በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ጉልህ ድርሻ እንዳለው የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የወልቂጤ ከተማ አስተደደር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ትምህርት ፅህፈት ቤቶች በጋራ “ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሁለንተናዊ የአገር ግንባታ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራ ውድድር ኤግዝቢሽን በሰላም በር ትምህርት ቤት አካሂደዋል ።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በውድድሩ ወቅት እንደተናገሩት ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት የሀገሪቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ በሳይንስና ኢንፎርሜሽን ስራዎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል ።

በመስኩ በየደረጃው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚሰሩ ስራዎች ከፍተኛ አበርክቶ ስላላቸው የራሱን የገቢ አቅም በማሳደግ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠር እንዲቻል ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።

በዞኑ የተመዘገበውን የተሻለ የፈጠራ ተግባር እንዲቀጥል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሀምዱ ካሚል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ግንባታ በሚል መሪ ቃል የተከናወነው የኤግዚቢሽን ተግባር ተማሪዎች የርስበርስ ውድድር የሚያደርጉበት ዕውቅና የሚያገኙበትና ልምድ በመቅሰም የተሻለ ትውልድ እንዲፈጠር ትልቅ እገዛ የሚያበረክት ነው ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ስሜነሽ ግርማ በበኩላቸው በኤግዚብሽኑ በፈጠራ ስራው ውጤታማ ተማሪዎች ኢንተር ፕራይዞች እና የግል ተወዳዳሪዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰው በዚህም የገቢ አቅሙን ማሳደግ የሚችል ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ አስተወጽኦ እንዳለው ተናግረዋል ።

ለስራው ውጤታማነት መምህራኖች እንዲሁም ሌሎ ች ባለድርሻ አካላት ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይም መሰል ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል ወይዘሮ ስሜነሽ ።

በዕለቱ በነበረው የፈጠራ ስራዎች ኤግዚቢሽን ውድድር ላይ ያነጋገርናቸው የፈጠራ ስራ ባለቤቶች በሰጡት አስተያየት የዚህ አይነት ኤግዚቢሽን መኖሩ ለፈጠራ ስራቸው ትልቅ እገዛ እንዳለው ጠቁመዋል ።

ዘጋቢ፡ ከፉአድ አብደላ – ከወልቂጤ ጣቢያችን