ሀዋሳ፡ ነሐሴ 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገሪቱ የተጀመረው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የችግኝ ተከላ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ሚናው የጎላ በመሆኑ በተሞክሮነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑን ተገለፀ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ችግኞች ተከላ ተካሂዷል፡፡
በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሻ እንደገለፁት በሀገሪቱ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የተጀመረው የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ከመቅረፍ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርዓያነትና በተሞክሮነት የሚጠቀስ ተግባር ነው፡፡
የተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ለታለማላቸው አላማ እንዲውሉ በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በበኩላቸው ችግኝ መትከል የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግና የአካባቢውን ስነ ምህዳር ከማስጠበቅ በተጨማሪ ምቹ ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ ያለው ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በልዩ ወረዳው በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ለችግኝ ተከላ ፕሮግራም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብደላ ጀማል ማህበረሰቡ በችግኝ ተከላው ወቅት ያሳየውን ተነሳሽነትና ፍላጎት የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብና በመጠበቅ እንዲፀድቁ በማስቻል መድገም እንዳለበት ጥሪ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት አመታት በልዩ ወረዳው የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
በልዩ ወረዳው በሱንካ ቀበሌ በተካሄደው በዚህ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ከ22 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን የገለፁት ሃላፊው በዕለቱ በ28 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት 86 ሺህ የተለያየ ዝሪያ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ግብ ተይዞ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁና ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ በልዩ ትኩረት ይሰራል ያሉት ደግሞ የልዩ ወረዳው ደንና አከባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ያቆብ ግርማ ናቸው።
በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉ የልዩ ወረዳው ነዎሪዎች በሰጡት አስተያየት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር 600 ሚልየን ችግኝ ለመትከል የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ በዕለቱ ችግኝ በመትከል ለቀጣይ ትውልድ መተላለፍ የሚችል የራሳቸውን አሻራ ማኖር በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ በመንከባከብና በመጠበቅ እንዲፀድቁ ለማስቻል በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል ፡፡
ዘጋቢ፣ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ