በአብርሃም ማጋ
የዛሬ የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን ወጣት መሰለ መንግስቱ ይባላል፡፡ አካል ጉዳተኛ መገለልና መድልዎ ካልተደረገበትና አስፈላጊውን ድጋፍ ካገኘ ተምሮ ከራሱም አልፎ ለሀገሪቷ እድገት ላቅ ያለ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ወጣቱ ፅኑ እምነት አለው፡፡
ለዚህም በሀገሪቷም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚና በተለያዩ እውቀት በሚሹ ዘርፎች ሁሉ ተሳታፊ መሆናቸው ጥሩ አስረጂ ነው ይላል፡፡
በዚህ መነሻም አካል ጉዳተኛ እንደማንኛውም ሰው መማር፣ መመራመር፣ መነገድ፣ ትዳር ይዞ ልጅ መውለድና ማሳደግ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት ሥራ ከመሥራት የሚያግደው ነገር አለመኖሩንም አክሎ ይናገራል፡፡
እሱም ቢሆን በህፃንነቱ ያልታሰበ አደጋ ደርሶበት በጉልበቱ እየዳኸ ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ፣ ተምሮ፣ በዲግሪ ተመርቆ እንደማንኛውም ሰው በመንግስት ሥራ ተቀጥሮ ለመሥራት መብቃቱ ለመሰሎቹና ለሌሎቹም አርዓያ ሊሆን እንደሚችል ይናገራል፡፡
ወጣት መሰለ መንግስቱ በአሁኑ አጠራር በወንዶገነት ወረዳ፣ በኤዶ ቀበሌ በ1989 ዓ.ም ተወለደ፡፡ አሁን 28ኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል፡፡
ወጣቱ ገና የአንድ ዓመት ህፃን ሳለ የዘመድ ለቅሶ ተፈጥሮ ወላጆቹ ራቅ ወዳለ አካባቢ ይዘውት ይሄዳሉ፡፡
እንደሄዱም የቀብር ሰዓት ሲደርስ እናቱ በአንድ ዘመድ ቤት ውስጥ ከልጆች ጋር አስቀምጠውት ለቀብር ይወጣሉ፡፡
ከቀብር ቦታ ሲመለሱ ልጃቸውን እንደነበረ አላገኙትም፡፡ መላ ሰውነቱ ተይዟል፡፡ እግሮቹ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆነዋል፡፡ ምን እንደነካው ባለማወቃቸው ሲጮሁ የተሰበሰበው ለቀስተኛ ሁሉ መፍትሔ ሊያገኝለት አልቻለም፡፡
በዚሁም ተደናግጠው ለቅሶውን ትተው ወደ ቤት ቢያመጡትም ጤንነቱ ላይ የተሻለ ነገር አልተገኘም፡፡ ለተወሰኑ ወራት በባህላዊ ወጌሻ እየተሞከረ ቢቆይም ምንም ጠብ የሚል ነገር ጠፋ፡፡
ግራ ቢገባቸው አባቱ ከቤቱ ታላቅ ልጅ በመሆኑ በጣም ስለሚወዱት ወደ ዘመናዊ የህክምና ማዕከላት መውሰዱን እንደ አማራጭ ወሰዱት፡፡
ከዚያም በኦሮሚያ ክልል ጅጌሣ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥር ለአካል ጉዳተኞች የሚደረግ ህክምና ማዕከል አደረሱት፡፡
ቢሆንም ከጉልበቱ በታች ባሉት እግሮቹ ላይ የደረሰውን የልጅነት ልምሻ ለማዳንም ሆነ ለውጥ ለማምጣት አልተቻለም፡፡ በዚህም አባቱ የልጃቸው ሁኔታ ተስፋ አስቆርጧቸው በከፍተኛ ሃዘን ውስጥ ገቡ፡፡
በወቅቱ ልጃቸውን ለሚሲዮኖች /ለነጮች/ ሰጥተው እንዲመጡ ብዙዎች ቢገፋፏቸውም በህይወት እያለሁኝ ልጄ ከእኔ አይለይም ብለው ይዘውት ወደ ሀገር ቤት ገቡ፡፡
እሱም እንደመጣ በጉልበቱ እየሄደ ከግቢው ውጭ ሳይወጣ ይንቀሳቀስ ጀመር፡፡ ወደ ውጭ የማይወጣበትም ምክንያት ሰው እንዳያየው ተብሎ ነበር፡፡
ከእለታት አንድ ቀን አንድ ዘመድ ራቅ ካለ አካባቢ መጥቶ ልጁን ቡሽሎ ሎቄ በሚገኘው በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥር በሚገኘው ከፍተኛ ክሊኒክ እንዲወስዱት ጥቆማ ሰጠ፡፡
በዚሁም አባቱ ወደ ክሊኒኩ/ማዕከሉ/ ወሰዱት፡፡ ማዕከሉ ለተወሰኑ ቀናት ካቆየው በኋላ ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልገው ገልፆ የቤተሰቦቹን ፈቃደኝነት ጠየቀ፡፡
ቢሆንም አባቱ ከግንዛቤ እጥረት ልጄ የባሰ ይበላሽብኛል ብለው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ፡፡ ልጅ መሰለም በወቅቱ ከፍተኛ ፍራቻ ይዞት ስለነበር ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
ከዚያም ወደ ቤት አመጡትና ተቀመጠ፡፡ በሌላ ጊዜም እንዲሁ ቦታውን ባያስታውሰውም ከአዲስ አበባ ከተማ አልፎ ወዳለና አካል ጉዳተኞች ወደሚታከሙበት ህክምና ማዕከል ተወስዶም የተሻለ ሕክምና ሳያገኝ ተመልሷል፡፡
እንዲህ እያለ እድሜው ወደ ሰባት ዓመት ደረሰ፡፡ እቤት ተቀምጦ በጉልበቱ እየዳኸ፣ አንዳንዴ ደግሞ ከግቢ ውጭ እየወጣ ይመለስ ጀመር፡፡ ውጭ ሲሆንም መንገደኞች ሲመጡበት አፍሮ መዳሁን ትቶ እንደ አካለ ሙሉ ልጅ ቁጭ ብሎ ያሳልፋቸዋል፡፡ ሌሎች እንዳይመጡበትም ቶሎ ብሎ ወደ ግቢው ውስጥ ይሸሻል፡፡
ከዚያም ከፍተኛ የሞራል ውድቀት ውስጥ ገብቶ ከግቢው መውጣቱን ቀነሰ፡፡ አባቱ ትምህርት ቤት እንዲገባ ቢፈልጉም “ምን ብዬ እልከዋለሁ” ብለው፤ እሱም ቢሆን ሙሉ አካል ካላቸው ልጆች ጋር ተቀላቅዬ እንዴት እማራለሁ በሚል ፍራቻ ትምህርት ቤት ሳይገባ አንድ ዓመት ያሳልፋል፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳለ ሴት አያቱ ማለትም የአባቱ እናት የአንተ መድሃኒቱ ትምህርት ነውና ምንም ነገር ሳትፈራ ትምህርት ቤት ግባ አሉት፡፡ “ትምህርት ከተማርክ ከማንም በታች ሳትሆን እኩል ሆነህ ትኖራለህና፡፡ እኔ በህይወት እያለሁ ግባ” ብለው መክረውት ድፍረት እንዲያገኝ አደረጉት፡፡ አባቱም በአያቱ ሃሳብ ተስማምተው አሳምነውት እንዲማር አደረጉት፡፡
በወቅቱ ኤዶ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ከቤታቸው በራፍ ላይ ስለሚገኝ ደብተርና እስክሪብቶ ተገዝቶለት መማሩን ጀመረ፡፡
በጉልበቱ እየሄደ ስለሚሄድ መማሪያ ደብተሮቹን መያዝ ስለማይችል ልጆች ነበሩ ደብተሮቹን ይይዙለት የነበረው፡፡
ትምህርት ቤት እንደገባ ጐበዝ ተማሪ ስለነበር ከ1ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ድረስ ተምሮ በጥሩ ውጤት አጠናቀቀ፡፡ ትምህርት ቤቱ ቀጣይ ክፍሎች ስላልነበሩት ከ6ኛ ክፍል በላይ መማሩ ፈተና ሆነበት፡፡
ቢሆንም ከፍተኛ የትምህርት ፍቅር ስለነበረው ከቤተሰቦቹ ጋር ተማክሮ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄዶ ለመማር ወሰነ፡፡ በዚሁም ቡሳ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄዶ እንዲማር ተደረገ፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታው ከተማሪዎቹና ከመምህራኑ ጋር ተላምዶ ቀደም ሲል የነበረውን ፍርሀት አስወግዶ በማህበራዊ ህይወቱም ጥሩ መንፈስ መላበስ ቻለ፡፡
በቡሳ ትምህርት ቤት ሲማር ቤተሰቦቹ የፈረስ ጋሪ ገዝተውለት ስለነበር በእሱ እየተመላለሰ ይማር ጀመር፡፡ በተጨማሪም ጋሪው እሱ በሚማርበት ወቅት ሰው ተቀጥሮ እየሰራ ገንዘብ ያመጣለትም ነበር፡፡
የሚገርመው ነገር ትምህርቱን በሚማርበት ወቅት አባቱ ከሌላ ስፍራ ናፍጣ/ጋዝ/ እያመጡለት በችርቻሮ እየሸጠ ገንዘብ ያጠራቅም ነበር፡፡ ብዙ ዶሮዎችንም ገዝቶ በማርባት እንዲሁ ገቢውን ሲያሳድግ ቆየ፡፡ የፈረስ ጋሪው ሲገዛም ግማሽ ገንዘቡ የተሸፈነው ከራሱ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ የጋሪውንም ቁጥር ጨምሮ ሁለት አደረገ፡፡
ትምህርት ቤት ተመላልሶ በሚማርበት ጊዜ ቀልጣፋና ተግባቢ ስለነበር በብዙዎቹ ዘንድ ታዋቂነትን አትርፏል፡፡ ብዙ የሚኒባስ ሾፌሮችም ስለሚያውቁትና ስለሚወዱት በጋሪው መመላለስ ቀርቶ በበራፉ ላይ ቆሞ ያለክፍያ በነፃ እየጫኑት እየተመላለሰ በትምህርት ቤቱ 8ኛ ክፍልን አጠናቀቀ፡፡ ጥሩ ውጤትም አምጥቶ ወደ 9ኛ ክፍል ተዛወረ፡፡
ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ስላልነበረው ወደ ሐዋሣ ከተማ ሄዶ መማሩ ግድ ሆነበት፡፡
በሐዋሣም በአዲስ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ በዚህን ወቅት አባቱ አቶ መንግስቱ ያደረጉለት ነገር ቢኖር በትምህርት ቤቱ አጠገብ ተከራይቶ የሚኖርበትን ቤት መፈለግ ነበር፡፡
በመሆኑም በትምህርት ቤቱ አጠገብ የሚከራይ የዘመድ ቤት አገኙ፡፡ ልጃቸውም ከክፍል ጓደኞቹና ከመምህራኖቹ ጋር ከፍተኛ ተግባቦት ስለነበረው በጥሩ መንፈስ ትምህርቱን ከመከታተል ያገደው ነገር አልነበረም፡፡ ጠዋት ትምህርት ቤት ሲሄድና ሲመለስ የመማሪያ ቁሳቁሶቹን የክፍል ጓደኞቹ ይይዙለታል፡፡
በዚህ ዓይነት ሁኔታ 9ኛ ክፍልን አጠናቅቆ 1ዐኛ ክፍል ሲማር የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ተማሪዎችንና መምህራኑን ሰብስበው ዊልቸር እንዲገዛለት እንደየዓቅማቸው ገንዘብ እንዲያዋጡለት ያስተባብራሉ፡፡ ሁሉም የአቅማቸውን ያህል ቢያዋጡለትም የተሰበሰበው ገንዘብ ለዊልቸር መግዣነት ሳይበቃ ይቀራል፡፡
ቢሆንም ርዕሰ መምህሩ የተዋጣውን ገንዘብ መጠን ነግረውት እንዲወሰድ ይጠይቁታል፡፡ ወጣት መሰለ ግን ገንዘቡን ለሌላ ዓላማ ማዋል እንደሌለበት ስላመነ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ተጨማሪ ገንዘብ እስከሚገኝም ርዕሰ መምህሩ ጋር እንዲቀመጥ ጠይቆ በሃሳቡ ይስማማሉ፡፡
ውሎ ሳያድር አንድ ጥሩ እድል ይገጥመዋል፡፡ ዘመዱ የሆኑ አቶ በላቸው ጂላ የተባሉ ግለሰብ ቸሻየር የተሰኘ ድርጅትን ጠይቀው “ትራይ ሳይክል” የሚባል ባለሶስት ጐማ ብስክሌት አስገኙለት፡፡
ብስክሌቱን ካገኘ በኋላም በትምህርት ቤት በኩል የተዋጣለትንም ገንዘብ አመስግኖ ተቀብሎ የሞዲፊኬሽን ሥራዎችን አሠርቶ መጠቀም ጀመረ፡፡
ይህ ብስክሌት በእጅ የሚነዳ በመሆኑ ያለችግር እየነዳ እንደልቡ እየተንቀሳቀሰ ተምሮ የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትኖ ያጠናቅቃል፡፡ በትምህርቱም ጐበዝ ስለነበር የመሰናዶ ትምህርት ለመማር የሚያበቃውን ውጤት አመጣ፡፡
በውጤቱም የ11ኛ ክፍል የመሰናዶ ትምህርት ቢጀምርም በተመደበበት ትምህርት ቤት ያልተመቸው ነገር በመኖሩ ለማቋረጥ ተገድዶ ኒው ግሎባላይዜሽን በተሰኘ በግል ኮሌጅ የዲፕሎማ ትምህርቱን መማር ጀመረ፡፡
የትምህርት ክፍሉም ኦፕሬቲቭ ኦርጋናይዜሽን እና ቢዝነስ አመራር ሲሆን፣ ይህን ትምህርቱን ተከታትሎ በዲፕሎማ መመረቅ ቻለ፡፡
ትምህርት መማር ስለሚወድ የትምህርቱ ነገር በዲፕሎማ ደረጃ ብቻ አላበቃም፡፡ በመቀጠልም በሻሸመኔ ከተማ ኒው ግሎባል ቪዥን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሳምንታዊ ፕሮግራም በቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርት ዘርፍ ተከታትሎ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡
በዲግሪ ከተመረቀ በኋላም በ2008 ዓ.ም የወንዶ ገነት ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት ተወዳድሮ በማለፍ በጽ/ቤቱ የንብረት ክፍል ሃላፊ ሆኖ ከጥር 1 ጀምሮ ተቀጥሮ እስከ አሁን በሥራው ላይ ይገኛል፡፡
ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ከመንግስት መደበኛው ሥራ ውጭም በግል የግብርና ሥራም ይሠራል፡፡ ከቤተሰቦቹ በውርስ ካገኘው መሬት በተጨማሪም ከግለሰቦቹ የእኩል ወስዶ በበጋ ወራት ድንች፣ ጥቅል ጐመን፣ ቲማቲም የመሳሰሉ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን በመጠቀም ያመርታል፡፡
ተማሪ ሳለ የረዱትን አቶ ጋሜ ጋትሶ እና አቶ ማሙሽ ብርሃኑን ሳያመሰግናቸው አላለፈም፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች የኮሌጅ ትምህርቱን በሚማርበት ወቅት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉለት እንደነበርም ያስታውሳል፡፡
መነሻው የሆኑትን ሴት አያቱን (አሁን በሕይወት የሉም) በሕይወቱ ትልቅ አሻራ እንዳሳረፉ ይናገራል፡፡ “እኔ እዚህ ደረጃ መድረሴን አይተው በማለፋቸው ብዙም ቁጭት አይፈጥርብኝም” ሲልም ያመሰግናቸዋል፡፡
ትምህርቱን በሚማርበት ወቅት ስላጋጠሙት ችግሮች ተጠይቆ ምላሽ ሲሰጥ 8ኛ ክፍል ሲማር በጉልበቱ ላይ የወጣበት እባጭ ሕመሙ ከፍተኛ ሆኖበት ዝናብ ሲዘንብ መዳህ አቅቶት መላ ሰውነቱ ጭቃ በጭቃ ሆኖ መግባቱ ተስፋ አስቆርጦት ትምህርቱን ሁሉ ለማቋረጥ ወስኖ በመምህራኑ ምክር ተምሮ መጨረሱን ያስታውሳል፡፡
ከዚህ ባሻገር አንዳንድ ሆቴሎች አካል ጉዳተኞችን አናስተናግድም ሲሉ መስማቱ እንደሚያስከፋው አልሸሸገም፡፡ አያይዞም በሆቴሎች፣ በት/ቤቶች፣ በካፍቴሪያዎች፣ በሆስፒታሎች…ወዘተ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥኑ መፀዳጃ ቤቶች እና ሊፍቶች አለመኖራቸውም ከባድ ፈተናዎች ናቸው ይላል፡፡
በግሉም አካል ጉዳተኛ ከሰው በታች እንደሆነ ተቆጥሮ ሞራሉን የሚነኩ በደሎች እንደደረሰበትም ያወሳል፡፡ በማህበራዊ ሕይወቱም ከባድ ፈተናዎችን እንደተጋፈጠ ይናገራል፡፡
ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ጀምሮ አብራው የቆየችውን ሴት ጓደኛውን ሲያገባ ቤተሰቦቿ አሻፈረኝ ብለው ለ5 ወራት ያህል አስታራቂ ሽማግሌ አንቀበልም ማለታቸውን ያስታውሳል፡፡
ይህም ድርጊታቸው ስነልቦናውን ቢጎዳውም ባለቤቱ እሱን ለማግባት የወሰደችው ቁርጠኛ አቋም እርቅ ፈጥሮ መጋባታቸውን ይናገራል፡፡
ከመጀመሪያ ባለቤቱ ሁለት ወንድና አንድ ሴት ልጅ ወልዶ የመጀመሪያ ልጃቸው እንደሞተባቸው ይናገራል፡፡ ኋላም ባለቤቱ ሶስተኛ ልጅ ከወለደች በኋላ መሞቷ ከፍተኛ ሃዘን ውስጥ ከትቶት ነበር፡፡
ለ5 ዓመታት ሌላ ትዳር አልይዝም ብሎ ቢቆይም በጓደኞቹ፣ በቤተሰቦቹና በቤተክርስቲያናቸው ሽማግሌዎች ግፊት ሌላ ትዳር ይዞ አንድ ወንድ ልጅ መውለዱንም ጠቅሷል፡፡
ከዚህ ውጭም ወጣቱ ለአካል ጉዳተኞች ባገኘባቸው ሁሉ ራሱን ምሳሌ በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጣል፡፡
ልክ እንደሱ የነበሩትንና በአካል ጉዳተኝነታቸው የተነሳ ቤተሰቦቻቸው ከቤት እንዳይወጡ ያደረጉአቸውን በርካታ ልጆችን በማስተማር መደበኛ ትምህርት ቤት እንዲገቡ አድርጓል፡፡
ከእነዚህ ውስጥም አንድ ልጅ 12ኛ፣ ሌላኛው 1ዐኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ በርካቶቹ በ1ኛ ደረጃና በሁለተኛ መለስተኛ ደረጃ ት/ቤት እንደሚማሩም አብራርቷል፡፡
የዚህ ቆራጥ ወጣት ተሞክሮ በሌሎቹም ዘንድ እንዲለመድ ምኞታችን እንደሆነ እየጠቆምን ዝግጅታችንን በዚህ ቋጨን፡፡ ሰላም፡፡
More Stories
“ትልቅ ዓላማ ይዞ መነሳት ከሁሉም ይበልጣል” – ወጣት ነፃነት ምትኩ
“የሳሙና ተብሎ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር” – አቶ ደረጀ ሞገስ
“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ