በአንዱዓለም ሰለሞን
ለዛሬ በዚህ አምድ ተሞክሮውን ያካፈለን ወጣት ተስፋ ጽዮን ንጉሴ፣ ትውልድና ዕድገቱ በአርቤጎና ወረዳ፣ ያዬ ከተማ ነው። ብዙም ሳይቆይ፣ ገና የሁለት ዓመት ልጅ ሳለ፣ ቤተሰቦቹ በስራ ምክንያት ወደ ይርጋለም ከተማ በመዛወራቸው፣ እሱም ኑሮውን በዚያው አደረገ፡፡ ለኪነ ጥበብ የተለየ ፍቅር እንዳለው የተገነዘበው፣ ገና በልጅነቱ ትምህርት ቤት ሳለ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን የጀመረውና በትምህርት ቤት የቀጠለው የጥበብ ተሰጥኦውም፣ በከተማው በነበረ አንድ ክበብ ጎለበተ፡፡ ተስፋ ጽዮን ስለ ሁኔታው ሲያስታውስ፡ “ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ፣ ግጥም በመጻፍ ትምህርት ቤት ሰልፍ ላይ አቀርብ ነበር፡፡ በትምህርት ቤታችን ባለው የጸረ ኤድስ ክበብ ጥሩ ተሳትፎ አደርግ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ በአንድ ወቅት ሀላባ ለስልጠና ተልኬያለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ የወላጆች ቀን፣ ለእኔና ለመሰል ጓደኞቼ ትልቁ መድረካችን ነው፤ ወላጆቻችን ፊት ተሰጥኦአችንን የምናሳይበት” ነው ይላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተከሰተው አንድ አጋጣሚ ተሰጥኦውን የሚያሳድግበትን እድል ፈጠረለት፡፡ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ፣ እርሱና የክበቡ አባላት ለወላጆች ቀን በዓል “እፀ በለስ” የሚል ድራማ አዘጋጁ፡፡ ድራማውን ለማየት ከትምህርት ቤቱ አጠገብ የነበረው የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ የስነ ጽሁፍ ክበብ አባላት ታድመው ነበር፡፡ ድራማው በተመልካች በመወደዱ እንዲደገም ተጠየቀ፡ ፡ በዚህ የተነሳ፣ ከሳምንት በኋላ በቤተሰብ መምሪያ አዳራሽ ድራማውን በድጋሚ አሳዩ፡ ፡ ይህ ደግሞ ቤተሰብ መምሪያ እንዲገቡ ምክንያት ሆናቸው፡፡ ወጣት ተስፋጽዮን ከትምህርቱ ጎን ለጎን የቤተሰብ መምሪያ የኪነ ጥበብ ቡድንን በመቀላቀል ተሳትፎ ማድረጉን ቀጠለ።
መጀመሪያ ላይ በድራማ ነበር የሚሰራው። በሂደት ግን ሙዚቃውንም ውዝዋዜውንም ከሞከረ በኋላ ትኩረቱን ውዝዋዜ ላይ አደረገ። በ1999 ዓ/ም፣ የመጀመሪያው የኢትጵያን አይዶል ውድድር ሲደረግ፣ ከተወሰኑ የቡድኑ አባላት ጋር በመሆን በውዝዋዜ ተሳተፉ። በወቅቱ ስላጋጠመው የማይረሳ ገጠመኝ አስመልክቶ እንዲህ በማለት ሁኔታውን ያስታውሳል፡ “የመጀመሪያውን ውድድራችንን ሀዋሳ፣ በሲዳማ ባህል አዳራሽ ነበር ያደረግነው። ውድድሩ ልምድ ያገኘንበት ነበር፡፡ እስከ አምስተኛ ዙር ድረስ ደርሰን ነበር፡፡
ከምንም በላይ የማልረሳው ግን አዲስ አበባ በተደረገው ሁለተኛው ዙር ውድድር ስራችንን ስናቀርብ ዳኞቹ ቆመው ነበር ያጨበጨቡልን። ባቀራረባችን በጣም ተደንቀው ነበር፡፡ “በወቅቱ ውዝዋዜውን የሰራነው ወንድማገኝ አርጋው በተባለና ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ይሰራ በነበረ ድምጻዊ ሙዚቃ ነበር፡፡ አጋጣሚ ከዳኞቹ መካከል ሁለቱ የሙዚቃው ክሊፕ ላይ በውዝዋዜ ተሳትፈው ነበር፡፡ እነርሱ ክሊፑ ላይ ከሰሩት ሥራ አንጻር በማየት ነበር ለእኛ አድናቆታቸውን የገለጹልን። እኛ ቱባ ባህሉን መሰረት በማድረግ፣ ትክክለኛውን ባህላዊ ልብስ ተጠቅመንና የጸጉር አሰራሩን በአግባቡ ጠብቀን ነበር ውዝዋዜውን የሰራነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ ባህላዊ አልባሳት የገዛልን በመሆኑ ጠቅሞናል፡፡ እንደየጭፈራው ዓይነት (ፋሮ፣ ቄጤላ እና ሀኖ) የተለያዩ አልባሳትን ተጠቅመን ነበር ሥራውን የሰራነው” በማለት ተናግሯል፡፡ በውድድሩ እስከ አምስተኛ ዙር ለመዝለቃቸው ባህሉን ተረድተውና ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው እንደጠቀማቸው የሚገልፀው ተስፋፅዮን፣ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ያጋጠመውንና የማይረሳውን አንድ ገጠመኙን እንዲህ አውግቶኛል፡ “አዲስ አበባ ለውድድር በምንሔድበት ጊዜ ቢያንስ ለሳምንት እንቆያለን፡፡ በቆይታችን ብር ስለማይበቃን፣ አልጋ የምንይዘው ለሁለት ተዳብለን ነበር፡፡ እኔ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ነበር አልጋ የምይዘው፡፡ ባለቤቶቹ ግን ሁለት ወንድ አንድ ላይ ማደር አይችልም በማለት ከለከሉን። በዚህ የተነሳ ለቀጣዩ ዙር ውድድር ስንሔድ አንድ ዘዴ መዘየድ እንዳለብን ተሰማን፡፡ ጓደኛዬ የእናቱን ድርያና ሻሽ ይዞ በመሄድ፣ ወደ አልጋ ቤቱ ልንገባ ስንል ይህን ልብስ በመልበስ ሴት መስሎ አብረን መግባት ጀመርን፡፡
አንድ ቀን ግን ጓደኛዬ ከውስጥ የለበሰውን ጅንስ ሱሪ ሳያወልቅ ረስቶ ድርያውን በላዩ ለበሰው። አልጋ አከራዩ ተጠራጥሮ ፈተሸና ማታለያችን ታወቀብን፡፡ ያም ሆኖ፣ ባለቤቶቹ ሁኔታችንን በመረዳት ነገሩን ቀለል አድርገው አለፉት። ከዚያ በኋላም ቤተሰብ እስከመሆን ደረስን፡፡”
ወጣት ተስፋጽዮን፣ ከቤተሰብ መምሪያ የለቀቀው፣ በ2007 ዓ/ም ወደ ሀዋሳ በመምጣትና “ወሊማ ባንድ” ን በመቀላቀል ነበር፡፡ የባንዱ አባል መሆኑ ለስራው የተሻለ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረለትና ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመገናኘት ልምድ ለመቅሰም እንዳስቻለው ይገልጻል፡-
“ቤተሰብ መምሪያ ሳለሁ በአንድ ኪ – ቦርድ ብቻ ነበር ሙዚቃ የምንጫወተው፡፡ እዚህ ግን በሙሉ ባንድ ታጅበን ነው የምንሰራው፡፡ ይህ በራሱ አንድ ለውጥ ነው፡፡ ከሲዳማ ብሔረሰብ ባሻገር የሁሉንም ክልሎች ባህላዊ ጭፈራና ውዝዋዜ እንሰራለን፡፡ ከብሄራዊ ቴአትር ቤት የመጡ ባለሙያዎች የሰጡንን የአንድ ወር ስልጠና ጨምሮ፣ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደናል፡፡ በሀዋሳም ሆነ ከሀዋሳ ውጪ የተለያዩ መድረኮች ዝግጅቶቻችንን የማቅረብ ዕድል አግኝተናል፡፡ ይህ ደግሞ የበለጠ ልምድ እንዳገኝና ብዙ ነገሮችን እንዳውቅ ረድቶኛል። ሰላሳ ዓመታትን ባስቆጠረውና በርካታ ባለሙያዎችን ለማፍራት በቻለው በዚህ ባንድ አባል በመሆኔ ዕድለኛ ነኝ” ብሏል፡፡ ከባንዱ አባላት ጋር በመሆን በተለያዩ መድረኮች ላይ ሥራውን ከማቅረቡ ባሻገር፣ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፖች ላይ ተሳትፏል፡፡ ከዚህ አንጻር በቀጣይም የሚሰራቸው ስራዎች እንዳሉ አጫውቶኛል፡፡ አሁን ላለበት ደረጃ ለመብቃት ብዙ ውጣ ውረዶችን በትዕግስት ማለፉን የሚናገረው ተስፋጽዮን ሌሎች ወጣቶችም ይህን በመገንዘብ ተስፋ ባለመቁረጥ ሁልጊዜም መጣርና መትጋት እንደሚገባቸው ሲገልጽም፡-
“ጥበብ ነገሮችን በተለየ መንገድ ማየት መቻል ነው፡፡ አንድ ሰው ተሰጥኦ እንዳለው ከተገነዘበ እያዳበረው መሄድ አለበት፡፡ እያንዳንዷን ቀን ራስን ለማሻሻል ከተሰራ ካሰቡበት መድረስ ይቻላል፡፡ ይህ ሲሆን ግን ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ የግድ ነው፡፡ ጥበብ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እያንዳንዱ እርምጃ በዚህ መልኩ የሚደረግ ነው” ይላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ያነሳው አንድ ነገርም አለ፡ “የአብዛኞቹ የጥበብ ሰዎች መነሻ ታች ላይ በትምህር ቤቶች አለያም በሚኖሩበት አካባቢ ባሉ ክበቦች ነው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ተሰጧቸውን አሳድገው ነው በሂደት ለታላቅ መድረክ የሚበቁት፡፡ በእኛ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ካሁኑ ጋር ሳነጻጽረው ቅር የሚለኝ ነገር አለ፡፡
በአሁኑ ሰዓት እንደ እኛ ጊዜ ያን ያህል ክበባት የሉም፡፡ ያሉትም ቢሆን እንቅስቃሴያቸው ብዙም ጠንካራ የሚባል አይደለም፡፡ ወጣቶች የፈጠራ ክህሎታቸውን ለማዳበርና ለዕድሜያቸው የሚመጥን መድረክ እንዲያገኙ እንደእነዚህ ዓይነት ክበባት ሊኖሩ ብሎም ሊጠናከሩ ይገባል፡፡ ለእኔና ለመሰል ጓደኞቼ የጠቀመን ይህ ነው፡ ፡ ይህን በመገንዘብም አልፎ አልፎ ወደ ክበባት በመሄድ ልምዳችንን እናካፍላለን፡፡ እኛም ብንሆን የእኛን ታላላቆች በማየት ነው ለዚህ የበቃነው፡፡ ይህን በማድረግ ተተኪዎችን ለማፍራት የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ጥረት እናደርጋለን” በማለት ከተሞክሮው በመነሳት ሀሳቡን አጋርቶናል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው