በገነት ደጉ
ወባን መከላከል ቀላል መስሎ ቢታይም ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ በሽታ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ወባ በየሁለት ደቂቃዎች አንድ ህፃን ሲገድል በየዓመቱ ከ2 መቶ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በወባ ይያዛሉ።
በሽታን ከመከላከል አንፃር ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ ለውጦች ቢመዘገቡም እ.አ.አ ከ2015 ወዲህ ግን ወደፊትም ወደ ኋላም እየሄድን አይደለም ይላል ያለፈው ዓመት የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት፤ ቁጥሩ ባለፉት ሶስት ዓመታት ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳላሳየ በማመልከት፡፡
ወባ ዛሬም መከላከል ሲቻል የሰው ህይወት ከሚቀጥፉ ግንባር ቀደም በሽታዎች ተርታ አልወጣም። የዓለም የጤና ድርጅት በወባ በሽታ ላይ የሚያደርገውን የመከላከል እና የመቆጣጠር እርምጃ ለማጠናከር እንደሚሻ ዘንድሮም ለዓለም አሳውቋል።
ወባን ለመዋጋት የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱም በሽታውን ለመከላከል የሚሠራውን ሥራ ህብረተሰቡ በባለቤትነት ሊይዘው ስለሚገባ፡፡ ስለሆነም ወባን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርም ሆነ ለማጥፋት የሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ወባን ከነጭራሹ ለማጥፋት ህብረተሰብን ያሳተፈ እንቅስቃሴ መኖር አለበት፤ ይህ ደግሞ ዘመቻው በህብረተሰቡ ባለቤትነት መያዝ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ቤተሰብም ሆነ ግለሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚያስፈልግ መረጃዎች ያትታሉ።
የወባ ትንኝ ለመራባት ሞቃት አካባቢ እና እርጥበት እንደሚያስፈልጋት ነው የሚነገረው።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ውስጥ በዝናብ ወቅቶች ማለቂያ ላይ የብዙ ሰዎች በወባ የመያዝ ዕድል ሰፊ የሚሆነው።
እኛም የክረምት ወራትን ተከትሎ ለወባ መራባት በአብዛኛው ክልሎች ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው በቅድመ መከላከሉ ላይ ምን እየተሰራ ነው? ስንል ከደቡብ ኢትጵያ እና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ፣ የወባ በሽታ እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር በፍጥነት እንደጨመረ በመጠቆም፣ ከተለዩት ክልሎች መካከል አንዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስለመሆኑ ነው የገለፁት።
ይህንንም በተመለከተ በሰኔ ወር አጋማሽ በሚዛን አማን ከተማ ላይ የፓርላማ አባላት ባሉበት እስከ ታህሳስ 30 ድረስ በየሳምንቱ ለመገምገም ለኮሚቴው አቅጣጫ ተሰጥቶት እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው ያስረዱት፡፡
እንቅስቃሴው በሁሉም ክልሎች ላይ ያለ ሲሆን በየሳምንቱ ሰኞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ከፌዴራል ጋር ስራዎች እንደሚገመገሙና አቅጣጫ እየተቀመጠለት ስለመሆኑ ያስረዱት የቢሮው ኃላፊው፣ እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በየሳምንቱ ሁሉም የማናጅመንት አባላት በተገኙበት አፈፃፀሙ እንደሚገመገም ገልፀዋል፡፡
እንደ ሀገር 222 ወረዳዎች እንደ ደቡብ ክልል ደግሞ 18 ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ የወባ በሽታ ጫና ያለባቸው ወረዳዎች የተለዩ ሲሆን የተመረጡት 18 ወረዳዎች የመጀመሪያ ሳምንት ላይ 63 በመቶ የወባ ሽፋን ያለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ባሻገር 3 በጣም ጫና ያለባቸው ወረዳዎች ተጨምረው 21 ወረዳዎች ላይ ግብረ ሀይሉ እየተንቀሳቀሰ በ2ኛ ሳምንት 64 በመቶ ጨምሮ የነበረው ስርጭቱ በቀጣዮቹ ተከታታይ ሳምንታት ሲገመገም ወደ 49 በመቶ ዝቅ ማለቱን የጤና ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
መሻሻሎች ቢኖሩም ቀጣይ ብዙ የሚሰሩ ስራዎች እንደሚጠብቃቸው ያስረዱት ኃላፊው፣ እንደ ክልል ምንም ዓይነት የመድሀኒት አቅርቦት ችግር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ያም ሆኖ ጤና ኬላዎች ላይ የአቅርቦት ውስንነቶች ስለመኖራቸው ነው ያስረዱት፡፡
አሁን ላይ በርካታ ጤና ጣቢያዎች በመከፈታቸው የመድሀኒት እና የመመርመሪያ መሳሪያ እየተላኩ ሲሆን የሰዎች ሞት ቢቀንስም እንኳን የስርጭት መጠኑ የዚህን ያህል ቀንሷል የሚባል አለመሆኑን ነው አቶ እንዳሻው የጠቀሱት፡፡
የመድሀኒት ፈንድ የአርባ ምንጭ እና የሀዋሳውን ማዕከል እንዲሁም የፌዴራል ተቋምን ጨምሮ በየሳምንቱ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚገመገም የተናገሩት አቶ እንዳሻው፣ ጎን ለጎን በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሙሉ በሙሉ የወባ መከላከያ ርጭት ስለመደረጉ ገልፀዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው እንዳሉት በተለይም በወረዳዎች አካባቢ ቅድመ መከላከሉ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ በመሆኑ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የሚዲያ አካላት በጋራ እንዲሰሩ የማስተሳሰር ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል፡፡
በተለይም ዞን አመራሮች እና የፓርቲ ኃላፊዎችን ጨምሮ በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራው የንቅናቄ መድረክ በማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ የሚመራ ሲሆን እስከአሁንም ከባዱ ጊዜ ገና ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሰራሩን እስከታችኛው መዋቅር መዘርጋት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የወባ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ በጤናው ሴክተር መስሪያ ቤት ብቻ ውጤት ማምጣት እንደማይቻልና ትኩረት ካልተሰጠው ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችልም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
የወባ በሽታን ከመከላከል አንፃር በተለይም አጎበር አጠቃቀም ላይ ያለው ችግር አስከ አሁንም ያልተቀረፈ ስለመሆኑ ያስረዱት የቢሮው ኃላፊው፣ ከመቶ ሰው 58 ሰው ብቻ አጎበር እንደሚጠቀም ነው የገለፁት፡፡
በማህበረሰቡ ላይ ከአጎበር አጠቃቀም ጋር ያለው መዘናጋት በተለያዩ አማራጮች እና ሚዲየሞችም ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አጎበር መጠቀም እንዲችሉና በሽታው ከያዛቸው ግን በወቅቱ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ህክምናውን በአፋጣኝ ማግኘታቸው አስፈላጊ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ለአካባቢው ህብረተሰብ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የመኖሪያ አካባቢያቸውን በማጽዳት፣ በማፋሰስና በማዳፈን ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ እንዳሻው፣ በተመረጡ አካባቢዎች መረጃ በየዕለቱ በመውሰድ ለሚመለከታቸው አካላት በማድረስ ረገድ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡ የወባን በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት የባለ ድርሻ አካላት እና የማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆናቸውን አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍሰሀ ለመንጎ፣ በክልሉ የወባ በሽታ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ስለመጨመሩ ጠቅሰው፣ ከዚህም ቀደም በክረምት ወራት የወባ በሽታ ቁጥር መጨመር የማይታሰብ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ነገር ግን፤ በክረምቱ ወራትም ከጊዜ ወደ ጊዜ ስርጭቱ እየጨመረ ስለመምጣቱ ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ የወረርሽኙን ያህል ጉዳቱ የከፋ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
በተለይም በዚህ ወቅት ከአየር መዛባት ጋር ተያይዞ የመጣው ጫና እና ከወባ ትንኝ ባህሪ መቀየር ጋር ተያይዞ በጥናትም እስኪረጋገጥ ድርስ እንዲህ ነው ሊባል የማይችል የባህሪ የመቀያየር ሁኔታዎች በስፋት ስለመታየታቸው አመላክተዋል
በዚህ ወቅት ዝናብ እንቁላሉን ጠርጎት ስለሚወስድ እምብዛም የወባ በሽታ ለጉዳት እንደማያጋልጥ ያስረዱት አቶ ፍሰሀ፣ ወባ ቢኖርም እንኳን በዚህን ያህል መጠን እንደማይኖር አያይዘው ገልፀዋል፡፡
በዚህም ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ የወባ በሽታ መስፋፋት ካሳየበት ጊዜ ጀምሮ በተቻለ መጠን በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጤና ቢሮዎች ግብረ ሀይል ተቋቁሞ በቁጥጥር ስር እየዋለ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ ከወረርሽኙ አንፃር በየሳምንቱ ከፌዴራል እና በየቀኑ በቢሮ ደረጃ በመገምገም ከባለድርሻ አካላት ጋር የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል፡፡
በየቀኑ መረጃዎች እየተሰበሰቡ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እየተገመገመ ስለመሆኑ ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ትኩረት ተሰጥቶ በከፍተኛ አመራሮች እየተመራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በተለይ በክልሉ የወባ ጫና ባለባቸው 18 ወረዳዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑ የገለፁት አቶ ፍሰሀ፣ የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚቻለው በህብረተሰቡ ተሳትፎ በመሆኑ፣ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልጋዮች፣ መምህራንን፣ ሀገር ሽማግሌዎችን እና የሀይማኖት ተቋማትን ባሳተፈ መልኩ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የወባ በሽታን መከላከል ስራን ለጤናው ሴክተር መስሪያ ቤት በመተው ብቻ ውጤት ማምጣት ስለማይቻል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አሁን በተጀመረው አካሄድ፣ በጋራ ስራዎችን መስራት አለባቸው የሚለው መልዕክታቸው ነው።
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው