የኢትዮጵያ ቡና በአለም ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከደን ምንጣሮ ነጻ በሆነ መልኩ መልማት እንዳለበት ተጠቆመ።

ከደን ውጪ የለማና የአከባቢ ጥበቃ ሂደትን ያላለፈ ቡና የአውሮፓ ዩኒየን እንደማይቀበልም ተገልጿል።

ይሄም የተገለጸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ የፍሎር ፕሮጀክት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ባካሄደበት ወቅት ነው

የፍሎር ፕሮጀክት በኢትዮጵያ 4 ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 3 ወረዳዎች ላይ  እንደሚሰራ የተናገሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ  የደን ​​መጥፋትን መከላከል፣ መልሶ ማልማትን ማቋቋም   እና ዘላቂነትን በኢትዮጵያ የቡና እሴት ሰንሰለት እና የምግብ ስርዓት ማቀናጀት ዋነኛ የፕሮጀክቱ ተግባራት   እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችለው የአውሮፓ ዩኒየን ባወጣው ህግ መሰረት ቡናና ደን በአንድነት መልማት ሲችሉና የአከባቢ ጥበቃ ሂደት ውስጥ ሲያልፍ መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛቴ ከዚህ ውጪ ያለውን  ቡና የአውሮፓ  ዩኒየን  እንደማይቀበል አስታውቀዋል።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፍሎር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ወርቁ በኢትዮጵያ  ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ያረጀ ቡና ምርት ስለማይሰጥ በአርሶአደሩ ማሳ ይሄንኑ በማደስ ዘላቂ ምርት እንዲሰጥ የማድረግ ስራን ፕሮጀክቱ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ በተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ከፍተኛ እምርታ እያሳየች ነው ያሉት  አቶ ሙሉጌታ የፍሎር ፕሮጀክት ከ60 ሺ ሄክታር ያላነሰ የተፈጥሮ ደኖችን ዘላቂ ሆነው እንዲቀጥሉ የማድረግና የተራቆቱት ደግሞ መልሰው እንዲያገግሙ ይሰራል ብለዋል።

 ማንኛውም ቡና አምራች አከባቢ ከደን ምንጣሮ ነጻ ሊሆን ይገባል ያሉት የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ ይሄንኑ ህግ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ እንዳለ ገልጸዋል።

ዘጋቢ : ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን