በአለምሸት ግርማ
ሴቶች ህልማቸውን እንዲያሳኩ ትምህርት ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ከዚህም በተጨማሪ ከማህበረሰቡ የሚያገኙት ድጋፍና ማበረታቻም ለስኬታማነታቸው የጎላ አስተዋፅኦ አለው። በቤት ውስጥ ትችያለሽ እየተባለች ያደገች አንዲት ሴት በሔደችበት ቦታ ሁሉ በራስ መተማመኗና ውጤታማነቷ ከፍ ይላል። የዛሬዋ እቱመለኛችን የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ናቸው። ያለፉበትን ተሞክሯቸውንና ልምዳቸውን እንደሚከተለው አጋርተውናል፦
ዶክተር ብርሃን ደመቀ ይባላሉ። ትውልድና ዕድገታቸው በኦሮሚያ ክልል በቀድሞ አጠራር ክብረመንግስት በአሁኑ አዶላ ከተማ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት እዚያው ነው። ምንም እንኳን ልጅ እያሉ መሆን የሚፈልጉት ሀኪም የነበረ ቢሆንም ህይወት ግን ወደ ሌላ ሙያ መርቷቸዋል።
በእርግጥ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ በሚኒ ሚዲያ ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው። በዚህም ለጋዜጠኝነት ቅርበት ወይም ልምምድ የሚያደርጉበት አጋጣሚ ስለሆነላቸው ጋዜጠኛ እንደሚሆኑም በውስጣቸው ማሰብ ጀምረው ነበር።
ይሁን እንጂ ያሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ራሳቸውን በመምህርነት ሙያ ውስጥ አግኝተውታል። የመምህርነት ስራቸውን የጀመሩት ከመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ከተመረቁ በኋላ በወጣትነታቸው መሆኑን ይናገራሉ። የጋዜጠኝነት ሙያ በልባቸው ስለነበር ስራው ለጋዜጠኝነት ቅርበት እንዳለው በማሰብ ነበር የሚሰሩት። ይሁን እንጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከጨረሱ በኋላ የጋዜጠኝነት ዝንባሌያቸውን ሙሉ በሙሉ በመተው በመምህርነት ሙያቸው ገፉበት።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በአሁኑ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞ ደቡብ ዩኒቨርሲቲ ዲላ መምህራንና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ነው። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ አግኝተዋል።
የመምህርነት ስራ የጀመሩት በሃዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ነው። በ1996 ዓ.ም የማስተማር ስራቸውን በጀመሩበት አመት ነበር የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበርን በበጎ ፈቃደኛነት የተቀላቀሉትና አባል የሆኑት። ወቅቱ ተማሪዎች ከ10ኛ ክፍል ተፈትነው ወደ ኮሌጅ የሚገቡበት ነበር። አፍላ ወጣቶች ትምህርታቸውን ለመማር ከተለያየ ቦታ ተመልምለው ሲመጡ ከቤተሰብ ተለይተው፤ ቤት ተከራይተው ህይወትን ለብቻቸው የሚጋፈጡበት ሁኔታ ይገጥማቸዋል። በተለይ ከገጠራማ አካባቢ የሚመጡ አፍላ ወጣት ሴት ተማሪዎች እንደሃዋሳ ባለ ትልቅ ከተማ የአካባቢውን ሁኔታ ተቆጣጥረው፣ ተላምደውና እራሳቸውን ጠብቀው ትምህርታቸውን መከታተል መቻል ትልቁ ፈተናቸው ነበር።
በወቅቱ በክፍል ውስጥና ከክፍል ውጪ ከተማሪዎች ጋር በነበራቸው ቅርርብ ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን ፈተናዎች ስፋትና ግዝፈት ለመረዳት እንዲችሉ እድል ፈጥሮላቸዋል። ችግሮቹን አይተው ግን ዝም አላሉም። ይልቁንም ተማሪዎቹን የሚያግዙበትን መንገድ ማፈላለግ ጀመሩ እንጂ። በዚህ ወቅት ነበር የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ወጣቶች በየትምህርት ተቋማቱ እየተዘዋወሩ የሚሰጡትን የአቻ ለአቻ የስነ-ተዋልዶ ጤና ትምህርት ለማየትና በበጎ ፈቃደኝነትም ለመመዝገብ የወሰኑት። ወደ ማህበሩ ሲቀላቀሉ በማህበሩ በሚሰሩ ስራዎች ላይ ለትውልድ አሻራን ማሳረፍ ትልቁ ዓላማቸው ነበር።
በ1997 ዓ.ም በተደረገው የደቡብ አካባቢ ጽ/ቤት የበጎ ፈቃደኞች ቀን በተደረገ የአካባቢ ጽ/ቤቱ አማካሪ ቦርድ ምርጫ ላይ የአማካሪ ቦርድ አባል በመሆን ተመረጡ። በዚህ ሁኔታ ማህበሩን ለረጅም ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን የበጎ ፈቃደኝነትን ፅንሰ ሃሳብ፣ የማህበሩን ዓላማ እንዲሁም የማስተዳደርና የመምራት ልምድ በማዳበር ከ4 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ለሁለተኛ ዙር ለተጨማሪ 4ዓመታት በአማካሪ ቦርድ ሰብሳቢነትና በብሔራዊ ቦርድ አባልነት አገልግለዋል።
“በመቀጠልም የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሰረት ለአራት ዓመታት ካረፍኩኝ በኋላ ለ3ኛ ጊዜ ለተጨማሪ 4ዓመታት ማህበሩን ለማገልገል በአካባቢ ጽ/ ቤቱ በጎፈቃደኛ አባላት ዕድል ተሰጥቶኛል። በዚህም ከ2015ዓ.ም ጀምሮ ማህበሩን በፕሬዝደንትነት እንዳገለግል በጠቅላላ ጉባኤ አባላት በመመረጤ በአሁኑ ወቅት የማህበሩ ፕሬዝደንትና የብሔራዊ ቦርዱ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ።
“ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እያገለገልኩ በምገኝበት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲም ይሁን በሌሎች የትምህርት ተቋማት በስራዬም ይሁን በተጓዳኝ ካበረከትኳቸው አስተዋፅኦዎች ወይም በተለያዩ የማህበረሰብ ተቋማት ላበረከትኩት አስተዋፅኦ ከተሰጡኝ የምስክር ወረቀቶችና የምስጋናና ሽልማቶች የላቀ ቦታ የምሰጠው በ2016 ዓ.ም በተደረገው ʻየአቢሲኒያ የኢንደስትሪ ሽልማትʼ መርሃ-ግብር ላይ ያገኘሁት የከፍተኛ አመራርነት ከፍተኛ ክብር የወርቅ ሜዳሊያና ሊሻን ነው” ሲሉም በሙያቸው ስላበረከቱት ስኬት ይናገራሉ፡፡
በበጎ ፈቃደኝነት በሰጡት አገልግሎት ከኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ በተሰጣቸው እውቅና ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ሴቶች ራሳቸውን ብቁና ዝግጁ ካደረጉ መስራት የማይችሉት ነገር የለም የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ ከሴትነት ጋር በተያያዘ በሀገራችን ያልተቀረፉ ችግሮች መኖራቸውን ያነሳሉ። በተለይም የሴቶችን አስተዋፅኦና የስራ ድርሻ ተገቢውን ዋጋና እውቅና አለመስጠት፤ እንዲሁም አለመገንዘብ በዋናነት ጎልተው የሚታዩ መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥተው ያነሳሉ። በሌላም በኩል ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጫናዎች አለመቀረፋቸው ለሀገርና ለማህበረሰብ ዕድገት ትልቅ እንቅፋት መሆናቸውንም እንዲሁ።
“አባቴ እንደነገረኝ እኔም እንደማምንበት፤ ለሴት ልጅ ትልቁ የማሸነፊያ መሳሪያ ትምህርት ነው።” ይላሉ፡፡ ነገር ግን ትምህርት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ በመጥቀስ፡፡ በራስ መተማመን፣ እራስን በብዙ ዘርፎች ማብቃት፣ ትጋትና ቆራጥነት በእጅጉ አስፈላጊ መሆናቸውንም ይናገራሉ። “ሴቶች ከወንዶች እኩል ሳይሆን ከወንዶች በላይ ሃላፊነትና አስተዋፅኦ እንደሚጠበቅብን ማመንና መዘጋጀት ያስፈልጋል” ሲሉም ያብራራሉ።
ችግሮቹን ለመቅረፍ መፍትሔ ነው የሚሉትን ሃሳብ እንደሚከተለው አጋርተውናል፦
“የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመቅረፍ በቅድሚያ በማህበረሰባችን ውስጥ ሴቶች የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ በተገቢው ሁኔታ መገንዘብ ነው። ሌላው ሴቶች ከጓዳ ጀምሮ እስከ አደባባይ ለሚወጧቸው ተደራራቢ ኃላፊነቶች ተገቢውን ዋጋና እውቅና መስጠት ያስፈልጋል። እንዲሁም ሴቶችን ማስተማር ደግሞ እጥፍ ድርብ ጥቅም እንዳለው በመረዳት ሴቶች እንዲማሩ በሚደረገው ሒደት ውስጥ መሳተፍ ይገባል። በተጨማሪም ሴቶች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን በተገቢው ደረጃ መረዳትና ማስወገድ የማህበረሰባችን ትልቅ ሃላፊነት ነው። በዋናነት የሴቶችን ሰብዓዊና ህጋዊ መብቶች በማንኛውም ሁኔታ የሚገዳደሩ አመለካከቶች መቀረፍ አለባቸው። በዚህ ሒደት ውስጥ የሁሉም ተሳትፎና ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል”
ዶክተር ብርሃን ካካፈሉን ልምዳቸው በመነሳት ሴቶች የሚገጥማቸውን ማንኛውንም ችግሮች ለማሸነፍ የሚችሉት ሲማሩ ነው። ከትምህርት በተጨማሪ ደግሞ በሁሉም ነገር ራሳቸውን ማብቃትም ይጠበቅባቸዋል። በማህበረሰቡ ዘንድ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመቅረፍ በጋራ ተባብሮ መስራት የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ያስችላል!
More Stories
“ሳንቲም ሲጥሉልኝ አመስግኜ ነው የምመልሰው” – ወጣት ማህቶት በለጠ
“ጥበብ ነገሮችን በተለየ መንገድ ማየት መቻል ነው” – ተወዛዋዥ ተስፋ ጽዮን ንጉሴ
ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!