የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ባለፉት ሶስት አመታት በወባ ወረርሺኝ ሳቢያ ተደጋጋሚ ጉዳት በማስተናገዳቸው ለከፍተኛ የጤናና የኢኮኖሚ ችግር መዳረጋቸውን ተናገሩ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቤንች ሸኮ ዞን የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ባለፉት ሶስት አመታት በወባ ወረርሺኝ ሳቢያ ተደጋጋሚ ጉዳት በማስተናገዳቸው ለከፍተኛ የጤናና የኢኮኖሚ ችግር መዳረጋቸውን ገለጹ።
በዞኑ የወባ ወረርሽን እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል።
በቤንች ሸኮ ዞን ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ አሁንም አንገብጋቢ የማህበረሰቡ የጤና ችግር መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በዞኑ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተመስገን መለሰ፣ ወንጌላዊ ጎታብ ኮይካብ እና አቶ ደሳለኝ ኮብቴት እንደተናገሩት ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በአካባቢያቸው በተደጋጋሚ በሚከሰት የወባ ወረርሽኝ ሳቢያ ለከፍተኛ የጤና ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
በተለይ አሁን ላይ በአካባቢው የወባ በሽታ ህክምና ወስደው ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ዳግም እያገረሸባቸው በመሆኑ ተቸግረናል የሚሉት ነዋሪዎቹ ይህም ለከፋ የጤናና የኢኮኖሚ ቀውስ መጋለጣቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በሁሉም አካባቢ የወባ በሽታ በማህበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለው ሞትና ጉዳት ከፍተኛ ሆኗል የሚሉት ነዋሪዎቹ፥ መንግስት የበሽታውን ስርጭት ለመቀልበስ አፋጣኝ ግብረ-መልስ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ምናሴ በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት ሁለት ሶስት አመታት የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለሞትና ለጉዳት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
በዚህ መምሪያው የወባ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የሚያደርሰውን የጤና ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል የመከላከል ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፥ በተለይ በዞኑ በተያዘው አመት የወባ በሽታው ስርጭት መጨመርን ተከትሎ ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጀምሮ ከየደረጃው የተዋቀረ ግብረ ሀይል በመደራጀት እስከ ቀበሌ ተወርዶ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ አሁን ላይ የወባ ወረርሽኝ ምጣኔ 67 ከመቶ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኤልያስ፥ በሽታውን ለመከላከል በዞኑ ባሉት 95 ጤና ኬላዎች፣ 27 ጤና ጣቢያዎችና በ2 የመንግስት ሆስፒታሎች የወባ ህክምና በነፃ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በዞኑ ከዚህ ቀደም በወባ ወረርሽኝ ሆስፒታል መጥተው የሚተኙ ታማሚዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመው፥ ህብረተሰቡ ተደጋጋሚ በወባ በሽታ እንዳያዝ በአካባቢው ወባን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን በተገቢው ከመስራት ባለፈ ፈዋሺነታቸው ያልተረጋገጡ መድኃኒቶችን ከመውሰድ መቆጠብ እንዳለበት አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ