“በርካታ ችግሮችን ተጋፍጬ ፤ በፅናት አልፌአለሁ” – ባይራይ በርሄ

በገነት ደጉ

ከላይ በርዕሱ የተጠቀምነውን ሃሳብ የሰነዘሩት የዛሬው የችያለሁ አምድ ተረኛ ናቸው፡፡ አቶ ባይራይ በርሄ ይባላሉ፡፡ ትውልድ እና እድገታቸው በትግራይ ክልል፣ ልዩ ስሙ ውጀራት ሰርአዲ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ነዋሪነታቸው በመቀሌ ከተማ ሲሆን የትግራይ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበር ተወካይ ናቸው፡፡

አቶ ባይራይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በትግራይ ክልል በሚገኘው ፀሐፍቲ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ደግሞ “አዲ ጉደም” ተብሎ በሚጠራ መሰናዶ ትምህርት ቤት መከታተላቸውን ነው ያጫወቱን፡፡

የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በ2012 ዓ.ም በቢዝነስ ካምፓስ በኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡

ትምህርታቸውን ባጠናቀቁበት ዓመት የኮሮና ወረርሽኝ ከመከሰቱ ባሻገር፡፡ መቀሌ ላይ ደግሞ ከባድ ጦርነት ነበር፡፡ ወቅቱ እንኳንስ ለአካል ጉዳተኛ ጉዳት አልባ ለሆነውም ሰው ከባድ በመሆኑ ዋጋ ከፍለው ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በወቅቱ በትምህርታቸው ጥሩ ዝንባሌ ያላቸው ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ ያስታወሱን አቶ ባይራይ፣ 3 ነጥብ 3 በማምጣት በጥሩ ውጤት ለመመረቅ በቅተዋል፡፡

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ “ኢማጅን ዋን ዴይ” ተብሎ በሚጠራ ግብረሰናይ ድርጅት በማህበረሰብ አገልግሎት ባለሙያ በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

አቶ ባይራይ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ነበር፡፡ ወላጆቻቸው ይኖሩ የነበረው ገጠር አካባቢ በመሆኑ ልጅ እያሉ የፖሊዮ ክትባት ባለመውሰዳቸው ምክንያት የልጅነት ልምሻ ተጠቂ ሆነዋል፡፡

አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ምንም ዓይነት የመከፋት ስሜት እንደማይሰማቸው ይናገራሉ። አንድ ሰው የአካል ጉዳቱን ካመነበት ምንም ማለት እንዳልሆነም ይገልጻሉ። ከዚህም የተነሳ አካል ጉዳተኝነታቸው የሚሳቀቁበትና የሚሸማቀቁበት ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው ቀና ብለው የሚሄዱበት፣ ብሎም ራሳቸውን የሚገልጹበት እንደሆነም ያምናሉ፡፡

አቶ ባይራይ በአሁኑ ወቅት ባለትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ናቸው፡፡ የትዳር አጋራቸው ጉዳት አልባ በመሆናቸው ብዙውን ነገር እያገዟቸው ዛሬን ማየት ስለመቻላቸው ያነሳሉ፡፡

በ2013 ዓ.ም ነበር ወደ ትዳር ዓለም የገቡት፡፡ በወቅቱ ስራ እንደያዙ የሚያገኙት ደመወዝ የቤት ኪራያቸውን ከፍሎ እና የቤት ውጪያቸውን ሸፍኖ የነገ ህይወታቸውን የተሻለ የማድረግ አቅም አልነበረውም፡፡

ኑሮ ቢከብዳቸውም የገጠማቸውን ፈተና የሚያቀልላቸው አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ” በማለት ስራ እንደያዙ ወዲያው በትዳር ተጣመሩ፡፡

ከባለቤታቸው ጋር የነበራቸው ፍቅር የሚያስቀና ቢሆንም ወላጆቿና ቤተሰቦቻቸው በጽኑ ተቃውመዋቸው ነበር፡፡

“ሰው አጥተሽ ነው እንዴ እሱን የምታገቢው?” የሚለው ቅሬታ ከባድ ፈተና ሆኖ ብቅ አለ፡፡ አልፎ አልፎ አለመግባባት እና ግጭቶች መከሰታቸውም አልቀረም፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ግን ትዳራቸው በጽኑ መሠረት ላይ መቆም ችሏል፡፡

በወቅቱ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ለአካል ጉዳተኞች የነበረው የተሳሳተ አመለካከት ክፉኛ እንደጎዳቸው አቶ ባይራይ ይናገራሉ፡፡ በቤተሰብ ጣልቃ ገብነት የተነሳም ፈታኝ ጊዜያትን ማሳለፋቸው የግድ ነበር፡፡

“በህይወቴ በርካታ ችግሮችን ተጋፍጫለሁ፡፡ እነዚህን ሁሉ በጽናት አልፌያለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የህብረተሰቡ የተሳሳተ አመለካከት ካልሆነ በቀር አካል ጉዳተኝነቴ በእኔ ህይወት ላይ የፈጠረብኝ የተለየ አሉታዊ ተጽዕኖ የለም” ሲሉም አስረድተዋል፡፡

“እንዲያውም የህብረተሰቡ የተሳሳተ እሳቤ አበርትቶኛል እንጂ ካሰብኩት ጎዳና ወደ ኋላ አላስቀረኝም” ሲሉም የገጠማቸውን ፈተና ወደ በጎ መቀየር መቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡

የትዳር አጋራቸው የቤት እመቤት ስለመሆናቸው የተናገሩት አቶ ባይራይ ባሳለፏቸው ውጣ ውረዶች እና የስኬት ጎዳናዎች የቤተሰቦቻቸውና የአካባቢውን ህብረተሰብ ጫና ወደ ጎን በመተው ከጎናቸው አብረው እንደነበሩ ነው የገለፁት፡፡

አቶ ባይራይ በሚሰሩበት መስሪያ ቤት ጠንካራ እና ታታሪ ባለሙያ ናቸው፡፡ እኛም ያገኘናቸው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መድረክ በሀዋሳ ከተማ በተካሄደበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አያይዘን በመድረኩ ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው ምን እንደተሰማቸው ጠይቅናቸው ምላሽ ሲሰጡም፡-

“አካል ጉዳተኞች በሰላም ጉዳይ ላይ ተሳታፊ መሆናቸው እጅግ አስደስቶኛል፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት ሀገራችን ሌላ በርካታ ቁጥር ያላቸው አካል ጉዳተኞች ልትጨምር ተገዳለች፡፡ የምኖረው በመቀሌ ከተማ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በነበረው ጦርነት ምክንያት በመቀሌ ከተማ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ጨምሯል፡፡

“አሁን በምክክር መድረኩ ግን ለሰላም ቅድሚያ ተሰጥቷል፡፡ በዚህም ስለሰላም ሲወራ ከምንም በላይ ዘብ መቆም ያለባቸው አካል ጉዳተኞች ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ የምክክር ኮሚሽን ከጦርነቱ በፊት ቢሆን ኖሮ ትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰቱ ምስቅልቅል የሆኑ ጉዳዮች አይስተናገዱም ነበር” በማለት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አክለውም የምክክር ኮሚሽኑ ይዞት የመጣው አጀንዳ በተለይም ለአካል ጉዳተኞች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡

“በሀገራችን እንደሚታወቀው አካል ጉዳተኞች የተገለሉ ናቸው፡፡ ይህም መድረክ ለአካል ጉዳተኛ አመራሮች ብቻ ሳይሆን እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ አለበት” የሚልም ሃሳብ አንስተዋል፡፡

አካል ጉዳተኞችም በሀገራቸው ሰላም ጉዳይ እኛን ያገባናል በማለት ንቁ ተሳታፊ በመሆን እስከታሰበው ውጤት ድረስ አብረው ሀሳብ በመስጠት በባለቤትነት መሳተፍ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች ሰላም ከሌለ ከምንም በላይ ተጎጂ፣ በአንፃሩ ደግሞ ሰላም ካለ ተጠቃሚ ስለመሆናቸው አያይዘው ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገር አካል ጉዳተኞች ማንኛውንም ስራ ሳይመርጡ እና ሳይፈሩ በድፍረት መስራት እንዳለባቸው ምክረ ሃሳባቸውን ይለግሳሉ፡፡ “ተስፋ ባለመቁረጥ የነገ ህይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ በመስራት ውጤታማ መሆን አለባቸው” ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡

ሰው በራሱ ጥረት እንጂ በሰው ድጋፍ ብቻ ሰው መሆን እንደማይችል ያስታወሱት አቶ ባይራይ፣ “ለዚህ የራሳችን የውስጥ ጥንካሬ እና ዓላማ ወሳኝ በመሆኑ የውስጥ ጥንካሬያችን ላይ መስራት ያስፈልጋል” ሲሉም መክረዋል፡፡