በፈረኦን ደበበ
ክፍል-2
ውድ አንባቢያን ዓመታት የጊዜ ቀመር ናቸው፡፡ ሰዎችን ጨምሮ የሁሉም ነገሮች ዕድሜን ይወስናሉ፡፡
ወደ ኋላ መታጠፍ የሚባል ነገር ሳይሰማቸው ሁል ጊዜ ወደ ፊት የሚገሰግሱት የጊዜ ቀመሮቹ ከሰዎች ጋርም የጠበቀ ቁርኝት አላቸው፡፡ እስከ መቼ እኖር? ምን አገኝ? ምን አጣ? የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሳን ከጊዜ ጋር ኑሮን ለማሻሻል እንተጋለን፡፡
ይህ የህይወት ጉዳይ እንደመሆኑም በእርግጥ ብዙዎች ብዙ እንዲያስቡበት አድርጓቸዋል፡፡ ኃይማኖትን ጨምሮ የተለያዩ የፍልስፍና ዘውጎችን እንዲከተሉም አነሳስቷቸዋል፡፡ ዕቅድ ከማውጣት ባለፈ የህይወት ዜይቤያቸውን በተለያዩ ምትሀታዊ ተግባራት እንዲመለከቱም አስገድዷቿል፡፡
ባለፈው ዕትማችን ድርጊቱ መፈጸሙን በተለያዩ ሀገራት የሚከናወኑ ተግባራትን ሁሉ እያነሳን ለማብራራት ሞክረናል፡፡ በሀገራችን ካለው የበዓል አከባበር ጋር እያነጻጸርን ”አፋር“ በተባለው ድረ-ገጽ የተዘረዘረውን አቅርበን ነበር፡፡
በአፍሪካም ሆነ በዓለም ዙሪያ ሰዎች ህይወታቸውን ለማሻሻል ከዕድል ይልቅ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ምርጫ እያደረጉ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ አስተሳሰቡ ተመልሶ መምጣቱ ቢያስገርምም መቼስ ልማድን አንድ ጊዜ ማስወገድ አይቻልምና ቀጣዩን ክፍል በሚቀጥለው መልክ እንመልከተው።
በጀርመን ያለው ልማድ አስገራሚ ነው። እርሳስን በእሳት ማቃጠልና ማሟት ዕድልን ያስገኛል ብለው የሚያከናውኑት ተግባር ሲሆን ድርጊቱ ሌሎች ጀርመንኛ ቋንቋ በሚናገሩ ሀገራትና እንደ ፊንላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ ቼክ ሪፑብሊክና ቱርኪዬ ባሉ ሀገራትም ይፈጸማል፡፡
የቀለጠውን እርሳስ በቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ በማድረግ የሚፈጥረውን ቅርጽ ማየትና ቀጣይ ሊገጥማቸው የሚችለውን ዕድል የሚጠብቁት በዓል አክባሪዎቹ ድቡልቡልና ኳስ ቅርጽ የሚመስል ነገር ከፈጠረ ዕድለኛ እንደሚሆኑ ያስባሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከእርሳስ ውጪ መለስተኛ የዕቃ መያዣ ነገሮችን በማቃጠልም ነው ዕድላቸውን እየገመቱ የሚገኙት፡፡
በሩሲያ የሚከወነው ተግባርም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል፤ ምክንያቱም በአዲስ ዓመቱ ዋዜማ ዕኩለ ሌሊት ላይ ምንም ዓይነት ድምጽ በሌለበት ሁኔታ ለ12 ሰኮንዶች በዝምታ መዋጥ ዕድልን ያስገኛል ብለው ስለሚያስቡ፡፡
ያለፈው ዓመት ትውስታ ለመግለጽ ሲፈልጉም ዕኩለ ሌሊት ከመድረሱ በፊት ባለፈው ዓመት የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮችን እያስታወሱ ምስጋና የሚያቀርቡት በዓል አክባሪዎቹ የመልካም ምኞት መግለጫም ያስተላልፋሉ፡፡
በድረ-ገጹ በተጠቀሰችው ስፔንም ብዙ አፍንጫ ያለው ሰው ፍለጋ የሚባለው አስተሳሰብ ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ አዲሱ ዓመት ሊገባ ሲል ከሚቀሩት ጥቂት ቀናት ጋር የሚነጻጸረው ይህ ዕሳቤ መልካም ምኞትን ለማስተላለፍ እንሚረዳም ነው የተጠቆመው፡፡
ሌላኛዋ የምዕራብ አውሮፓ ሀገር በሆነችው ዴንማርክ ደግሞ የአዲስ ዓመት ዕድልን ማግኛ ዋነኛው ተግባር በዝላይ መሻገር ነው፡፡ ከወንበርም ሆነ ሶፋ ሳይቀር የሚደረገው ዝላይ መልካም ዕድልን ለማግኘት አንዱ ዘዴ ሲሆን ይህን ያለማድረግ በበኩሉ ውድቀት ያመጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡
በአሁኑ ማህበረሰብ ውስጥ በተጨባጭ እነዚህ ተግባራት ይከወኑ አይከወኑ ማረጋገጫ ባልሰጠበት ሁነታ ድረገ-ገጹ አተገባበሮችን ዘርዝሯል፤ ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ከመደበኛ የአዲስ ዓመት ማስታወሻዎች ጋር ሁሉ ቢገናኙም። የአከባበር ይዘቶቹ ዘመኑን ያልዋጁ ከመሆናቸው አንጻር ለማስቆም የተደረገ ጥረት መኖሩንም እንዲሁ የመረጃ ምንጫችን አልገለጸም፡፡
በሞት ከቤተሰባቸው የተለዩ አባላትን ለማስታወስ ሲባል በአይርላንድ የሚደረገው ተግባር በሀገራችን ካለው ሥርዓት ጋርም ይመሳሰላል፡፡ ይህም ምግብ በሚበሉበት ማዕድ ላይ ለተለየው አባል ማስታወሻ ተብሎ የሚያስቀምጡትን ሣህን ሲያመለክት አዲሱን ዓመት የሚያሳብቁ ሌሎች ተግባራትንም ያካትታል፡፡
ከእነዚህ መካከል በብዙዎች ዘንድ የተለመደው ቤት ማጽዳት አንዱ ሲሆን ይህ ክፉ መናፍስት ለማባረርና አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ጽዱ በሆነው ቤት ለማክበር እንደሚጠቅምም ተገልጿል፡፡ የቤቱ ውጭ ግድግዳዎች ጭምር በዳቦ መቀባትን የሚያካትተው ይህ ሥነ-ሥርዓት በሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ ቅርጽ አለው፡፡
በጣሊያንና ስፔይን የሚለበሰው ቀይ የውስጥ ልብስም እንዲሁ በረከትን ለማግኘት ጠቃሚ ነው ተብሎ ታስቧል፡፡ ይህ ደግሞ ከልብሱ ሁኔታ ጋርም ተገናኝቷል፤ ምክንያቱም እንደ ስፓኒሾች ዕድልን ለማግኘት የሚደረገው ልብስ አዲስ መሆን አለበት ተብሎ ስለሚታመን፡፡
በተመሳሳይ ጣሊያኖችም አሮጌ ነገሮችን በመስኮት በኩል ወደ ውጭ ይወረውራሉ አዲሱን ዓመት የሚያሳብቁ አዲስ ነገሮች አይደሉም በሚል፡፡ ለአዲስ ዓመት ይህ ያህል ትኩረት መስጠታቸው ዕድሉ በዕቅድና ሥራ ሳይሆን በአስተሳሰብ ዘይቤ እንደሚመጣ ስለሚያስቡት ነው፡፡ ይህ ግርምቱንም ከፍ ያደርጋል፡፡
በጃፓኖች ዘንድ ያለው እምነት ከዚህ የሚለይና በሀገራችን ከሚተገበረው ጋር መመሳሰሉ አድናቆትን ይፈጥራል፡፡ ደስታን ለማግኘት ሲባል ሰዎች ወደ ቤተ-መቅደስ መሄድን የሚያካትተው ይህ ተግባር በየዓመቱ ይከበራል፡፡ ያለፈው ዓመት ትውስታዎችም ወደ አዲሱ ዓመት እንዲገቡ ይረዳል በሚል፡፡
ቀጥሎም ህዝቡ እንደ ዓሣ ያሉ ምግቦችን መብላት የሚጀምር ሲሆን ይህም ዕድሜ ለመጨመርና እናቶች ብዙ ልጅ መውለድ እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡
ውድ አንባቢያን፡ አዲስ ዓመት ማለት የሰዎች ተስፋ ብርሃን ነው፡፡ ብዙዎችንም መንፈሳዊ እርካታን ያጎናጽፋል፡፡ ያጋጠማቸው እክሎችና ጭንቀቶችን ሁሉ እርግፍ አድርገው ብሩህ ተስፋ እንዲሰንቁም ያነሳሳል፡፡
ሆኖም ይህ የሚሳካው ተጨባጭ ዕቅዶችን በማውጣት ወይስ በምኞት እንደሆነ አሁን ላለንበት ማህበረሰብ የሚጠፋው አይደለም፡፡ ብዙዎች ከትንሽ እስከ ትልቅ የሚደርሱ ዕቅዶችን ያወጣሉ። በዚህ መልክ ደፋ ቀና በማለት እራሳቸውንና አካባቢያቸውንም ይለውጣሉ፡፡
ከዚህ ውጭ በአጋጣሚ ካልሆነ በቀር ስኬትን ማግኘት የሚቻል አይደለም፡፡ ከላይ የዘረዘርናቸው በተለያዩ ሀገራት ያሉ ልማዶችም እንዲሁ ለምኞት ያህል ካልሆነ በቀር ተጨባጭ ለውጥ ስለማምጣታቸው ያጠራጥራል፡፡
ለምሳሌ አንድ ሰው እንደ ዴንማርኮች ከሶፋ ላይ ተወርውሮ መውረድ፣ እንደ ጀርመኖች ብረት ቢያቀልጥም ሆነ እንደ ሩሲያኖች ዕኩለ ሌሊት ላይ በዝምታ መዋጥ እንዴት ዕድለኛ እንደሚያደርገው ምንም ተጨባጭ ማሳያ የለም፡፡ ይልቁንም ወደፊት በአስተሳሰቡ ላይ ሰፊ ጥናት እንዲደረ እንዲደረግ የሚያነሳሳ ነው፡፡
More Stories
“ትልቅ ዓላማ ይዞ መነሳት ከሁሉም ይበልጣል” – ወጣት ነፃነት ምትኩ
“የሳሙና ተብሎ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር” – አቶ ደረጀ ሞገስ
“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ