የፀጥታ አካላት በየዘመኑ የአገር ክብርና ሉአላዊነትን በማረጋገጥና መስዋዕትነት በመክፈል እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ

ጳጉሜን 3 – የሉአላዊነት ቀን በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ በመድረኩ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአለም ብቸኛዋ የ13 ወር መቁጠሪያ ካላንደር ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

መንግስትም ባለፉት ዓመታት ጳጉሜን የተለያዩ ትርጓሜ በመስጠት በድምቀት ሲያከብር መቆየቱን አስታውሰዋል።

የፀጥታ አካላት በየዘመኑ የአገር ክብርና ሉአላዊነትን በማረጋገጥና መስዋዕትነት በመክፈል እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከማንም በፊት በኩራትና በድፍረት በአደባባይ የምትናገረው ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ መቆየቷን ነው ያሉት አቶ ጸጋዬ ለአለም የጥቁር ህዝቦች ነጻነት ምሳሌ የሆነችና ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች ተምሳሌት ሀገር ናት ብለዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ እንደተናገሩት ሀገራችን ከጥንት አባቶቻችን ጀምሮ ታፍራና ተከብራ የኖረች በቅኝ ያልተገዛች የአፍራካ የነጻነት ተምሳሌት ተደርጋ እንደምትታይ አንስተዋል።

እንደ ሀገር ከውጭ የሚሰነዘርብንን የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና በማህበራዊ ሚዲያ ጫና በተባበረ ክንድ ተደምረን በመመከት ሉአላዊነታችንን ማስከበር ይገባል ብለዋል።

በተለይ የፀጥታ መዋቅሩ የሀገርን ሉዓላዊነትና ነፃነት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሁሉንም ችግሮች ተቋቁሞ በላቀ ብቃት ግዳጁን እየፈፀመ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የጸጥታ አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አለሙ፤ ክልላዊ የጸጥታ መዋቅር ተግባራት ላይ ለውይይት መነሻ ሰነድ አቅርበዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ አካላት እንደተናገሩት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረ የጸጥታ መደፍረስ በርካታ የሰራዊቱ አካላት ከህይወት መስዋዕትነት ጀምሮ መስዋዕትነትን በመክፈል ዛሬ ላይ አንጻራዊ ሰላም ተገኝቷል ብለዋል።

በክልሉ ሁሉም አካቢዎች አሁን ላይ የጸጥታ መዋቅሩ የጀመረውን የሠላም ስራ ይበልጥ አጠናክሮ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፌደራል፣ የክልሉና የዞን የፖሊስ ሰራዊት አባላት በከተማው የሰልፍ ስነ-ስርዓት ያካሄዱ ሲሆን በመድረኩ ማጠቃለያም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በጋራ ተዘምሯል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን