በ2016 የአረንጓዴ አሻራ አካል የሆነው ተራራ የማልማት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ጎላ ቀበሌ ተካሄደ
በዞኑ ዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ከ75 ሚሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉም ተገልጿል።
የጌዴኦ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ታደሰ የ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል የሆነው ተራራ የማልማት ተግባር በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ሀሳብ ጠንሳሽነት የሚከናወን ተግባር መሆኑን እንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ገልጸዋል።
ተራራ የማልማት ተግባር ለሦስት ተከታታይ ዓመት የሚቀጥል ሲሆን ዛሬ ላይ አራት ሺህ ገደማ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን የገለፁት አቶ ዮሐንስ፤ ደን የዓለም ሀብት በመሆኑ ወትሮ ከሚደረገው በላይ ጥበቃና የእንክብካቤ ሥራ በመሥራት የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም መትጋት ያሰፈልጋል ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በዘንድሮ ዓመት በዞኑ እንሰት፣ ቡናና የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ከ75 ሚሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸዋል።
ጌዴኦ ባህላዊ መልከአ ምድር አያያዝን በዓለም በዩኔስኮ ያስመዘገበ ብቸኛ ህዝብ መሆኑንና በቀጣይ የአለም አጥኚዎች የጥናትና ምርምር ለመሥራት እንደሚመጡ የገለጹት አስተዳዳሪው በዞኑ በጎላ ቀበሌ በሚገኘው ተራራ ላይ የተለያዩ ችግኞችን የመትከል መርሀ ግብር አስጀምረዋል።
በቀጣይም በዞኑ በሚገኙ ስምንቱም ወረዳዎች ተራራ የማልማት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ዶ/ር ዝናቡ፤ አሥራ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊየን የተለያዩ ፋይዳ ካላቸው ችግኞች ውስጥ ሦስት ሚሊየን ችግኝ በአንድ ጀምበር እንደሚተከል አስረድተዋል።
የዲላ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታርኩ ታደሰ በጎላ ቀበሌ የሚገኘው ተራራ አሥራ አንድ ነጥብ ሁለት ሄክታር መሬት የሚሸፈን መሆኑን በመግለጽ ዛሬ የተተከሉ ችግኞች 30፣ 40፣ 30 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው ብለዋል።
የአየር ሁኔታ ጥሩ በመሆኑ የጽድቀት መጠኑን ለመጨመር ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ መጠበቅ፣ የእንክብካቤና የድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት አስተዳዳሪው።
አቶ አበበ ጠቀቦ የጎላ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ዛሬ ችግኞች የተተከለበት ቦታ ከዚህ በፊት ለእምነት ተከታዮችም ሆነ ለሌሎች በርካታ ጥቅም እየሰጠ የነበረ ተራራ በመሆኑ በዞኑ ታቅዶ መልማቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ተሰፋዬ ጎበና – ከይርጋ ጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የወባ በሽታ ስርጭት ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ ተጠቆመ
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት