጠናቸውን ለአንድ አመት ተከታትለው ጨርሰዋል፡፡
ከዚያም በካፋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በመምህርነት፣ በርዕሰ-መምህርነትና በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ላይ በሙያቸው አገልግለዋል፡፡ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡
አቶ በዛብህ ቡሾ በተለይ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላይ ባላቸው ተሳትፎ መሠረት ቀይ ባህር እንዲሁም የአሰብን ወደብ ኢትዮጵያ ማጣቷ ሁሌም የሚቆጫቸው ጉዳይ መሆኑን እያነሱልን ቆይታ አድርገናል፡፡
ከአዲስ አበባ 882 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስለሚገኘው፣ 811 ኪ∙ሜ የሚሆነው በኢትዮጵያ በኩል ስላለው፣ ቀሪው 71 ኪሎ ሜትር ደግሞ በኤርትራ በኩል ስለሆነው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተካኼደውን ጦርነት ተከትሎ ለ20 ዓመታት ተዘግቶ ስለነበረው አሰብ ወደብ ከጣቢያችን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ዳግም ጥሪ ተቀብለው ወደ ኤርትራ ሲያቀኑ በአሰብ አድርገው 24 ሰዓት በመርከብ ተጉዘው ምፅዋ መሻገራቸውን ያስታውሳሉ፡፡ መዳረሻቸውም ከረን ተብላ የትምጠራ አውራጃ ናት፡፡ በመቀጠልም በኤርትራ የሚገኙ በርካታ አከባቢዎች ላይ ደርሰዋል፡፡ ደቀ-መሓሪ፣ መንደፈራ እና ሌሎችም ከፍተኛ ውግያ ባለባቸው አውራጃዎች ተገኝተዋል፡፡
ታዲያ የደርግ መንግስት መውደቅን ተከትሎ አሰብ ወደ ኤርትራ ተካለለች መባሉ ከፍተኛ ቁጭት እንዳሳደረባቸው ይገልፃሉ፡፡ በወቅቱ ለመከራከርም ሆነ ጉዳዩን ማንሳት የሚቻል ባለመሆኑ በአጠቃላይ “ስህተት ተፈጽሟል” ሲሉም ይወቅሳሉ፡፡
“ኤርትራ ሀገር ሆነች መባሉን የሰማነው ዘግይተን ነበር፣ እኛ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል መሆኗን ነበር የምናወቀው” ሲሉም የኤርትራን ሀገር የመሆን ውሳኔ ፈጣን መሆኑን ያብራራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ በፍጥነት የተሠራውን ሸፍጥም “የባሕር በርን የሚዘጋ፣ ባድመን፣ ኢሮብን፣ ጾረናን፣ ከፊል አፋርንና ሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶችን ለኤርትራ አሳልፎ የሚሰጥ ውዝግብ በ285 ቀናት ውስጥ መጠናቀቁ የጊዜ ሰሌዳውን አጠያያቂ ያደርገዋል።
ከኤርትራ ጋር በታሪክም ሆነ በሕግ አግባብ የማትገናኘው አሰብ በስጦታነት የቀረበችው ኢ-ፍትሐዊ በሆነ አግባብ ነው። አሰብ ከኤርትራ ይልቅ ለኢትዮጵያ የሚቀርባት መሆኑን ገልጸው ፤ እንዲሁ ከመጠቀምም አኳያ ከኤርትራ ይልቅ ለኢትዮጵያ የተሻለ እንደነበር አንስተዋል፡፡
‹‹አሰብ የኤርትራ ግዛት፣ የኤርትራ አካል አልነበረም። ወደ ኢትዮጵያ መቅረት ነበረበት። ግን ጠያቂ አልነበረም›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡
“አሰብና ቀይ ባህር የኢትዮጵያ አንድ አካል መሆናቸውን ነው የማውቀው” የሚሉት አቶ በዛብህ ፤ ኢትዮጵያ አሰብን ማጣቷና ቀይ ባህርን መጠቀም ያለመቻሏ በኢኮኖሚዋ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በ60 ኪሎ ሜትር በቅርብ ርቀት ላይ ሆና እንዳትጠቀም መደረጓ ጉዳዩን ይበልጥ ጥያቄ ውስጥ የሚከት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ የባህር በር ባለመኖሩ ለጅቡቲና ሌሎች የወደብ ባለቤት ሀገራት የሚከፈለው ኪራይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያዳክም እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡
ታዲያ ይህ ጉዳይ የፈጠረባቸው ቁጭት ጥልቅ መሆኑን ተናግረው ፤ “በወቅቱ የነበረው መንግስት ስህተቶች እንዲታረሙና ሃሳቦች በነፃነት አደባባይ እንዲወጡ አይፈልግም ነበር” ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
አሁን ላይ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ጥያቄ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ታዲያ እንዴት ሊገኝ ይችላል በሚል ለጠየቅናቸው ጥያቄ ” ኢትዮጵያ ይህን ለማሳካት በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሁም በሠራዊት ግንባታ ራሷን ማጠናከር ይጠበቅባታል” ብለዋል፡፡
ወጣቱ ትውልድ “ሀገሩን ይወቅ” ያሉት አቶ በዛብህ ፤ ስለ ሀገር ማንበብና የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ታሪክ ሰርቶ ማለፍ አለበት” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዘጋጅ፡ ዳንኤል መኩሪያ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ብሄራዊ ቴያትር ከክልሉ 12 ዞኖች ለተውጣጡ ባለ ተሰጥኦዎች ምልመላ በአርባምንጭ ከተማ አካሄደ
በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚከናወኑ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ
በመኸር እርሻ የተዘሩ ሰብሎችን ከአረምና ተባይ የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ