የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በነገው ዕለት መካሄድ ይጀምራል
ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በጃፓን ርዕሰ መዲና ቶኪዮ በነገው ዕለት መካሄድ ይጀምራል።
በሩቅ ምስራቋ ሐገር በሚካሄደው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ20 ሴቶች እና በ16 ወንድ በአጠቃላይ በ36 አትሌቶች ለአሸናፊነት ትፎካከራለች።
በመድረኩ በሁለቱም ፆታ ከ800 ሜትር አንስቶ እስከ ማራቶን ባሉት ርቀቶች አትሌቶቿን ታሳትፋለች።
በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ 200 ከሚጠጉ ሀገራት የተውጣጡ 2 ሺህ 22 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያስረዳል።
በሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታ ተመሳሳይ 24 የውድድር አይነቶች እና አንድ በድብልቅ የሚካሄድ ውድድርን ጨምሮ በአጠቃላይ 49 የውድድር አይነቶች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል።
ለአሸናፊዎች ደግሞ 147 ሜዳልያዎች የሚበረከቱ ይሆናል።
ከሜዳልያዎቹ በተጨማሪም የዓለም አትሌቲክስ ለውድድሩ አጠቃላይ ወደ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ሽልማት ማዘጋጀቱን ተናግሯል።
የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች 70 ሺህ ዶላር እንዲሁም አዲስ ክብረወሰን ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ደግሞ 100 ሺህ ዶላር የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱ ተሰምቷል።
በተለምዶው የፀሐይ መውጫ ተብላ የምትጠራው ጃፓን በብዞዎች ዘንድ የሚወደደውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስታስተናግድ የዘንድሮው ለ3ኛ ጊዜ ነው።
ጃፓን ከዚህ ቀደም እንደ አውሮፓውያኑ በ1991 የተካሄደውን 3ኛው የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በ2007 ኦሳካ ላይ የተከናወነውን 11ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማስተናገዷ አይዘነጋም።
ከዚህ ቀደም ጃፓን ላይ በተካሄዱት በሁለቱም ውድድሮች የተካፈለችው ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 5 ሜዳልያዎችን በተለያዩ አምስት አትሌቶች ማግኘት ችላለች።
የሩቅ ምስራቋ ሀገር በታሪኳ ለ3ኛ ጊዜ የምታስተናግደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከነገ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ዘጠኝ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ማቲያስ ኩንኛ ከደርቢው ጨዋታ ውጪ ሆነ
የወሩ ኮኮቦች
ካርሎስ አልካሬዝ የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ሆነ