በደረሰ አስፋው
የወጣትነት ዘመን እንዴት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል የሚታሰብበት የእድሜ ክልል ነው። አንዳንዶች የስኬትን መንገድ ጀምረው ለጉዞው ደፋ ቀና የሚሉበት የሕይወት ምዕራፍም ነው። መነሻቸውንም የማይዘነጉ የስኬት አርዓያዎች መሆንም ከወጣቶች የሚጠበቅ ነው” የሚሉት ወ/ሮ መድሃኒት ከበደ ሰው በተፈጥሮ ያገኘውን ተሰጥኦ ከዓላማና ጥንካሬ ጋር አስተሳስሮ፣ እደርስበታለሁ ብሎ ከሚያስበው ግብ ላይ መድረስ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
እውቀት ያለው እውቀቱን፣ ገንዘብ ያለው ገንዘቡን እንዲሁም ጉልበት ያለው ጉልበቱን አቀናጅቶ ለማህበረሰቡ ታምኖ ቢሰራ ሀገርን፣ ማህበረሰብን ብሎም እራሱን ይጠቅማል የሚል የጠለቀ ሀሳባቸውን በማጋራት ነው ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ በአሁኑ ወቅት ሴቶች የሚያጋጥማቸውን ባህላዊ ተጽእኖዎች ተቋቁመው በተሰማሩባቸው የስራ መስኮች ሀብት አመንጭተው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል የፈጠሩ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡ በዛሬው የእቱ መለኛ አምዳችን በአመራርነት ሀገርንና ህዝብን ስለሚያገለግሉ ሴት አመራር የህይወት ተሞክሮ እናጋራችኋለን፡፡
በወጣትነት ዕድሜ ላይ እንደመገኘታቸው ወጣትነትን ለበጎ ዓላማ መጠቀም አለብን የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ የተሰጣቸውን የወጣትነት እድሜያቸውን ለበጎ በማዋል ለሌሎች ሴቶች አርያ ሆኖ የመታየት እልህና ቁጭት ያለባቸው ስለመሆኑም በንግግራቸው ላይ ይገልጻሉ፡፡ ወ/ሮ መድሃኒት የሲዳማ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የአቅም ግንባታና የመሰረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ በመሆን መንግስት የጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚተጉ ወጣት ሴት አመራር ናቸው፡፡ በጠንካራ ትጋት ታጅበው በስኬት ጎዳና ላይ ከሚገኙ ስኬታማ ሰዎች መካከልም ተጠቃሽ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሴትነትና ማህበራዊ ተጽእኖው ከአላማቸው ሳይገታቸው ለሌሎች ወጣቶችና ሴቶች አርያ ለመሆን በሚያስችል የአመራር ቁመና ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
በተለይ አሁን ወጣቱ አላስፈላጊ ተግባራትን በማስወገድ ለሀገር በሚጠቅም መንገድ በመሰማራት ህዝብን ማገልገል እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በሲዳማ ክልል ሀዌላ ሊዳ ወረዳ የተወለዱት ወ/ሮ መድሃኒት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት በሀዌላ ሊዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 5ኛ ክፍል በመማር ነው ትምህርታቸውን የጀመሩት፡፡ ወደ ሀዋሳ ከተማ በመምጣት በኢትዮጵያ ትቅደም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ6ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የተከታተሉ ሲሆን ከ9ኛ ክፍል እስከ መሰናዶ ትምህርት በታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡
የዩኒቨርስቲ የመግቢያ ፈተናንም ጥሩ ውጤት በማምጣት በባህርዳር ዩኒቨርስቲ በጂኦግራፊካል ኢንቫሮመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከአንድ አመት የመንግስት ስራ በኋላም በአርባን ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ 2ኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡ የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ወ/ሮ መድሃኒት ከነጋዴ ቤተሰብ ቢገኙም በመንግስት ሥራ መቆየትን ነው የመረጡት፡፡ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት በወሳኝ ኩነት ምዝገባ በባለሙያነት ተመድበው የስራ ጅማሬያቸውን ያደረጉ ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርስቲም በመምህርነት ለ4 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ አሁን ደግሞ መንግስት የጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በሲዳማ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የአቅም ግንባታና የመሰረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ በመሆን እያገለገሉ ይገኛል፡፡
ወደ አመራርነት ከመጡ በኋላ የወጣትነት ዕድሜያቸውን ህዝብንና ሀገርን በአወንታዊ መልኩ እያገለገሉ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የወጣትነት ዕድሜን በአግባቡ ከተጠቀሙበት አወንታዊ ጎኑ እንደሚያዘነብል የሚገልጹት ወ/ሮ መድሃኒት ሴትነትም ይሁን አመራርነት በስራቸው ተግዳሮት እንዳልሆነባቸው ያነሳሉ፡፡ ወደ አመራርነት ቢመጡም ያሉበት የዕድሜ እርከን የስራ አቅምን የሚጠቀሙበት በመሆኑ በበጎ ጎኑ ነው የሚመለከቱት፡፡
የመንግስት ኃላፊነትን በተቀመጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎችን የመፈጸም ስራ በመሆኑ ሴት ስለተሆነ ሌላ ፈታኝ ነገር እንደሌለው ያነሳሉ፡፡ በተለይ ሴቶች አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብ ለመቀየር ተግባራቸውን በቁጭትና በታማኝነት በመፈጸም አስተሳሰቡን የመቀየር ዓላማ አንግበው እንደሚሰሩ ይናገራሉ፡፡ ይህን ዕድል በተሻለ እይታ ቃኝቶ በህብረተሰቡ ውስጥ ጥያቄ የሆኑ ጉዳዮችን ቅድሚያ እየሰጡ ማገልገል እንጂ አመራርነትና ሴትነት የሚጋጭ ነገር የለውም ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ በርካታ ሰዎች እራሳቸውን ቀድመው ተሸናፊ በማድረግ ለሽንፈት እጅ ይሰጣሉ፡፡ በተለይ ሴቶች፣ “እኔ ብቁ ነኝ፤ እችላለሁ” ከማለት ይልቅ “ያቅተኛል፤ አይሆንልኝም” ማለትን ሲለማመዱ በራስ መተማመን ብቃታቸውን ይሸረሽረዋል። በአንጻሩ ደግሞ “ይቻላል” የሚለው ስሜት ሰዎችን በራሳቸው እንዲተማመኑ የማድረግ ሀይል እንዳለው ልብ ሊባል ይገባል፡፡
እችላለሁ ብሎ ከተነሳ ያን ያሰበውን ከማድረግ የሚከለክለው እንደሌለ ካላቸው የስራ ህይወት በመነሳት ይገልጻሉ፡፡ “ህይወቴን በመርህ በመምራቴ ተጠቃሚ አድርጎኛል፡፡ ቤቴን የምመራበት ህግ አለ፡፡ በተመሳሳይ የመንግስት አመራርነትን የምመራበት አሰራር አለ፡፡ እንዚህ ሳይደበላለቁ መምራት ከተቻለ ፈተና የሚሆንበት ነገር የለም፡፡ ይሄ ችግር አለብኝ ብዬ ከማስበው ይልቅ እየሰራው ባልደረስኩበት ነገር ነው የምቆጨው ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚል አባባል አለ፡፡ እርስዎ ኃላፊነትን በሀቀኝነት ከማገልገል አኳያ እንዴት ይገልጹታል? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ፡- “የሰው ልጅ ዕድል የሚመጣው አንድ ጊዜ ነው፡፡ ብዙ ስለተማረ መሪ ሊሆን አይችልም፡፡
ስላልተማረም መሪ ላይሆን አይችልም፡፡ ስልጣን ከፈጣሪ ካልተሰጠ ለማንም የለውም፡፡ ይህን ዕድልን የሚሰጠው ፈጣሪ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህን የተሰጠህን ሀላፊነት በአግባቡ መጠቀም ደግሞ ከግለሰቡ የሚጠበቅ ነው። ስርአቱ የፈቀደው ስርቆትም የለም፡፡ ችግሩ የግለሰቡ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ፈጣሪም ይሁን ህዝቡ አምኖ በሰጠኝ ሀላፊነት የሚጠብቀው ነገር አለ። ባለጉዳይ ከማስተናገድ አኳያ ችግሩን ሰምቶና ተረድቶ ምላሹ ባለጉዳዩን ያርካውም አያርካውም በተገቢው ተስተናግዶ መውጣት አንዱ መገለጫ ሊሆን ይገባል፡፡ “ለእኔ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን አባባል “ሲሾም የበላ ሲሻር መግቢያ የለውም” በሚለው ሀሳብ ነው የምስማማው።
የምከተለው የህይወቴ መርህም ይሄንኑ ነው። ትናንት በቅንነት ያላገለገለው ማህበረሰብ ነገ እንዴት ይቀበለዋል፡፡ ማህበረሰቡ ዞሮ መግቢያ በመሆኑ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል፡፡ ሁሉም የህበረተሰቡ አካል እንደመሆኑ የህብረተሰቡ አገልጋይ መሆን አለበት፡፡ “እራስን በትምህርት ከማብቃት ውጭ ኃላፊ እሆናለሁ ብዬ አይደለም የተማርኩት፡፡ በተሰጠኝ ዕድል ግን ህብረተሰቡን ማገልገል እንዳለብኝ በማሰብ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ላይ አገልግሎት ሰጥቻለሁ። ማህበረሰቡን በጥንቃቄና በአግባቡ ነበር የማገለግለው፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ የተዝረከረከ ስራን አልወድም፡፡ ጊዜም እንዲባክንብኝ አልፈልግም፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ለ4 ዓመታት ሳስተምር ተማሪዎቼን ቀለም ብቻ ሳይሆን በስነ- ምግባር በማነጽ ለነገዋ ሀገር ተስፋዎች እንዲሆኑ የራሴን ምክር በመለገስ የበርካቶችን ህይወት ለውጫለሁ፡፡
በአመራርነትም የተሰጠኝን የመንግስትና የህዝብ ኃላፊነት በብቃት ከመፈጸም ውጪ ሌላ ዓላማ የለኝም፡፡ ኃላፊነት ከማህበረሰቡ በሚያርቅ መልኩ መሆን የለበትም፡፡ “አንድ አመራር ህዝብን በሀቀኝነት ማገልገል ሲወደው የሚያደርገው ሳይሆን የህይወቱ መርህ ሊሆን ይገባል፡፡ የሚያገለግለው እራሱን፣ እናቱን፣ አባቱንና ወንድም እህቶቹን እንደሆነ መረዳት አለበት፡፡ ከአቅሜ በላይ ካልሆነ በስተቀር ባለጉዳይ እንዲጉላላ አልፈልግም፡፡ በኔ ዘንድ የባለጉዳይ ቀን ተብሎ የተለየ ቀን የለም፡፡ ሁሉም ቀን የባለጉዳይ ቀን ነው፡፡ ከሌሎች መደበኛ ስራዎች ጎን ለጎን ባለጉዳይ ይደመጣል፤ ይገለገላል፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነ አገልግሎት ግን ሀጢያት ነው፡፡
ወ/ሮ መድሃኒት ለስኬታቸው ያበቃቸውን ሚስጥር ሲገልጹ፡- “የፈጣሪ እገዛ የመጀመሪያው ቢሆንም የዓላማ ጽናት ለስኬት ቁልፍ ነገር ነው፡፡ የት እደርሳለሁ ብዬ አስብ ነበር፡፡ የዕድሜዬን መልካም አጋጣሚ ለሌላ ብልሹ ነገር አልተጠቀምኩም፡፡ መድረስ ያለብኝን ቦታ እያሰብኩ ነበር የምጓዘው፤ አሁንም መድረስ ያለብኝ ቦታ ገና አልደረስኩም። አንድ ሰው እውነተኛ ስኬት አገኘ የሚባለው ደግሞ በተሻለ የህይወት መንገድ መጓዝ ሲችል ነው፡፡ ይህ መንገድ አምላክ የፈቀደውን የስነ- ምግባር መስፈርቶችን ተግባራዊ ማድረግንም የሚጠይቅ ነው፡፡ ወ/ሮ መድሃኒት በልጅነት ዕድሜያቸው አመራር እሆናለሁ ብለው ባያስቡም ውጤታማ ሴት እንደሚሆኑ ግን ህልሙ ነበራቸው።
አባታቸው አብዛኛውን ጊዜ በንግድ ስራ ላይ ስለሚያሳልፉ እንደሌሎች ልጆች ስታድጊ ምን ትሆኛለሽ? ተብለው የተጠየቁበትንም አያስታውሱም፡፡ የ8ኛ ክፍል እንደተፈተኑ ግን ሳያስቡት ጠየቋቸው፡፡ የሰጡት ምላሽም ፕሮፌሰር እሆናለሁ የሚል ነበር፡ ፡ በህይወታቸው ሽንፈት የሚባል ነገር አስበው እንደማያውቁ የሚገልጹት ወ/ሮ መድሃኒት የአንደበትህን ፍሬ ትበላለህ እንደሚለው ቅዱስ ቃሉ እኔም እመኝ የነበረው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህም አሁን ላሉበት ደረጃ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው የሚገልጹት፡፡ “ሴት ልጅ መሪ ናት፡፡ ሴት ቤቷን ማስተዳደር ከቻለች ሌላውንም ትችላለች፡፡ ሴት መሪ የመሆን የተፈጥሮ ችሮታ ተሰጥቷታል፡፡ ሴት የተከፈተ አዕምሮ ያላት ነች፡፡ ይህን በአግባቡ ብትጠቀመው ደግሞ ለሀገርም ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለች፡፡ መሪነት ለሴት ተመራጩ ዘርፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በእርግጥ ስራውን በአግባቡ ካልመራነው አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ጊዜን በተገቢው መጠቀም ከቻልን ውጤታማ እንሆንበታለን ይላሉ፡፡ ሴት ልጅ ለበርካታ ዘመን የባህልና የማህበረሰቡ ተጽእኖ ተጭኗት መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ከቤት ይጀምራል፡፡ ወ/ሮ መድሃኒት ግን ይህ ተጽእኖ አልፈተናቸውም፡፡ ከወላጅ አባታቸው የሚጀምረው ነጻነት የትዳር አጋራቸውም ለስኬታቸው አጋዥ እንደሆናቸው ነው የሚገልጹት፡፡ አመራር በመሆናቸው ከማገዝ ውጪ ለምን ወጣሽ ለምን ገባሽ የሚል አመለካከት አልገጠማቸውም፡፡
በዚህም ዕድለኛ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት፡፡ ወ/ሮ መድሃኒት የቀጣይ መዳረሻቸው የት ነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ በትምህርቱ ዘርፍ የላቀ ደረጃ ለመድረስ እቅድ እንዳላቸው ነው የተናገሩት፡፡ አሁን ያሉበትን የትምህርት ደረጃ ወደ ፒ.ኤች. ዲ ማሳደግ ነው ህልማቸው፡፡ መንግስት ተጨማሪ ኃላፊነት የሚሰጣቸው ከሆነም ህዝብንና ሀገርን ለማገልገል ደከመኝ እንደማይሉ በመግለጽ። ሌላው በህይወታቸው ማሳካትና ማድረግ የሚሹት የበጎ አድራጎት ተግባር ላይ መሰማራት ነው፡፡
ለትርፍ የሚቋቋም ሳይሆን ወላጅ አልባ የሆኑ ህጻናትና ሴቶች የሚደገፉበት፣ ጠዋሪ ያጡ በየጎዳናው የወደቁ የእድሜ ባለጸጋዎች አሰባስበው ድጋፍ የሚያደርጉበት ተቋምን መስርተው የማየት ትልቅ ህልም እንዳላቸው ነው የገለጹት። “በኔ መኖር ውስጥ ለሌሎች የመኖር ምክንያት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ይህ በህይወቴ ስኖር ትልቁ የህይወት እርካታና ስኬት አድርጌ የምወስደው የበጎ አገልግሎት ተግባራዊ ሲሆን ነው” ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ ባህላዊ ተጽእኖዎችን አልፈው ስኬታማ ሴት ወጣት መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ለሌሎች ሴቶች ምን መልዕክት አለዎት? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡- “በሴቶች ላይ ባህላዊና ማህበራዊ ተጽእኖዎች አሉ፡፡ ተጽእኖው ደግሞ ተማሩ በተባሉ ጭምር መንጸባረቁ የችግሩን ስፋት ያጎላዋል፡፡
መጠኑና ይዘቱ በተለያዩ ቦታዎች ይለያያል፡፡ እንደ እድገት ደረጃችንም ይለያያል፡፡ ለዚህ ግን ተሸናፊ አለመሆን ከሴቶች ይጠበቃል፡፡ ለራስ ከራስ በላይ እንደሌለ መገንዘብ ይገባል ይላሉ፡፡ ከራሷ በላይ ለሴቷ የሚያስብ ስለሌለ መፍትሄ አምጭዎቹ እራሳቸው ሴቶች ሊሆኑ ይገባል፡፡ እኔ የመፍትሄው ባለቤት እራሴው ነኝ ማለት ይገባታል፡፡ መሪነት ላይ ያለች ሴትም በልዩ መልኩ ተጽእኖ አለባት። እኔም ተጽእኖው ቢለያይም ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለት አልችልም፡፡ መፍትሄ እንዲያመጣ ሌላውን አካል መጠበቅ አይገባም። በየአመቱ የሴቶች ቀን ከማክበር በዘለለ የሴቶች መብት እንዲከበር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ