በገነት ደጉ
የዛሬው እቱ መለኛ ዓምድ ባለታሪካችን በንግዱ ስራ እና በመንግስት መስሪያ ቤት ከ15 ዓመታት በላይ ሰርተዋል፡፡
የመንግስት መስሪያ ቤት ከአንድም ሁለት እና ሶስት መስሪያ ቤቶች ጎራ ብለው እራሳቸውም ሆነ ቤተሰባቸውን በተሻለ የኑሮ ደረጃ ለመምራት በንግዱ መዝለቅን መርጠዋል፡፡
ወ/ሮ መአዛ አለማየሁ ይባላሉ፡፡ ትውልድ እና እድገታቸው እዚሁ ሀዋሳ ፒያሳ ፥ በተለምዶ ባህል አዳራሽ ጀርባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ኮምቦኒ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡
ከ7ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ወንድማቸው በመምህርነት ሙያ ስራ ተሰማርተው ስለነበር እርሳቸው ጋር በመሄድ በኦሮሚያ ክልል ሀገረ ማሪያም አካባቢ ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ ከ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ደግሞ ሶያማ፥ ልዩ ስሙ ቀርጫ በሚባልበት አካባቢ ነው ተምረው የጨረሱት፡፡
በ1991 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ውጤታቸው ጥሩ ቢሆንም ወደ ኮሌጅ እንዲገቡ ቤተሰባቸው ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ነው ያጫወቱን፡፡
አንድ ዓመት ቁጭ ብለው እንደገና ዳግም ማትሪክ ለመፈተን በማጥናት ጊዜ ሰጥተው እንደነበር ያስረዱት ወ/ሮ መዓዛ የተሻለ እና ከቀድሞው ውጤት የበለጠ ውጤት በማምጣት በ1993 ዓ.ም የትምህርት ማስረጃቸውን ይዘው ወደ ሀዋሳ መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ፀጉር ቤት በመግባት ፀጉር በማጠብ ስራ ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስም ሙያውን ከለመዱት በኋላ ለአንድ ዓመታት ያህል በሴቶች ፀጉር ቤት ሙያ ተቀጥረው ሲሰሩ እንደነበር ያስታወሱት ወ/ሮ መአዛ በሹሩባ እና ፀጉር በማጠብ ሰዎች እንደሚያደንቋቸው ነው የተናገሩት፡፡
ዛሬም ማንኛውንም ፀጉር ቤት ሄደው ቁጭ ማለትን እንደማይመርጡ ያጫወቱን ወ/ሮ መአዛ ሙያው ስላላቸው ወረፋ ካላ ቁጭ ብለው ከሚጠብቁ ይልቅ እንደሚያግዟቸው ነው ያጫወቱን፡፡
በኋላም በበኩር ልጃቸው ስም አብጊያ የሴቶች ውበት ሳሎን መክፈታቸውን አስረድተዋል፡፡
አብጊያ የውበት ሳሎንን ለሶስት ዓመታት ያህል በስራ ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ 05፣ አቶቴ እና ሰፈረ ሰላም ላይ ቅርንጫፎች ነበሩት። ወይዘሮ መዓዛ ከአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በሴክረተሪያል ማናጅመንት በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡ ፡ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በማዕረግ በመመረቃቸው ኮሌጁ እንደቀጠራቸውም ነው የተናገሩት፡፡
ወ/ሮ መዓዛ በኮሌጅ ውስጥ የነበራቸውን ስራ በማቋረጥ ከሰው ጋር በጋራ በመሆን የባህላዊ ምግብ ቤት መክፈታቸውን ነው ያጫወቱት፡፡
ብዙም ሳይቆዩ በጋራ እየሰራች የቆየቸው ሴት በወቅቱ ባለገንዘብ እርሷ ስለነበረች ገበያው በደንብ መልመዱን ስታውቀው እንድትለቅ እና አስረክባ እንድትወጣ በማድረጓ ምክንያት በአንድ ወር ውስጥ ዕቃ ተካፍለው ስለመውጣታቸው ነው ወ/ሮ መአዛ ያስረዱት፡፡
እራሳቸውን ለመቻል እና በግላቸው ለመስራት ሰዎችን አማክረው በወቅቱም ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ብር እንደሚያበድር መረጃ ሰብስበው 5ሺ ብር በመበደር ወደ ምግብ ቤት ስራ መግባታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በወቅቱም ጥሩ ምግብ ስለሚያቀርቡ ትልልቅ ሰዎች እና ባለስልጣናት እርሳቸው ጋር እንደሚመገቡ የተናገሩት ወ/ሮ መአዛ ዶክተሮች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሁሉ እያበረታቱአቸው እና እያመሰገኑአቸው ምግባቸውን ወደውት እንደሚበሉ ነው ያስታወሱን፡፡
በወቅቱ ምግባቸው በጣም ተፈላጊ እንደነበር ያስረዱት ወ/ሮ መአዛ በተለይም አትክልትና ሾርባን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን ለቁርስም ሆነ ምሳ እንዲሁም እራትን ጨምሮ እንደሚያቀርቡ ነው የተናገሩት፡፡
ምግብ የማንም እረዳትነትን ሳያሻቸው እራሳቸው ፈጥረው እንደሚሰሩ እና ደንበኞቻቸው ግን ስም እንደሚያወጡለት አንስተው “ምን ቀረሽ” የሚል ምግብ በሜኗቸው ላይ እንደነበር ነው የገለፁት፡፡
በኋላም ባንኮች ለምን እኛ ጋር ጫረታ አሸንፈሽ አትገቢም በማለት የባህላዊ ምግብ ስራ ትተው ወደ ንግድ ባንክ በመዛወር ሻይ ቡናን ጨምሮ ምግብ ማቅረብ ጥሩ እየሰሩ ቢቆዩም እንኳን ያቀረቡት ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ እና ብዙ ሰራተኛ በመኖሩ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ስራውን ማቋረጣቸውን ነው ያስታወሱን፡፡
በንግድ የተሻለ ቦታ መድረስ እንደሚችሉ የሚያስቡት እና ተስፋ ያልቆረጡት ወ/ሮ መአዛ በ56 ብር የፉርኖ ዱቄት ብድር በመውሰድ ወደ ኩኪስ ስራ ስለመግባታቸው ተናግረው አንድ ኪሎ ዱቄት በወቅቱ 15 ብር በመግዛት አንድ ኪሎ ኩኪስ 44 ብር በመሸጥ ዳግመኛ ወደ ንግዱ ዓለም መቀላቀላቸውን ነው ያጫወቱን፡፡
በወቅቱም ኩኪሱን ለማስተዋወቅ በኩርቱ ፌስታል በማያዝ አዙረው እንደሚሸጡ ተናግረው ከሀዋሳ ውጪ ሻሸመኔ፣ ዲላ፣ ጩኮ፣ አቡስቶ፣ ይርጋለም፣ወላይታ ሶዶ፣ ሀላባ እና ሀገረ ማሪያም ድረስ በመሄድ በእግር አዙረው እንደሚያስረክቡ ነው የተናገሩት፡፡
ለማደግ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ለራሳቸው ጉልበት ምንም ዓይነት ስስት እንዳልነበራቸው አንስተው ከዛሬ 13 ዓመት በፊት በ2003 ዓ.ም ወደ ስራው መግባታቸውን ነው ያስረዱት፡፡
እውቅና እያገኙ ሲሄዱ አዚ ኩኪስ የሚለውን እስቲከር ማሰራታቸውን አጫወተውን አዚ የልጅነት ስማቸው ሲሆን አብዛኛው የሀዋሳ ሰው መዓዛን ሳይሆን አሁንም ድረስ አዚ የሚለውን ስማቸውን እንደሚያውቅላቸው ነው የተናገሩት፡፡
ስልክ ቁጥራቸውን እዛው አስቲከር ላይ ባስቀመጡ ጊዜ ሀዋሳ ላይ የነበሩ ሱፐር ማርኬቶችም ሆነ ሚኒ ማርኬቶች በመደወል ትዕዛዝ እንደሚቀበሉ አጫወተውን ቀስ በቀስ ኩኪሳቸው እጅግ ተፈላጊ እና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት ስለመቻሉ ነው ያስረዱት፡፡
ስራው በጣም አድካሚ ነው ያሉት ወ/ሮ መዓዛ 24 ሰዓት እንቅልፍ በማጣት እንደሚሰራ አጫውተው የሰዎች ግብረመልስ እና ተቀባይነቱ እየጨመረ ሲመጣ ለምን ንግድ ፈቃድ አላወጣም በሚል ቀድሞ በፀጉር ቤት እና በምግብ ቤት ፈቃድ በእጃቸው የነበረውን በቅጣት መልሰው የኩኪሱን ንግድ ፈቃድ ስለማወጣታቸው ነው ያስረዳሉ፡፡
በጣም ብዙ ሀገሮችን በመዞር የህብረተሰቡን ፍላጎት በስፋት ስላዩ ሀዋሳ ላይ ላሉት ማንኛውም የንግድ ቤቶች በደረሰኝ በማስረከብ የተሻለ ገበያን በማትረፍ ከቆዩ በኋላ ስኳር ባለባቸው ሰዎች ጥያቄ መሠረትም የገብስ ኩኪስ እስካሁን ድረስ በጣም በፍቅር እና በብዛት እንደሚያቀርቡ ነው ያጫወቱን፡፡
በዚህም ያላበቁት እኚሁ ወ/ሮ በቀጣይነት ካሳቫ፣ የስኳር ድንች እንዲሁም የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ኩኪስ ላይ ቀስ በቀስ በመግባት የተሻለ በገበያ ላይ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ስለመምጣታቸው ነው ያስረዱት፡፡
በአሁኑ ሰዓት በስራቸው ለ11 ሰዎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረ የተናገሩት ወ/ሮ መዓዛ ባለቤታቸውም በክልሉ አደረጃጀት ምክያንያት ወልቂጤ ተመድበው የነበረ ሲሆን ስራቸውን ለቀው እያዙአቸው ሲሆን አሁን ላይ ጤናን መሰረት ያደረገ ኪኪስ እየሰሩ ስለመሆናቸው አስረድተዋል፡፡
በተለይም ቡርትካናማው ስኳር ድንጅ በቫይታሚን “ኤ” የበለፀገ በመሆኑ በላብራቶሬም የተረጋገጠ ስለመሆኑ አንስተው ምጥን ኩኪስ እያቀረቡ ስለመሆናቸው ነው ያስረዱት፡፡
አሁን ላይ 16 ዓይነት በቫይታሚን በበለፀጉ የጥራጥሬ እህሎች የተዘጋጀ ኩኪስ ያቀርባሉ፡፡
በተለይም ከጤና አንፃር ማሽላ እና አጃ ላይ በጣም እንደሚሰሩ ተናግረው እያንዳንዱ ምርታቸው በቫይታሚን የበለፀገ እና ጤናን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በሰዎች ዘንድ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት።
ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅርበት የሚሰሩ ሲሆን በተለይም ብርቱካናማው ስኳር ድንች ላይ የሚሰራ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመሆን በተለያዩ ኤግዚቢሽኖችም ላይ በማቅረብ እውቅናን ማትረፋቸውን ነው ያስረዱት፡፡
አሁን ላይ የኢትዮጵያ “ኤክስፖርቶች” ማህበር ጋር እንደ ሀገር “ኤክስፖርት” ከሚደረጉ የቅባት እህሎች አኩሪ አተር አንዱ ሲሆን ኢትዮጵያ አኩሪ አተርን “ኢንፖርት” በማድረግ እና እንዲሁም የአኩሪ አተር ምርቶችን “ኤክሰፖርት” በማድረግ ረገድ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለች ነው ያጫወቱን፡፡
አኩሪ አተር ዳቦ፣ወተት፣ ኩኪስ መሆን እንደሚችል የተናገሩት ወ/ሮ መአዛ ማቀነባበሪያ ያላቸው ድርጅቶች ጋር አብረው እየሰሩ ሲሆን ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ምርቶቻቸውን አስተዋውቀዋል፡፡ ያስተዋወቁ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም አንፃር በትኩረት እየሰሩ ስለመሆናቸው ነው የተናገሩት፡፡
አሁን ላይ ለአዲስ ዓመት የአኩሪ አተር ኩኪስ ምርቶችን እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ወ/ሮ መአዛ የእኛ ድህነት ዋናው የአስተሳሰብ ድህነት ነው በማለት አጽንኦት ሰጥተው ብዙ ልንመገባቸው የምንችላቸው ምግቦች እያሉ ግን እንደማንመገባቸው አስረድተዋል፡፡
ዱባ እና ስኳር ድንች የደሃ ምግቦች ተብለው የተፈረጁ ናቸው ያሉት ወ/ሮ መዓዛ የሀገራችን ህዝብ ከተለመደው ነገር ወጣ ማለትን አይወድም በማለት ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ባለትዳር እና የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ልጆቻቸውን በበለፀጉ ምግቦች ያሳደጉ በመሆናቸው ምንም ዓይነት ምግብ እንደማመርጡ እና ሀገራችን ላይ ኖሮ ውድ ነው ስንል ያልበላናቸው በርካታ ኦርጋኒክ የሆኑ ምግቦችም ወደ ጎን እንደተውናቸው ልብ ልንል ይገባልም ብለዋል፡፡
የንግድ ፈቃዳቸው በፌዴራል መንግስት ገቢዎች ስር እንዳለ አንስተው የአከራይ ተከራይ 7ሺ ዓታዊ ግብር እስከ 2መቶ ሺ በመክፈል የቫት ተጠቃሚ ስለመሆናቸው ነው ያስረዱት፡፡
የንግድ ፈቃዳቸውም “አዚ ሻሎም ምጥን ኩኪስ ሀላፊነቱ የታወቀ የግል ማህበር” ሲሆን የማሀበሩ መስራች እርሳቸው ስለመሆናቸውም አንስተዋል፡፡
በመጨረሻም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ2017 ዓ.ም በሰላም አደረሳችሁ በማለት ሴት እህቶች ማንኛውንም ስራ ከሰራችሁ ውጤታማ ትሆናላችሁና አዕምሮአችሁን በትንሽ አትገምቱት መስራት ከቻላችሁ ለራሳችሁ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች መትረፍ ትችላለችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ መብት ወይስ ግዴታ?
የ28 ዓመታት ትዝታ እና ፈተናዎች
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”