“መሸነፍ አልፈልግም” – ወ/ሮ ጀሚላ መሀመድ

በገነት ደጉ

ሰዎች ላይ በብዙ መንገዶች የአካል ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ በተፈጥሮም ሆነ በአደጋ ምክንያት ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡

ወ/ሮ ጀሚላ መሀመድ ተወልደዉ ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ልዩ ስሟ ቆሬ ተብሎ በሚጠራው ከተማ ሲሆን አሁን የሚኖሩት ደግሞ ሻሸመኔ ነው፡ ፡ የአካል ጉዳቱ ሲወለዱ ሁለት እግሮቻቸው ጤናማ እንዳልነበሩ ከቤተሰቦቻቸዉ መስማታቸዉን ነዉ የነገሩን፡፡

ስለ አካል ጉዳተኝነት ምንም ዓይነት ግንዛቤ ባልነበረበት ወቅት ገጠር አካባቢ ነው የተወለዱት። በተለይም በሚኖሩበት ማህበረሰብ ዘንድ ለአካል ጉዳተኞች ያለው ግንዛቤ የተሳሳተ መሆኑ በብዙ እንደጎዳቸዉ ጠቁመዉ ከዚህ ጫና ወጥተዉ ዛሬን ማየት መቻላቸዉ ልዩ ደስታ እንደፈጠረላቸዉ ገልፀዋል፡፡

ወ/ሮ ጀሚላ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ቦርድ አባል ሲሆኑ እንደ ኦሮሚያ ክልል ደግሞ የአካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም ለአካል ጉዳተኞች እንዲህ ያለ እድል እንዳልነበረ የጠቆሙት ወ/ሮ ጀምላ ብዙ ነገሮች የተገደቡ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ በተጽዕኖ የሚኖሩበት አስተሳሰብ ተለዉጦ ዛሬ ለአካል ጉዳተኞች ድምጽ መሆን መቻላቸዉን በኩራት ይናገራሉ፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ቆሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ነው የተከታተሉት፡፡ ወደ 9ኛ ክፍል ካለፉ በኋላ በአካባቢው የ9ኛ ክፍል ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ሻሸመኔ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ “በሻሸመኔ ጮራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” መከታተላቸውን ነው ያጫወቱን፡፡ በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ ሊያስገባቸው የሚችል ውጤት ባለማምጣታቸው እዛው ሻሸመኔ በሚገኘው ኮሌጅ በ“አይሲቲ” ዲፕሎማቸውን ተከታትለው መመረቅ ችለዋል።

“አካል ጉዳተኛ ነኝ ብዬ ለነገሮች መሸነፍን አልፈልግም” የሚሉት ወ/ሮ ጀሚላ. በዲፕሎማ እዛው ሻሸመኔ የመንግስት ስራ ተቀጥረው እየሰሩ ጎን ለጎን ለነገ ህይወትን የተሻለ ለማድረግ በሶሶሎጂ የትምህርት ክፍል ሻሸመኔ ሪፍት ቫሊ ኮሌጅ በመጀመሪያ ዲግሪ በጥሩ ውጤት መመረቃቸውን ነው ያስረዱት፡፡

ባለትዳር እና የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ጀሚላ አካል ጉዳተኛ በመሆናቸወ ትዳር ከመያዝና ቤተሰባቸውን ከማስተዳደርም ሆነ ወልዶ ከመሳም እንዲሁም ልጆቻቸውን ከማሳደግ ምንም እንዳላገዳቸው ነው ያጫወቱን፡፡

ከመደበኛው ስራቸው ባሻገር በአትሌቲክሱም ዘርፍ ጎራ ማለት ስለመቻላቸው ያጫወቱን ወ/ሮ ጀሚላ “ኦል አፍሪካ ጌም” ወክለው አልጀሪያ ላይ በተደረገው ውድድር በዊልቸር ሩጫ ያሸነፉ ሲሆን በወቅቱም ለብዙ አካል ጉዳተኞች ሞዴል መሆን ስለመቻላቸው ነው ያስረዱን፡፡

በተለይም አዲስ አበባ እና አዳማ አካል ጉዳተኞች በብዛት የሚገኙ ቢሆንም እርሳቸው ከገጠሩ አካባቢ አካል ጉዳተኞችን ወክለው ለስልጠና ይመላለሱ እንደነበርና እዛው ላሉት አካል ጉዳተኞችም መነቃቃትን እንደፈጠሩ ነው የተናገሩት፡-

“በተፈጥሮዬ በራስ መተማመን አለኝ፡፡ አካል ጉዳተኛ ነኝ ብዬ ወደ ኋላ የምለው ምንም ነገር አልነበረኝም፡፡ ብዙ ሰዎች በዚህ ተፈጥሮዬ ይገረሙ እና ይደነቁም ነበር፡፡ ትልቁ ነገር ለእኔ እችላለሁ ብሎ አዕምሮን ማሳመን ነው ያሉት ወ/ሮ ጀሚላ፣ ባላሰቡት ባላቀዱት ነገር ዓላማ ማሳካት ግን አይቻልም ይላሉ”

ባለቤቴ ጉዳት አልባ ነው ያሉት ወ/ሮ ጀሚላ በብዙ ነገር ከጎናቸው በመሆን እንደሚያበረታቷቸው እና ትችያለሽ እንደሚሏቸው ነው ያጫወቱ፡-

“ትልቁ ነገር አካል ጉዳተኛም ወይም ጉዳት አልባ መሆኑ አይደለም፡፡ የደረስኩበት ደረጃ ለእኔ ጀሚላ ማለት ማናት የሚለውን ምላሽ የሚሰጥ ነው ብዬ አስባለሁ” ይላሉ፡፡

በተለይም በዚህ ዘመን ጉዳት አልባ ሆኖም የራስ ተነሳሽነት የሌለው ተፈላጊ ሊሆን አይችልም። ከዚህም አንፃር ወ/ሮ ጀሚላ አካል ጉዳተኛ ሆነው የራሳቸውን ቤት በአግባቡ የመምራት፣ ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መገኘታቸው ለሌሎችም የሚያስተምር ነው።

ዋናው ነገር ማንም ስለደገፈኝ ሳይሆን ለዛሬው ስኬት ለመድረሴ ትልቁን ቦታ የምትይዘው ጀሚላ እና ጀሚላ ብቻ ነኝ በማለት ለራሳቸው ጥረት አውቅናውን ሰጥተዋል፡፡

እንዲህ ማለትን የመርጥኩት በህይወታችን ቆራጥ እና ጠንካራ ከሆንን የማይቻል አንድም ነገር የለም በሚል ነው፡-

“ብዙ አካል ጉዳተኞች መንገድ ላይ ክራንች ይዘው ሲለምኑ ሳያቸው በጣም ነው የምበሳጨው፡ ፡ የጎደለን አንድ አካል ነው እንጂ ሁሉም አካላችን ባለመሆኑ ሰርተው መለወጥ ሲችሉ ግን በየመንገዱ ሰዎችን ማስቸገር እንደሌለባቸው ነው የማምነው።

“ይህ ሙሉ በሙሉ እንዲቀረፍ ወደ ተሻለ ደረጃ የደረስን አካል ጉዳተኞች ለሚለምኑት ጥሩ አርአያ ልንሆን ይገባናልና ሰዎች ዛሬ ለራሳቸውም ተቸግረው በኑሮ ውድነት ውስጥ በሚኖሩበት ወቅት ማንንም ሳናስቸግር እራሳችንን እና ቤተሰቦቻችንን መቻሉ መልካ ነው፡፡

“ልጅ ማሳደግ ለማንኛውም ሰው የሚከብድ ሲሆን በተለይም አካል ጉዳተኛ ሲሆኑ ደግሞ እጅግ ፈታኝ ይሆናል፡፡ ያም ሆኖ እችላለሁ የሚል መንፈስ ስለነበረኝ እና ለማንም እጅ መስጠት ስላልፈለኩ ከህይወት ጋር መጋፈጥን መርጫለው፦

“አሁን ላይ የመጀመሪያ ልጄ የ12 ዓመት ልጅ ሲሆን በህፃንነቱ በአንድ እጄ ልጄን በአንድ እጄ ክራንቼንና በአንድ እጄ ዋንጫ በመያዝ አሰላ ለይ በነበረው የአካል ጉዳተኞች አትሌትክስ ውድድር ወቅት የተገኘሁበትን መቼም አረሳውም፡፡ በዚህም ብዙዎችንም አስደምሜያለሁ፡፡

“በወቅቱ ወልጄ ስለነበር አልችልም ብዬ መቅረትን አልፈለኩም፡፡ ሜዳሊያ እንኳን ለልጄ ነበር የተደረገለት፡፡ እችላለሁ ብዬ ሄድኩ በቴብል ቴንስ ስፖርት ተወዳድሬ ወርቅ አመጣሁ፡፡ በወቅቱ እጅግ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡

“በሀገራችን ብዙውን ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ስፖርት ላይ ግንዛቤው እምብዛም አልነበረም። አበበ ቢቂላ አካል ጉዳተኛም፣ ጉዳት አልባም ሆኖ የሀገራችንን ስም አስጠርቶ ስለነበር በተለይም በዊልቸር ሆኖ ያገኘው ድል ለእኔ ጥሩ አርአያ ሆኖኛል፡፡

“በዚህም የአካል ጉዳተኞች ስፖርት መጠናከር አለበት በሚለው እሳቤ የራሴን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ አሁን አሁን በሀገራችን በወርቁም ይሁን በብሩ የአካል ጉዳተኞች ስፖርት በኦሎሚፒኩም ውጤታማ በመሆናችን ኩራት ይሰማኛል፡፡

“በወቅቱ እኔ ችግር ውስጥ ሆኜ ባልወዳደር እና ዋጋ ባልከፍል ዛሬ ላይ ያለውን የአካል ጉዳተኞችን ስፖርት አላይም ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ብዙ አካል ጉዳተኞች እየወጡ ስለሆነ ዛሬ ብሞትም ደስተኛ ነኝ ምንም አይመስለኝም”፡፡

“በኢትዮጵያ የቦርድ አመራር ለመሆን ዕድሉን በማግኘቴ እና በመላው ሀገራችን ላሉት አካል ጉዳተኞች ድምጽ መሆን መቻሌ ትልቅ እድል ነው፡፡ ከዚህም በላይ ስኬት የለምና ከራስ አልፎ ለሌሎች ድምጽ መሆን እንዴት ደስተኛ እንዳደረገኝ ልገልጽ አልችልም፡፡

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአካል ጉዳተኞች በፈጠረው የአጀንዳ ልየታ መድረክ ላይ አግኝተን ለአካል ጉዳተኞች ያለው ጠቀሜታው ምን ይመስል ነበር? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ምላሻቸው ይህ ነበር፡-

“መንግስት ሁሉንም ማህበረሰብ ይመለከተዋል ብሎ ወደ መድረኩ ማምጣት መቻሉ ትልቅ ጅምር ስራ ነውና የሚመለከተው አካል ሁሉ ለውጤቱ ድምፁን ማሰማት አለበት የሚል ጽኑ እምነት አለኝ”

ቀድሞ መንግስት የሚፈልገውን ሰው መርጦ ይወስድ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ሁሉን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሳታፊ መሆን መቻሉ ነገ ላይ ለምናመጣው ውጤት ወሳኝ እና ጉልህ ድርሻ እንዳለው ነው የገለፁት፡-

“ከየክልሎች ከመጡ አካል ጉዳተኞች ጋር እርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ማድረግ መቻላችን በራሱ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው። የመጣንበትም ዓላማ አንድ ስለሆነ፣ አንድ ላይ ተገናኝተን ስናወራ እንደ ሀገር አንድ እንድንሆን የሚያደርግ ነው” ያሉ ሲሆን፣ ይህ የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁላችንንም ርብርብ ይጠይቃል የሚለው ደግሞ መልዕክታቸው ነው፡፡