‎የጡት ካንሰር የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ቅድመ ምርመራ ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

‎የጡት ካንሰር የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ቅድመ ምርመራ ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

‎የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ነፃ የጡት ካንሰር ህክምና ለአራት ተከታታይ ቀናት እየሰጠ ነው።

‎ጥቅምት ወር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ40ኛ ጊዜ በሀገራችን ደረጃ ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር በዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያ ሆስፒታል እየተከበረ ይገኛል።

‎በወርሃ ጥቅምት በዓለም አቀፍ ደረጃ የጡት ካንሰር እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ለህብረተሰቡ የበሽታውን አስከፊነትና ቅድመ ጥንቃቄ ግንዛቤ በማስጨበጥ ነፃ የምርመራና ህክምና አገልግሎት በመስጠት በየዓመቱ በጥቅምት ወር እንደሚከበር የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

‎በማስተማሪያ ሆስፒታሉ ለህክምና አገልግሎት ለመጡት ታካሚዎችና በስፍራው የተገኙትን በመሰብሰብና በዲላ በሚገኘው በማሞ ኮሞልቻ አደባባይ ስለበሽታው አስከፊነት ህብረተሰቡ ተረድቶ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ትምህርት እየተሰጠ ነው ሲሉም አቶ ትዝአለኝ አብራርተዋል፡፡

‎የጡት ካንሰር ህመም ሰውነት ላይ ምልክት ሳያሳይ ለከፍተኛ ጤና ጉዳት የሚዳርግ ነው ያሉት የምክርና ህክምና አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው በሆስፒታሉ የጠቅላላ ቀዶ ህክምና ሐኪም ዶክተር ኮከብ አያለሁ፤ የጡት ካንሰር የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ቅድመ ምርመራ ላይ በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

‎በሀገሪቱ ደረጃም በጡት ካንሰር ህመም የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩት ዶክተር ኮከብ፤ በተለይም እናቶች በየወቅቱ አስፈላጊውን ምርመራ አድርገው እራሳቸውን በማወቅ ከበሽታው እንዲጠነቀቁና የጤና ባለሙያዎችን ምክረ ሀሳብ ለመተግበር የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

‎በዲላ ከተማ በማሞ ኮሞልቻ አደባባይ አገልግሎቱን ሲያገኙ ያነጋገርናቸው ወ/ሮ እታበዝ ማሩ ከባለሙያዎች ባገኙት ትምህርት በመረዳት ተመርምረው እራሳቸውን በማወቃቸው ልባዊ ደስታ እንደተሰማቸው አብራርተዋል፡፡

‎በርካታ እናቶች ተመርምረው እራሳቸውን ባለማወቃቸው ለተለያዩ ጉዳት ሲዳረጉ እንደነበር የገለጹት ወ/ሮ እታበዝ፤ ሁሉም እናቶች ይህን ዕድል በመጠቀም ህክምናውን እንዲያገኙ መክረዋል።

‎ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን