በክልሉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የወባ በሽታ ታካሚዎች ቁጥር 27 በመቶ መቀነስ መቻሉም ተጠቁሟል።
በክልሉ የወባ ስርጭት ሂደት የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እና የጤና ባለሙያዎች በተገኙበት በሚዛን አማን ከተማ ተገምግሟል።
የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚገኙ በሁሉም ዞኖች መከሰቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ተናግረዋል።
የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል ባለፉት ሶስት ወራት በየደረጃው ባሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ህብረተሰቡን ባካተተ ሁኔታ ርብርብ መደረጉን ነው አቶ ኢብራሂም የሚናገሩት።
በዚህም በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር በተሰራው ስራ በተለይም በአጎበር አጠቃቀም እና በህክምና ዙሪያ ለ1ሚለየን 892 ሺ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተሰርቷል ብለዋል። እንዲሁም 735 ሺ 529 ቤቶች መጎብኘታቸውን ጠቁመዋል።
በክልሉ ለወባ መራቢያ ይሆናሉ ተብለው የተለዩ 2 ሚሊየን 231 ሺ ካሬ ሜትር ቦታዎች የማፋሰሻ እና የማዳፈን ስራዎች መሰራታቸውን የተናገሩት አቶ ኢብራሂም በተመረጡ 73 ቀበሌያትም 134 ሺ 165 ቤቶች ላይ ኬሚካል ተረጭቷልም ብለዋል።
ለዚሁ ተግባራትም ከ31 ሚሊየን 327 ሺ ብር በላይ በጀት ወጪ መደረጉንም ጠቁመዋል።
በክልሉ በአሁነ ሰአት ተኝቶ ታካሚ ቁጥር 27 ከመቶ እንዲሁም ተመላላሽ ታካሚ 11 ከመቶ ቀንሷል ያሉት አቶ ኢብራሂም አጠቃላይ ባለፉት አስራ አምስት ቀናት 27 ከመቶ ስርጭቱ መቀነሱን ተናግረዋል።
ቀጣይ ወራቶች ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ወራት በመሆናቸው የተጀመረው የመከላከል ስራ ተጠናክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ በበኩላቸው በክልሉ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል አቅጣጫ ተቀምጦ ሁሉም ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በተሰራው ስራ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።
ይህ የተገኘው ውጤት በተጀመረው የንቅናቄ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ መሰራት አለበት በማለት ተናግረዋል።
ከህገወጥ የመድኃኒት ዝውውር እና ሽያጭ ጋር ተያይዞ በየግል ተቋማት የሚገኙ የወባ መድኃኒት ጥራት አቅርቦት የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን ጥምር ደን መጠበቅ፣ ማስፋትና መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ