አንድነታችንን በማጠናከር ለሀገራችን ሰላም በጋራ መቆም እንደአለብን የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለጹ

በቀቤና ልዩ ወረዳ ጳጉሜን 4 “ኅብራችን ለአንድነታችንና ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ቃል የማስ ስፖርትን ጨምሮ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነታችንን በማጠናከር ለሀገራችንና ለአካባቢያችን ዘላቂ ሰላማችንና ብልፅግና በጋራ መቆም እንደሚገባ የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በዚሁ ወቅት ገልፀዋል፡፡

ያለወጣቶች የነቃ ተሳትፎ ልማትና ብልፅግና ማረጋገጥ አይቻልም ያሉት አቶ ሞሳ በተለይም ወጣቶች በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጁሃር ጀማል በበኩላቸው ስፖርት ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአብሮነት መሰረተ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም በያለበት አካባቢ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናውን ከመጠበቅ በሻገር ለሀገሪቱ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት መጎልበት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ የልዩ ወረዳው አመራሮች፣ ወጣቶች፣ የአካባቢው ማህበረሰብና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን