ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!

በቤተልሔም አበበ

ሰላም!! በዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ለእናንተ ለአንባቢያን ማድረስ የወደድነው ሰሞኑን ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ያገኘውን ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩም ህጻን ሄቨን የደረሰባት አረመኔያዊ እና አሰቃቂ ግድያን የተመለከተ ነው፡፡ ወላጅ እናቷ በማህበራዊ ሚዲያ ቀርባ ጉዳዩን እንዳስረዳቸው፡ ህጻኗ ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈፃሚው ጉዳት ካደረሰባት በኋላ አፏ ውስጥ አሸዋ መጠቅጠቅ፣ የእጁ ጣቱ ጉሮሮዋ ስር እስኪገባ አንቆ በመያዝ ፣ ለጋ ሰውነቷን ከቁጥጥር ውጪ አድርጎ መጠቀም እና አሳዛኝ የልጅ ገላዋን በምላጭ መተልተል፣ ድርጊት ነበር የፈጸመው፡፡ አንዳንዶች ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት ለመፈጸም ሲያቅዱ ጓደኝነትን፣ ጉርብትናን ይዘነጋሉ፡፡ ወደ አውሬነት ይቀየራሉ፡፡ እንዲህ አይነት ወንጀል ፈጻሚዎች በሀገራችን ብቅ ማለት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል፡፡

ድርጊቱ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰራጨ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎች ሀዘናቸውን ሲገልጹ ተስተውሏል። በርካቶችም ድርጊቱን አውግዘውታል፡፡ የህግ ባለሙያዎችም በህጉ ዙሪያ ማሻሻያ ሊደረግ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የልጅነት ጊዜዋን ገና በወጉ ቦርቃ ያልጨረሰችው ሄቨን በጠዋቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወቷን ተቀምታለች ፡፡አረመኔያዊ እና ነውር አልባው ድርጊት በሄቨን ብቻ አላበቃም፡፡ ተገቢውን ፍትህ ለማግኘት በምታደርገው እንቅስቃሴ በእናቷም ላይ ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰባት የመኖሪያ አድረሻዋን በተለያየ ጊዜ ተቀይራለች። በስጋት ውስጥ እንዳለችም ነው የተናገረችው። ብዙን ጊዜ ወንጀለኞች እጀ ረዥም በመሆናቸው በህግ የሚሰጡ ውሳኔዎች ፍርደ ገምድል ሲሆኑ ይስተዋላሉ፡፡በዚህም የቅጣት ህጉ አስተማሪ ሆኖ ባለመገኘቱ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር ይከፍታል፡፡ በተለይ ሀገራችን በሚገኙ ሴቶች እና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እና በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ በመሆኑ በቃ የሚል አካል ሊኖር ይገባል፡፡

ህጻን ሄቨን ላይ የደረሰባት አሰቃቂ ድርጊት በማህበራዊ ሚዲያ ሲወጣ ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም ጫፍ በርካታ ንቅናቄን ፈጥሯል። ይሁን እንጂ በቅርብ ቤተሰቦቻቸው ቤት ተዘግቶባቸው በተደጋጋሚ እየተደፈሩ ለሚማቅቁ እና ለሚሞቱ ህጻናት ሄቨን ስሟን በደሟ ጽፋ ለሌሎች የአብዮት ፊደል በመሆን የተዳፈነውን ፍትህ አልባ ድርጊት ምክንያት ሆናለች፡፡

በየቤቱ በሴት ህጻናት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች በየጊዜው መልካቸውን እየለወጡ የሚከሰቱ ከሀይማኖት፣ ከባህል እና ከሞራል አኳያ ሲቃኙ ያሉንን እሴቶች የሚሸረሽሩ እኩይ ተግባራት ናቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን በችግርም ሆነ በደስታ ጊዜ ያለን ማህበራዊ መስተጋብር ፣ ደግነትና መደጋገፍ ባይሸረሸርም ነገር ግን ነውራችንም በዛው ልክ እየተስፋፋ በመሆኑ ዞር ብለን መልካም ነገሮቻችንን መመልከት ብንችል የተጣመሙ እና የተበላሹ የሚመስሉ ነገሮቻችንን ለማስተካከል በጥቂቱም ቢሆን ይህ ሰሞነኛ ጉዳይ እድል የሚሰጠን ይመስለኛል፡፡

ሴት ልጅ ላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀል ደረሰባት ሲባል እንኳን ፣ የት? ምን ለብሳ ነበር? እንዴት ተደፈረች? የሚለውን ካደመጡ በኋላ ቅድመ ሁኔታውን ያመቻቸችው እራሷ ናት የሚል ድምዳሜ የሚሰጡ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ በመሆኑም እንዴት አንድ ሴት በአለባበሷ ጥቃት እንዲደርስባት ትዳረጋለች የሚለውን ለአንባቢያን እተወዋለሁ፡፡

እንስቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች ጉዳትን ያስተናግዳሉ፡፡ ለአብነትም በጎዳና ተዳዳሪነት በየአካባቢው የሚኖሩ ሴቶች በሚደርስባቸው የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ድርጊት በብዙ ነገር ተጎጂ ከመሆን ባለፈ የሚፈጠረው ዜጋ የማንነት ቀውስ እንዲገጥመው ያደርጋል፡፡ ቀን ጎድሎባቸው ጎዳና ላይ የወደቁ እናቶች ፣ እህቶች እና ህጻናት ብዙ ጥቃት እንደሚገጥማቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጾታዊ ጥቃት ከቤተሰብ ወይም ከቅርብ ሰው ጀምሮ ሊፈጸም ይችላል፡፡

እንዲሁም አንዳንድ ሴቶች በሚሰሩበት ተቋም የያዙትን ስራ ላለማጣት እና የእለት እንጀራቸውን ለማግኘት ብሎም የቤተሰብ ሀላፊነትን በተገቢው ለመወጣት በሚያደርጉት ጥረት በቢሮ አለቆቻቸው ዘንድ ጾታዊ ጥቃትን የሚያስተናግዱ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

በተመሳሳይ በአንዳንድ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በኩል ከውጤት አሞላል ጋር በተገናኘ የሴቷን ውጤት ሆነ ብሎ በማበላሸት ያለፍለጎቷ ከመምህራን ጋር እንድትተኛ የምትደረግበት አግባብ በየወቅቱ የሚዲያ ፍጆታ ቢሆንም ውጤት አላመጣም። በፍትህ በኩል የውሳኔ አሰጣጥ ግድፈቶች ገዝፈው በመታየታቸው አንዳንድ ግብረ ገብ የጎደላቸው ወንዶች ክንዳቸውን በመጠቀም ህጻናት ላይ ጾታዊ ጥቃቶች ያደርሳሉ፡፡ ይህ እየሆነ ያለው በሀገራችን እየተተገበረ የሚገኘው ህግ አስተማሪ ባለመሆኑ እና በሚመለከታቸው አካላት ዘንድ በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ ነው፡፡ ትኩረት አግኝቶም ባለመሻሻሉ ነው፡፡

ይህ ደግሞ ማህበራዊ እሴቶቻችንን ጥላሸት የሚቀባ ነው፡፡ ሴት ልጆች በስነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ጎረቤት ሀላፊነቱን እንዳይወጣ የሚያደርጉ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ወይም መተማመንን የሚያሳጡ ጉዳዮች መከሰት ጀምረዋል። በተቃራኒው ደግሞ አርአያ በመሆን የጎረቤትን ልጅ ከራሳቸው ልጆች እኩል በመመልከት ሲያጠፉ ተገቢውን ቅጣት በመስጠት ለትልቅ ደረጃ ያበቁ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ የነበሩንን መልካም እሴቶች ለማሳደግ የሚፈጠሩ እኩይ ተግባራት በማህበረሰብ በኩል ጥርጣሬን እንዳይጭሩ ሁሉም በያገባኛል መንፈስ ጥቃቶችን ሊከላከል ይገባል፡፡

በሀገራችን ሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም፡፡ በተለይ የሰላም እጦት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የጥይት እና የፍትወት ማብረጃ መሳሪያም ሆነዋል ህጻናት። በሴቶች እና በህጻናት ላይ የሚደርሱ የወንጀል ድርጊቶች እንዲቆሙ የህግ ክፍተቶች ታይተው እርምት ቢደረግባቸው፣ ወንዶች ልጆችን ቤተሰብ በስነምግባር እና በሀይማኖት አንጾ እንደሚያሳድግ ሁሉ ሴቶችም በእንክብካቤ ፣ በጥበቃና በስስት እንዲያድጉ ማድረግ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍሔ ሊሆን ይችላል፡፡ የህጻናት እና የሴቶች ጉዳይ ንቅናቄው ጥሩ ቢሆንም ዘመቻው የአንድ ሰሞን መሆን የለበትም፡፡ ሰላም!