የልማት ሥራዎችን ለማሣካት የሚመደብ በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ ተመላከተ

የልማት ሥራዎችን ለማሣካት የሚመደብ በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ ተመላከተ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 27/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የልማት ሥራዎችን ለማሣካት የሚመደብ በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ገለጸ፡፡

ቢሮው ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመሆን በታርጫ ከተማ ከዳዉሮና ኮንታ ዞኖች ለተወጣጡ ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት በአየር ንብረት ለውጥ፣ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ከአለም ባንክና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለያዩ የድህነት ቅነሣ ፕሮግራሞች ላይ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማሣካት እየሠራ ነው።

ባለፈው ዓመት በተፋሰስ፣ የመሬት አያያዝና አስተዳደር እንዲሁም በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ላይ ጭማሪ እንዲኖር ለማስቻል ከ310 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ እየተሠራ እንዳለም መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህ በጀት በተለይም በየደረጃው የሚገኙ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ፣ የፈጻሚን አቅም ለማሣደግና ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ረገድ የድርሻውን እንዲወጣ እየተሠራ እንዳለ በክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ዓለሙ ተናግረዋል።

በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የሚመደበው በጀት የፋይናንስ ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን በመፍጠር ረገድ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ የቻናል አንድ ፕሮግራምና ፕሮጄክቶች አስተባባሪ አቶ ጌታሁን ታደሰ በበኩላቸው በፋይናንስና ግብርና ቢሮ በጋራ የሚያከናውኗቸውን የልማት ሥራዎች ውጤታማነታቸውን በተገቢው በመገምገም ለዜጎች የጋራ ተጠቃሚነት እየሠራ ይገኛልም ብለዋል።

የዘርፉ አመራሮችም ሀብት በተገቢው መመደቡን በማረጋገጥ፣ በሪፖርት አላላክ ላይ የሚታየውን ችግር በመቅረፍ ሪፖርቱ ወቅታዊና ተኣማኒ እንዲሆን የድርሻቸውን እንዲወጡም ገልጸዋል።

ለዘርፉ የተመደበው በጀት ብቻ ሳይሆን ተሽከርካሪዎችና ሌሎችንም ቁሶች በተገቢው ሊመሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ በየደረጃው የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት የበጀት ፍትሃዊነትና አሳታፊነት ላይ እንዲሠሩም ተገቢ የክትትል ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ከዳዉሮና ኮንታ ዞኖች የተገኙ የውይይቱ ተሳታፊ በቀጣይ የኦዲት ሥርዓትና የግዥ ክንውን ላይ የሚታየውን ክፍተት በማጥበብ፣ የዘገየ የግዥ ሥርዓትን በማሻሻል ወቅታዊ ሪፖርት በማቅረብ በኩል የድርሻቸውን ለመወጣት የሚያስችል ሥራ እንደሚያከናውኑም ገልጸዋል።

በውይይቱም የዳዉሮና ኮንታ ዞኖች የፋይናንስና ግብርና መምሪያ ኃላፊዎች የየጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአየር ንብረት፣ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም (CALM) ፎካሎችና የባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ናቸው።

ዘጋቢ፡ መሳይ መሰለ – ከዋካ ጣቢያችን