ህብረ-ብሄራዊነትና ብዝሃነት ለኢትዮጵያዊነት ከፍታ መሠረቶች በመሆናቸው አብሮነትን ይበልጥ  በማጠናከር ለሀገራችን እድገት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህብረ-ብሄራዊነትና ብዝሃነት ለኢትዮጵያዊነት ከፍታ መሠረቶች በመሆናቸው አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር ለሀገራችን እድገት መስራት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ።

በዞኑ ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጳጉሜን 4 “ኅብራችን ለአንድነታችንና ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ-ቃል የማስ ስፖርትን ጨምሮ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ህብረ-ብሄራዊነትና ብዙሃነት ለኢትዮጵያዊነት ከፍታ መሠረቶች በመሆናቸው ይህንኑ አብሮነት  በማጠናከር ለሀገራችን እድገት መስራት ይገባል ብለዋል።

ህብረ-ብሄራዊነት ልዩነታችን ውበትን አላብሶ ውበታችን አንድነታችንን አረጋግጦ ተከባብረንና ተቻችለን እንድንኖር መሰረት የጣለ ነው ያሉት አቶ ላጫ፥ ይህን መነሻ ያደረገና በመተጋገዝ ላይ የተመሰረተ ስራ ከተሰራ ብልፅግናን በሀገራችን ማረጋገጥ እንደምንችል ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እየተሰሩ ያሉ ልማቶች የአብሮነትን ዕሴት የሚያጎለብቱ እና ማህበራዊ አንድነታችን የሚያጠናክሩ ናቸው በማለት በዋናነት  የሚሰሩ ሁሉን አቀፍ  ልማቶች የህዝቦችን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ  በመሆናቸው ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታ በበኩላቸው የከተማው ህዝብ በአካባቢው ልማትና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተጀመረው ተግባር በተሻለ ደረጃ መፈጸም ይኖርበታል ብለዋል።

የህብር ቀንን ምክንያት በማድረግ የተከናወነው ማስ ስፖርት ህዝቡ ህብራዊነቱ የሚያጠናክር ሲሆን ይህን በአዲሱ አመት አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

የማስ ስፖርቱ ተሳታፉዎች እንዳሉት ስፖርት ከጤናው ባሻገር አንድነትን ለማጠናከር አጋዥ መሆኑን ጠቁመው የህብር ቀንን ምክንያት በማድረግ የተደረገው እንቅስቃሴ የአብሮነት እሴት ማሳያ ነው።

ህብራዊነት ከብዝሃነት ውስጥ የሚወለድ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የመተሳሰብ፣ የወንድማማችነት ቀለም ነው በማለት ይህም በበጎ መልኩ በመውሰድ ለልማት ማዋል ይጠበቃል ብለዋል።

ተፈጥሮአዊ ፀጋችን ውበታችን የሆነውን ኅብራችን ለአንድነታችንና ዘላቂ ሰላማችን በመጠቀም ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ልንጠቀምበት ይገባል የሚል መርህ ያነገበው በአሉ የዞን ማዕከልና የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣የመንግስት ሰራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን