“በአሮጌው ዓመት መጨረሻ እና በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ” – ጳጉሜን

በብዙነሽ ዘውዱ

ጊዜን ለመረዳት እና ለማደራጀት የሰው ልጆች በታሪካቸው ከጥንታዊ ስልጣኔዎቹ ጀምሮ አንስቶ ኮከቦችን እያዩ የራሳቸውን ስርዓት ለመፍጠር እስከ ዛሬ ያለበት የጊዜ ቀመር አቆጣጠር መድረስ ችሏል፡፡

በራሳቸው የጊዜ ቀመር አቆጣጠር ከሚታወቁ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን የዘመን አቆጣጠሯም 13 ወራት ያላት በመሆኗ ልዩና ብቸኛዋ እንደትሆን አድርጓታል፡፡

እያንዳንዳቸው 12 ወራት 30 ቀናት ሲኖራቸው 13ኛዋ ወር ጳጉሜን 5 ወይም በየአራት ዓመት አንድ ጊዜ 6 ቀናት ሆኖ ይቆጠራል። የኢትዮጵያ ዓመት ከጎርጎርያን(እ.አ.አ) የዘመን አቆጣጠር ከ 7 እስከ 8 ዓመታት የዘገየ ሲሆን ይህም የኢየሱስን መወለድ መሠረት በማድረግ በተደረጉ የሂሳብ ልዩነቶች ምክንያት እንደሆነ መዛግብቶች ያስረዳሉ።

“የጨረቃ የዕለት፣ የወር እና የዓመት ቀመር በኢትዮጵያውያን ሥሌት ቀደምት ኢትዮጵያውያን የፀሓይና የጨረቃ የዘመን አቆጣጠርን ይጠቀሙ ነበር፡፡ የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንት ዛሬ ድረስ ሁለቱንም አቆጣጠር በዐዲስ ዓመት ላይ ያወጣሉ፡፡ ቀደምት የኢትዮጵያውያን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች በጨረቃ ላይ ያላቸው ዕውቀት እጅግ የተራቀቀ ስለነበር የጨረቃን መንገድ (ፍና ወርን) ሳድሲት ተብላ እስከ ምትጠራው ደቀቋ የጊዜ መስፈርት ድረስ ወርደው ያሠሉ እንደነበርም” ዶ/ር ሮዳስ ጌትነት እና ዶ/ር ጌትነት ፈለቀ  “አንድሮሜዳ” መጽሐፋቸው ላይ ለአብነት በዝርዝር አስቀምጠውት እናገኘዋለን፡፡

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ሲሆን በተመሳሳይ የዕብራይስጥ አቆጣጠር ከአይሁድ እምነት፣ የሂንዱ አቆጣጠር ከሂንዱይዝም ጋር የተቆራኘ እንደሆነ የዩኪፒዲያ ማሳረጃዎች ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ለሁሉም ህዝባዊ እና ሀይማኖታዊ አላማዎች የሚውል ሲሆን በሌሎች እንደ ህንድ፣ እስራኤል እና ቻይና ባሉ ሀገራት ባህላዊ የቀን መቁጠሪያዎች በዋናነት ለሀይማኖት ወይም ለባህላዊ ጉዳዮች ይገለገላሉ፣ የጎርጎርያን የቀን አቆጣጠር ለሲቪል ጉዳዮች ይጠቅማል።

የጎሪጎሪያን ካላንደር አብዛኛው ዓለም ቢከተልም፣ ኢትዮጵያ ግን ከጎሪጎሪያን ካላንደር ከ7 እስከ 8 ዓመታት ያህል ወደኋላ ያለውን የዘመን አቆጣጠር መከተሏን ቀጥላለች። በአንፃሩ የኢራን የቀን አቆጣጠር ከጥንታዊ ባህሎች የመነጨ ቢሆንም በዋናነት ለሲቪል ዓላማዎች ይውላል።

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የብሄራዊ ኩራት ምንጭ ጭምር ነው፡፡ የ13ኛው ወር ልዩነት የኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ላይ ያላትን ልዩነት የሚያሳይ ትልቅ ሃብቷ ነው። ጳጉሜን በአሮጌው ዓመት መጨረሻ እና በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ መካከል ያለ የሽግግር ወርሃም ነው። ጳጉሜን ብዙ ጊዜ የማሰላሰል ጊዜ እና ለአዲሱ ዓመት መንፈሳዊ ዝግጅት ተደርጎ ይወሰዳል። ብዙ ሰዎች በዚህች አጭር ወር ራሳቸውን በመንፈሳዊ ለማንጻት፣ ለአዲሱ ዕቅድ፣ ስኬት፣ ህልም ጅምር ለመዘጋጀት ይጠቀማሉ። ከጳጉሜን ወደ መስከረም የሚደረገው ሽግግር በዓዲስ መንፈስ እንደ መታደስ ተደርጎ እንደሚቆጠር ይገለጻል።

ቀደምት ኢትዮጵያውያን ባስቀመጡት መሠረት ይህን ስሌታቸውን አሁን ያሉት የሥነ ፈለክና የሒሳብ ሊቃውንት ተመራምረው እንዲደርሱበት፤ አንባብያንም ሒሳቡን ወደ ዘመናዊ እየለወጡ እንዲመራመሩበት የቤት ሥራ ደቂቃና ሴኮንድ እየለወጡ አስፍረው አኑረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አዲስ ዓመቷን ከዝናብ ወቅት ማብቂያ ክረምቱ መጠናቀቂያ ማግስት ገበሬው ፈጣሪውን አምኖ የበተነው ዘሩ ለምልሞ አድጎ ለፍሬ ሲቃረብ፤ በክረምቱ ዝናብ ደፍርሶ የነበረው የወንዙ ውሃ ሙላት ሲጎድል፤ አደይ አበቦች ምድሪቷን በሚያስጌጧት በመስከረም ወር ዓመቱን አሃዱ ብላ በድምቀት ታከብረዋለች።

ኢትዮጵያ ዓዲስ ዓመቷን በምታከብርበት በዚሁ ወረሃ መስከረም ተፈጥሮ በራሷ አስባበት እንኳን አደረሰሽ ለማለት ይመስል ውብ ህብር ያጌጠ መልኳን ይዛ በልምላሜ እና በአደይ ቢጫ አበቦች አጊጣ ትቀበላታለች፡፡

ኢትዮጵያውያን ዓዲስ ዓመትን በተስፋ፣ ልምላሜ፣ በታደሰ አዲስ መንፈስ፣ በደስታ በጉጉት የሚጠባበቁት ወቅት ነው፡፡ ዓዲሱን ዘመን ሲቀበሉም ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በመሆን ተሰባስበው አምላካቸውን ከከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት በሰላም ስላሸጋገራቸው እያመሰገኑ ዓዲሱ ዓመት ፍሬያማ የሚሆኑበት የሚባረኩበት እንዲሁም መልካም ገፀ-በረከት የሚቸሩበት ይሆንላቸው ዘንድ በመመኘት ይቀበሉታል፡፡