“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/
የዛሬው የንጋት እንግዳችን አቶ ታደሰ ገብሬ ወይም በቅጽል ስሙ ጃክሰን ይባላል፡፡ ዳንሰኛ፣ ኬሮግራፈር /የዳንስ አቀናባሪ/ እና አሠልጣኝ እንዲሁም በሀገራችን የመጀመሪያው የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውና የአካል ጉዳተኞች ዳንስ ማሰልጠኛ መስራችና አሠልጣኝ ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገን ተከታዩን ጥንቅር አቅርበንላችኋል፡፡ በስፋት የሚታወቀው ጃክሰን በሚለው ስሙ ሲሆን እኛም አስፈቅደን እሱኑ ለመጠቀም መርጠናል፤ መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፦ በመጀመሪያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ጃክሰን፦ እኔም ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፦ ከትውልድና እድገትህ እንጀምር…?
ጃክሰን፦ እድገቴ በህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ነው፡፡
ንጋት፦ ወደ ዳንስ እንዴትና መቼ ነው የገባኸው?
ጃክሰን፦ ከልጅነቴ ጀምሮ ዳንስ እወድ ነበር፡፡ ጎበዝ ዳንሰኛም ነበርኩኝ፡፡ ግቢ ውስጥ ዳንስ እሰራ ስለነበር የግቢ ልጆች ያውቁኛል፡፡ ውድድር ሲመጣም የግቢ ልጆች ናቸው ገንዘብ አሰባስበው እንድወዳደር ያበረታቱኝ፡፡ ክፍያው 16 ብር ነበር፡፡ በአስራ ስድስቱ ብር ተመዝግቤ ዳንስ መወዳደር ጀመርኩኝ። ከዚያ ጀምሮ እንዲህ እንዲያ እያለ ነው ወደዚህ የመጣሁት፡፡ የውድድሩ አይነት አስራ ስድስት ነበር፡፡ አስራ አራቱን በአንደኝነት ሳሸንፍ ሁለቱን ግን በሁለተኝነት በማሸነፌ በጣም አልቅሼ ነበር፡፡ በጣም እልህ አለብኝ፡፡ ከዚያ በኋላ አሸንፌ ወደ ግቢ ልጆች ቴፔን ይዤ ስሄድ አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ አልጋ ላይ ሆነው በደስታ ጨፈሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው አካል ጉዳተኞችን ዳንስ የማሰልጠን ሃሳብ በአዕምሮዬ የተጸነሰው፡፡
ንጋት፦ ይህን የዳንስና የውዝዋዜ ስልጠና መስጠት መቼ ጀመርክ? የሚሰለጥኑትስ እነማን ናቸው?
ጃክሰን፦ ወጣቶችን የተለያዩ ዳንስና ውዝዋዜዎችን አሰለጥናለሁ፡፡ እንደዚሁም ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነው የአካል ጉዳተኞች የዳንስ፣ የውዝዋዜና የሰርከስ ቡድኖችን በመፍጠር እና በማሰልጠን ላይ እገኛለሁ፡፡ በሌላ በኩል የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች በማደራጀት እና በማስተማር ህብረተሰቡ ስለ አእምሮ እድገት ውስንነት ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረግ በተጨማሪ የዳንስ እና የውዝዋዜ ስልጠናዎችን እሰጣለሁ፡፡
ንጋት፦ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ጨምሮ አካል ጉዳተኞችን ዳንስና ውዝዋዜ ለማሰልጠን ያነሳሳህ ቅድም እንዳልከው ውድድር አሸንፈህ ስትመለስ ባደረጉልህ አቀባበል ብቻ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት ነበረህ?
ጃክሰን፦ በነገራችን ላይ ኪነ ጥበብ አዝናንቶ ማስተማር ነው ዋናው ግቡ። እኔም ይህን መሳሪያ ተጠቅሜ የአካል ጉዳተኞችን፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን እና መስማት የተሳናቸውን እንዲሁም የአይነ ስውራንን ችግር ለመፍታት ነው የምጥረው፡፡ ምክንያቱም አካል ጉዳተኞች ተንቀሳቅሰው እንደልብ አይሠሩም የሚል ግንዛቤ በህብረተሰቡ ውስጥ አለ፡፡ እኔ ደግሞ ይህን አመለካከት ለመስበር ነው በትጋት እየሰራሁ ያለሁት፡፡
እኔ እንደግለሰብ ነው የምሰራው፡፡ ጥቅሙ ግን እንደ ሀገር ነው፡፡ ሀገር ከእኔ የምትጠብቀውን ነገር አቅሜ በሚፈቅደው ልክ እየሰራሁኝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ፡፡ ያንን ካልሰራ አልኖረም ማለት ነው፡፡ ትልቁ መነሻዬም አካል ጉዳተኞችንና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ወገኖች ህብረተሰቡ ሲያገላቸው አያለሁ፡፡ ለልመና እጃቸውን የሚዘረጉ እንጂ አዕምሯቸውን ለሥራና ለልማት ይጠቀሙበታል ብሎ አለማመኑ ሁልጊዜ ያበሳጨኛል፡፡ እሱን ለመስበር ነው ከዛሬ አስራ ስምንት አመት በፊት ጀምሮ እየተጋሁ ያለሁት፡፡
ንጋት፦ በእናንተ ዘርፍ ያሉ ብዙ ባለሞዎች ስለ ጃክሰን ሲጠየቁ እርሱ ለዳንስ ነው የተፈጠረው ይላሉ፡፡ እውነት ነው? አንተ በዚህ ትስማማለህ?
ጃክሰን፦ መክሊቴ ዳንስ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ በከፍተኛ ፍላጎት ነው የምሰራው፡፡ ዳንስን ስሰራ አልሰለችም፤ አንዳንዴ ትፈጠርበታለህ፡፡ ስትፈጠርበት ታዲያ አርተፊሻል ያልሆነ ትክክለኛውን ጥበብ ታይበታለህ፡፡ ከዚህ አንፃር ይመስለኛል የሚሉት፡፡ በእርግጥ ጥሩ ዳንሰኛም ነኝ፡፡
ንጋት፦ ወደዚህ ሞያ መግባት የሚፈልጉ ወጣቶች ወደውት እንዲገቡ ምን ትመክራለህ? ሞያው ምን ይፈልጋል? አንተስ እንዴት ሞያህን አሳደግክ? ከልምድህ ተነስተህ ንገረን?
ጃክሰን፡- ወደ አንድ ሞያ ስትገባ ራስህን ለሞያው ማስገዛት አለብህ፡፡ አንተ አይደለህም ሞያውን የምትገዛው፤ ይልቁንም አንተ ለሞያው ተገዢ መሆን አለብህ፡፡ ሞያው አንተን ሊገዛህ ይገባል፡፡ ማለትም የሞያውን ስነ ምግባር አክብረህ ሞያው የሚፈልገውን ነገር ጠብቀህ መስራት አለብህ፡፡ ጥሩ ባለሞያ ለመሆን ስትፈልግ እዚህ ድረስ መገዛት ይኖርብሀል፡፡
ከተለያዩ ሱሶች ነፃ መሆን ይጠበቅብሀል፡፡ እኔ በታሪኬ ጠጥቼ፣ ጫት ቅሜ፣ ሲጋራ አጭሼ አላውቅም። ምክንያቱም ሞያውም አይፈቅድም። ለጤናም አስፈላጊ አይደለም፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ቀዳሚው ፍላጎት ሲሆን ቀጣዩ ግን ሞያዊ ስነ ምግባር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ራስን ማብቃትና ወደ ህዝብ ለመውጣት ራስን መሸጥ ነው፡፡
ከዚያ ባለፈ ዋናው ነገር ምንድን ነው ልሰራ የምችለው? በሞያዬ ራሴን ማስጠራት የምችለው እንዴት ነው? የሚለውን አስቦ መውጣትና ለህዝብ በሞያዬ ይህን አበረክታለሁ የሚለውን ዓላማ መያዝ ተገቢ ይሆናል፡፡
ንጋት፦ አንተ የምትሰራው ዳንስና ውዝዋዜ ዘመናዊ ነው ወይስ ባህላዊ?
ጃክሰን፦ እኔ ሁለቱንም ነው የምሰራው፡፡ አፍሪካን ብሬክ ዳንስ፣ ኮንቴምፖራሪ፣ ሂፕ-ሃፕ እንደዚሁም ፍሪ ዳንስን እሰራለሁ፡፡ በተጨማሪም ባህላዊ እና ዘመናዊ ውዝዋዜዎችንም ነው የምሰራው፡፡ የብሔር ብሄረሰቦችንም እሰራለሁ፡፡ የመድረክ ቲያትርም አንዴ ማዘጋጃ ሰርቻለሁ፡፡ እናም ሁለገብ ሰው ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡
እኔ ስሰራ የሚገርመው ክፍያ አስቤ ሰርቼ አላውቅም፡፡ ሆኖም ግን በሞያው ጥሩ በመስራቴ እግዚአብሔር ይመስገን ጥሩ ደረጃ ላይ ነኝ፡፡ የፈጠራ ሥራዎችንም በማከል ስለምሰራ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአይነ ስውራን ዳንስ ስሰጥ ለእነርሱ የሚስማማውን ፈጠራ ጨምሬበት ነው የማሰራቸው፡፡ በዚህም ውጤታማ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡
ከተለያዩ የዳንስ ኩባንያዎች የዳንስ ኮርስ ወስጃለሁ፡፡ በኮንቴምፖራሪ ዳንስም ልምዶችን ቀስሜያለሁ፡፡ እንዲሁም በሀገራችን በዳንስ የብቃት ማረጋገጫ /ሲኦሲ/ ሁለት ያለኝ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ሲኦሲ ተፈትነው አንድ ያላቸው ወደ አራት የሚጠጉ ሰዎች አሉ፡፡ እናም ዳንሱን ከማሳደግ አንፃር ትልቅ ነገር ሰርቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለመጪዎቹና አሁንም ሞያው ውስጥ ላሉት ወገኖቼ ጥሩ መንገድ ከፍቻለሁ ማለት እችላለሁ፡፡
ንጋት፦ አሰልጥነህ ስላበቃሀቸው አካል ጉዳተኞች የዳንስ ቡድን ልጆችህ ጥቂት በለን?
ጃክሰን፦ የሀዋሳዎቹ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ቡድን “ፍቅር ኢትዮጵያ” ይባላል፡፡ የዛሬ 18 አመት አካባቢ ነው የተመሰረተው፡፡ ከዚህም ሌላ ጃክሰን ሀገርኛ የሚባል የዳንስ ማሰልጠኛ ተቋምም አለ፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ ልጆች የተሰጣቸውን ሥልጠና በአግባቡ ስለሚከታተሉ ውጤታማ እየሆኑ ነው። በቀጣይም ብቃታቸውን በማሳደግ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆኑ እየሰራን ነው።
ንጋት፦ ሀዋሳ ላይ በአጭር ጊዜ አሰልጥነህ ያበቃሃቸውን የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውና አይነ ስውራን ያቀረቡት የመድረክ ላይ ውዝዋዜ በጣም ድንቅ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ እንዴት እንዲህ ያማረ ሥራ አሳካህ?
ጃክሰን፦ እውነት ለመናገር ሥልጠናውን ስሰጣቸው ተግዳሮቶች ነበሩት፡፡ ነገር ግን ቴክኒኩን ስለማውቃቸው የእነርሱን ባህርይ እና ስሜት ስለማውቀው ነው በፍጥነት ማብቃት የቻልኩት፡፡ እንዳያችሁት አንድ የሲዳማ አንድ የሰቆጣ ነው የሰሩት፡፡ በጣም ድንቅ ነበር፡፡ አይነ-ስውራንም ህብረ-ዝማሬውን በእንቅስቃሴ አጅበው እንዲያቀርቡ ማድረግም በራሱ ከባድ ነው፡፡
ከስሜት፣ ከቦታ አያያዝና አጠቃቀም እንደዚሁም መድረክ ከማለማመድ አንፃር ከባድ ነው፡፡ ግን ተወጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ልጆቹ ራሳቸው ፍቅር ናቸው። ፍላጎታቸውን ስትመለከት በስሜት እንድትሰራና ለእነርሱ እንድትኖር ያደርጉሃል፡፡
ወደፊት ደግሞ እንዲህ እንዲህ እያልን እንቀጥላለን፡፡ ትልቁ የወደፊት ሀሳቤም በየክልሉ በመዞር እነዚህን አካል ጉዳተኞች ኪነ-ጥበባዊ ፍቅርና ስሜት በማምጣትና በማሰልጠን ወደ ቴሌቪዥን ፎርማት ለመቀየርና ውድድር ለመፍጠርነው፡፡ ይህ ማለት በቲያትሩም፣ በድምጽም፣ በውዝዋዜም እንደገና ደግሞ በእደ-ጥበብ በደቂቃ ማወዳደር እና የተሻለ ሽልማት አግኝተው የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ ማድረግ ነው እቅዴ፡፡
ንጋት፦ እንግዳችን ሆነህ ልምድህንና ሃሳብህን ስላጋራኸን በድጋሚ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ጃክሰን፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ቀልጣፋ የመንገድና ትራንስፖርት አገልግሎት በለለበት ልማትን ማሳለጥ የሚቻል ባለመሆኑ፣ የገጠር መንገድ