የወሩ ኮኮቦች

የወሩ ኮኮቦች

አሰልጣኝ አርኔ ስሎት እና ጃክ ግሪሊሽ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የወሩ ምርጥ አሰልጣኝ እና ምርጥ ተጫዋች ተብለው ተመርጠዋል።

ሆላንዳዊው አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ሊቨርፑል በአዲሱ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ወር ላይ ያከናወናቸውን ሶስቱንም ጨዋታዎች እንዲያሸንፍ በማስቻላቸው በእጩነት የቀረቡትን ሌሎች አራት አሰልጣኞችን አስከትለው የወሩ ተመራጭ አሰልጣኝ ሆነዋል።

የመርሲሳይዱ ክለብ አለቃ በፕሪሚዬር ሊጉ የወሩ ምርጥ አሰልጣኝ ተብለው ሲመረጡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

አሰልጣኙ ባለፈው ዓመት የህዳር ወር ምርጥ አሰልጣኝ ተብለው መመረጣቸው ይታወሳል።

በሌላ በኩል ጃክ ግሪሊሽ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የወሩ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል።

በክረምቱ ከማንቸስተር ሲቲ ወደ ኤቨርተን በውሰት ያመራው ግሪሊሽ በአዲሱ ክለብ የመጀመሪያ ወር ቆይታው በ3 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች 4 ግብ የሆኑ የመጨረሻ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በመርሲሳይዱ ክለብ አጀማመሩን እያሳመረ ይገኛል።

ኤቨርተንም በጃክ ግሪሊሽ አማካኝነት ከ5 ዓመታት በኋላ የወሩ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን አግኝቷል።

በኤቨርተን ይህንን ሽልማት ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው ዶሚኒክ ካልቨርት ሌዊን ነበር።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ