“እናት ከዚህም በላይ ይገባታል”

በአለምሸት ግርማ

ፈተና ሳይገድባቸው ያሰቡበት ለመድረስ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች የሚያልፉበት መንገድ ለብዙዎች ማስተማሪያ ነው። የዛሬዋ እቱ መለኛችንም አያሌ ፈተናዎችን አልፋ ራሷን ያበረታች ሴት ነች። ከልምዷ ልታካፍለን ዛሬ በስራ ቦታዋ ተገኝተናል፦ ወ/ሮ ታደለች ዴአ ትውልድና ዕደገቷ ወላይታ ሶዶ አካባቢ ነው።

ለቤተሰቦቿ 7ኛ ልጅ ስትሆን ትምህርቷንም እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ እዚያው የተወለደችበት አካባቢ ነው የተከታተለችው። በወቅቱ በትምህርቷ የመግፋት ትልቅ ጉጉትም ነበራት። ትልቅ ቦታ መድረስ እና ባለሀብት መሆን ደግሞ ዋናው ህልሟ ነው። በዚህ ህልሟ ውስጥ ደግሞ ወላጆቿን ማገዝ በክፍተታቸው አለሁላችሁ ማለትም የውስጧ ፍላጎት ነው። ያንን ህልሟን እውን ለማድረግ ገና በለጋ ዕድሜዋ ከትምህርቷ ጎን ለጎን ትንንሽ የንግድ ስራዎችን ትሰራ ነበር። ወላጅ አባቷ ገና በልጅነቷ ነበር በሞት የተለዩት።

በትምህርቷ ጎበዝ የነበረች ቢሆንም እስከምትፈልገው ማስቀጠል ግን አልቻለችም። ችግርን ለማሸነፍ ትምህርቷን አቋርጣ ስራ መስራት ግድ ሆነባት። ከእሷ ቀደም ብላ ታላቅ እህቷ ሃዋሳ ለስራ መጥታ ነበር። እሷም በ1997 ዓ.ም የእህቷን ዱካ ተከትላ ወደ ሃዋሳ መጣች። ሃዋሳ እንደመጣች የሰው ቤት ተቀጥራ መስራት ጀመረች። “ለአራት ዓመታት በሰው ቤት ሰራተኝነት ሰርቻለሁ” ብላ ስታጫውተን በወቅቱ የነበረችበትን ስሜት በማስታወስ ጭምር ነበር። የምታገኘው ገቢ በልጅነቷ መድረስ ወደ ምትፈልገው ደረጃ ለመድረስ መንገዱን ሩቅ አድርጎ አሳያት። በዚህ ጊዜ ነበር አንድ ነገር ለማድረግ የወሰነችው። የሰው ቤት ስራዋን አቁማ የራሷን ስራ ለመስራት። በዚህ ውሳኔዋ መሰረት ከሰው ቤት ወጥታ የራሷን ስራ መስራት ጀመረች።

ስራ ስትጀምር ቀድሞ ቀጥራ የምታሰራት ሴት በምትነግድበት ቦታ ባለ ትንሽዬ ትርፍ ቦታ ላይ ፌስታልና ቄጠማ እንድትነግድ ፈቃድ ሰጠቻት። አሰሪዋን በጉልበትዋ እየረዳች እሷ ደግሞ የራሷን ንግድ መነገድ ጀመረች። እንዲሁም ሻይና ቡና፣ እሸት በቆሎ ካለፈችባቸው ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ትንሽ ብትቆይም አሁንም ለውጥ እንደሚያስፈልጋት ማሰብ ጀመረች። ከጓደኞቿ ጋር በመሆን በማህበር ተደራጅታ ስራ ጀመረች።

መንግስት በወቅቱ ባመቻቸው የስራ ዕድል በመጠቀም እሷና ጓደኞቿ በመናኃሪያ መውጫ ላይ የፍራፍሬ ንግድ ጀመሩ። ንግዳቸው ውጤታማ ነበር። የገበያ ችግርም አልገጠማቸውም። በዚህ ሁኔታ ተግባብተው በመስራት ለአምስት ዓመታት አብረው ቆዩ። የቤት ኪራይ ስለሌለባቸውና ተጋግዘው ስለሚሰሩ የስራ ጫና አልነበረባቸውም። ተጠቃሚ መሆንም ችለዋል። እሷም ገቢዋ ከቀድሞ መሻሉን፤ ኑሮዋም መለወጡን ትናገራለች።

ህልሟን ለማሳካት ከምታገኘው ገቢ ትቆጥብ እንደነበርም አስታውሳናለች። በ2001 የተጀመረው የማህበር ስራ 5ዓመት ሲሞላው ጊዜያችሁ አብቅቷል ተብለው የስራ ቦታቸው ተወሰደባቸው። በዚህ ጊዜ ነበር ለራሷ ስራ ለመጀመር የወሰነችው። ይሁን እንጂ በወቅቱ ቶሎ ወደ ስራ መግባት እንዳልቻለችም ታስታውሳለች። ሁሉ ችግሮች ተቋቁማ እንደገና ወደ ስራ ለመግባት የምታውቃቸውን ሰዎች ታማክር ጀመር። ምን ብሰራ? የት ሰፈር ብሰራ? ውጤታማ እሆናለሁ፤ የሚለውን ጥያቄ የተሻለ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ትጠይቅ ነበር። እነሱም ይሆናል ያሉትን ሀሳባቸውን ከመለገስ ወደኋላ አላሉም። በዚህ መሃል ታዲያ ወደ ትዳር የምትገባበት አጋጣሚም ተፈጥሮ ነበር። በ2005 ዓ.ም ከተዋወቀችው ወጣት ጋር ትዳር ለመመስረት በቅታለች። በዚያም “ከአንድ ብርቱ ሁለት መዳሐኒቱ” እንደሚባለው ስራቸውን ሁሉ እየተጋገዙ እንደሚሰሩም ነው ያጫወተችን። ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት ለስራ ወጥተው ባሉበት ሌባ ቤታቸውን በሙሉ ዘረፋቸው። ማታ ከስራ ሲመለሱ በቤታቸው ውስጥ የቀረ ዕቃ አልነበረም።

በወቅቱ በሁኔታው በእጅጉ ድንጋጤ ውስጥ ገብተው ነበር። ስራ ለመስራትም ሆነ የዕለት ፍላጎታቸውን ለማሟላት ተቸግረው ነበር። በዚያም ብዙ ሰዎች ማለትም ጓደኞቻቸው፣ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው አፅናንተዋቸዋል፤ አግዘዋቸዋል። በኋላም ከዚህ በፊት ፍራፍሬ በጅምላ የሚያከፋፍል ደንበኛዋ የነበረ ሰው የደረሰባቸውን ችግር ሰምቶ አሁን የምትሰራበትን ቦታ አፈላልጎ፤ የ6 ወር የቤት ኪራይ ከፍሎ፤ ስራ ማስጀመሪያ ገንዘብ አግዞ ወደ ስራ እንድትገባ አድርጓታል። በዚህም ትልቅ ባለውለታዋ መሆኑን ከምስጋና ጭምር ነው የተናገረችው። በአሁኑ ሰዓት በንግድ ቦታዋ የአርባ ምንጭ አፕልን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን፣ ቡላና ቡና ትነግዳለች።

በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ስራ ዛሬ ተስፋፍቶ ብዙ ደንበኞችንም ማፍራት እንድትችል አድርጓታል። በተለይም ደግሞ ትላለች ወ/ሮ ታደለች “ጥራት ያለው ፍራፍሬ ስለምይዝ የረጅም ዓመታት ደንበኞን ማፍራት ችያለሁ። ጥራት ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ነው። አንዱ ደንበኛ ሌላውን ስለሚያመጣ የገበያ ችግር ገጥሞኝ አያውቅም። በዚህም ደስተኛ ነኝ” ወ/ሮ ታደለች ከትዳሯ ሁለት ልጆችን ማፍራት ችላለች። ባለቤቷም ቀድሞ የተለያዩ የንግድ ስራዎችን ይሰራ የነበረ ሲሆን በኋላም አብረው መስራት መጀመራቸውን አስረድታናለች።

የእሱ የንግድ ስራ እየተቀዛቀዘ ሲመጣ ከገቢያቸው በቆጠቡት ገንዘብ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ(ባጃጅ) ገዝተው እሱ መስራት ጀመረ። በባጃጁ የተወሰነ ጊዜ ከሰራ በኋላ፤ የእሷ ስራ እየተጠናከረ በመምጣቱ መለስተኛ ተሽከርካሪ(ሚኒባስ) ገዙ። ባለቤቷ በአሁኑ ሰዓት የታክሲ ስራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በሚያስፈልጋት ነገር ሁሉ እንደሚተጋገዙ ትናራለች። በተለይም ልጅ ሆና ከምታስበውና ከምታልመው አንፃር ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች።

ቤተሰቦቿን በሚገባ እያስተዳደረች ነው። በተለይም እናቷን ደግሞ በምትፈልገው ልክ እየተንከባከበች መሆኗ ትልቅ ደስታ የፈጠረላት ሲሆን፦ “እናት ከዚህም በላይ ይገባታል ለእኔ በቂ አይደለም ከዚህ የበለጠ ባደርግላት ደስ ይለኛል። ነገር ግን እናቴ በዚህ ሰዓት ምንም ሳይጎድልባት እየኖረች ትገኛለች። ይህም ትልቁ ስኬቴ ነው” ትላለች። እንዲሁም በስራ ቦታ ላይ በቀን ቢያንስ ከ20-30 ለሚሆኑ ሰዎች አንድ ጊዜ የሚመገቡትን ትለግሳለች። ህፃናት፣ እመጫት እናቶች፣ አዛውንቶች ለምፅዋት ወደ እሷ ይመጣሉ። እሷም አታሳፍራቸውም፤ ካላት ላይ ታካፍላለች። በዚህም ደስተኛ መሆኗን ጭምር ትናገራለች። ባልሰራ ኖሮ ይህንን ማድረግ አልችልም ነበር በማለት። ለወደፊት ያቀደችውን ስታጫውተን፦ አሁን የፍራፍሬ ችርቻሮ ነው የምሰራው።

ወደፊት ቢሳካልኝ ግን ማከፋፈያ ከፍቼ ለብዙዎች የስራ ዕድል መፍጠር ነው ፍላጎቴ። አሁን የምሰራበት ቦታ ተነሺ ነው። እዚህ የምቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው። ቦታዬን ስቀይር እንዳሰብኩት ስራዬንም መቀየርና ማስፋት እፈልጋለሁ። በእርግጥ በቃለ መጠይቃችን ወቅት የታዘብነው ነገር ቢኖር ከእግረኞች በተጨማሪ ብዙ ሰዎች በሞተርም፤ በመኪናም እየመጡ ይገዟት ነበር። መርጣ፣ መርቃ ያሉበት ወስዳ ትሰጣለች። እኛም ይሔ እንዴት ሆነ ስንል ጥያቄ ሰንዝረንላት ነበር፦ “አብዛኛዎቹ የረጅም ጊዜ ደንበኞቼ ስለሆኑ ፍላጎታቸውን አውቃለሁ። የሚፈልጉት ዓይነት ከሌለ የለም ነው የምለው እንጂ ዝም ብዬ አልሰጥም። ለዚያ እነሱም ያምኑኛል።

አንዳንድ ጊዜ ገንዘብ ባይዙ ወይም ቢጎድልባቸው በዱቤ እሰጣለሁ። እነሱም በሌላ ጊዜ አምጥተው ይሰጡኛል። ይሔ ነው መተማመንንና ደንበኝነትን የሚያጠናክረው” ሴቶች እሷጋ መጥተው ልምዷን ቢጠይቋት ምክር ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኗን ትናገራለች። ስራ ለመጀመር የሚያስፈልገው ፍላጎት ብቻ ነውም ትላለች። ምንም ገቢ የሌላቸው ሴቶች አንድ ሰው ጋር ተጠግተው ጥቂት ነገር ቢሰሩ ስራው ያድጋል። ለምሳሌ፦ ጎመን፣ ዳጣ የመሳሰሉትን መስራት ይቻላል። የስራ ትንሽ የለውም። ቢያንስ ገንዘብ ባያተርፉ ለቤታቸው የሚጠቀሙትን ሊያተርፉ ይችላሉ።

በተለይም ወደ ንግድ ለመግባት የሚፈልጉ ሴቶች ምናልባት ሲጀምሩ ስራውን እስኪለምድ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ትርፍ ላይኖር ወይም ኪሳራ ሊያጋጥም ይችላል። ነገር ግን ስራው ሲለምድ ማደጉ አይቀርምና ተስፋ ሳይቆርጡ እንዲሰሩ እመክራለሁ ትላለች ወ/ሮ ታደለች።