ትኩረት ለቅድመ መከላከል ሥራ
በደረጀ ጥላሁን
ኢትዮጵያ ውስጥ የመሬት መንሸራረት በተለያዩ ጊዜያት መከሰታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። የመሬት መንቀጥቀጥ ሲኖር የመሬት መንሸራተት ይኖራል፡፡ ከፍተኛ ዝናብ ባለበት አካባቢ በተለይ ገደላማ እና ቁልቁለታማ አካባቢዎች ላይ የመሬት መንሸራተት ይስተዋላል።
የመሬቱ አቀማመጥ ተዳፋት ወይም በጣም ቁልቁለታማ ከሆነ አፈሩ በመንሸራተት ከታቹ ያለ አካባቢ ላይ ወርዶ ይከመራል። ስፍራው የመኖሪያ መንደር ከሆነ ታዲያ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ መገመት ቀላል ነው።
ከሰሞኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በዚሁ መልኩ የተከሰተው የመሬት ናዳ የወገኖቻችንን ህይወት በመቅጠፍ የከፋ ጉዳት አስከትሏል።
ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም እሁድ ለሊት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ የተጫነውን ናዳ ለማንሳት ሰኞ ረፋድ ላይ ርብርብ እየተደረገ በነበረበት ወቅት መሬቱ ተደርምሶ ተጨማሪ ናዳ በማስከተሉ የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡
ስፍራው ተዳፋታማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ ናዳ ቢከሰትም፤ በዚህ ልክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ አደጋ ሲከሰት የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነም ተገልጿል።
የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምአ አደጋውን ተከትሎ እየተሠሩ ባሉ ተግባራት ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከዚህ ቀደም በጎፋ ዞን ተመሳሳይ አደጋ ተከስቶ እንደሚያውቅና በዚህ ልክ የሰው ሕይወት አጥፍቶ እንደማያውቅ አንስተዋል፡፡
አደጋን አስቀድሞ የመከላከልና የአደጋ ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች ማኅበረሰቡን የማስወጣት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰው አሁን አደጋው የደረሰበት አካባቢ ከዚህ ቀደም የስጋት ቀጠና ያልነበረ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ የደረሰው የናዳ አደጋ በአንድ የቤተሰብ አባላት ላይ የደረሰን ጉዳት ለመታደግ ወደ ስፍራው ባቀኑ በርካታ ሰዎች ላይ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ መቻሉን አብራርተዋል።
የክልሉ መንግስት ከፌደራል አደጋ ስጋት ጋር በመቀናጀት የተጎዱ ሰዎችን ነብስ የማዳን፣ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡትን የመቅበርና ለተጎጂዎች የመጠለያና ምግብ በማቅረብ ተጨማሪ ጉዳት ለመቀነስ ርብርብ በማድረግ ላይ መሆኑንና ተጎጂ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋዎች የሚከሰት ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም ከባድ ዝናብ ባሰከተለው የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ሰዎች መሞታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የአሁኑን አደጋ “እጅግ በጣም ልብ ሰባሪ ክስተት” ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ናቸው። “በተፈጠረዉ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የውድ ወገኖቻችንን ህይወት አጥተናል” ሲሉም ማዘናቸውን ገልፀዋል።
በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመሬት ናዳ ሳቢያ የሞቱ ወገኖች ቁጥር በመቶዎች ደርሷል፡፡ አስክሬን የማፈላለጉ ስራ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር እንደሚችልና የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ የቀጠለ ስለመሆኑንም ተነግሯል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት በህይወት ለተረፉ ቤተሰቦች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፥ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡ በቀጣይም በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋምና ለመደገፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከህዝቡ ጎን በመቆም የተጎዱትን ለመደገፍ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ርዕሰ-መስተዳድሩ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የፌዴራሉ መንግሥት የአደጋዉን ተጎጂዎችን ለመታደግ፣ በናዳ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ለማፈላለግና የነብስ አድን ሥራዎችን ለማከናወን እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸዉን ዜጎች መልሶ ለማቋቋምና የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመለየት ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ አስቸኳይ የአደጋ መከላከል ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ስፍራው መላኩን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በደረሱ የጎርፍ አደጋዎች የሠው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። በቅርቡም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን በደረሰ የጎርፍ አደጋ የሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳደር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልም ከሰሞኑ የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ የመሬት መሰንጠቅ መከሰቱን ከክልሉ መንግስት የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ተደጋጋሚነት ያለው የዝናብ መጠን በሚኖርበት ወቅት አፈሩ ውሃ የመሸከም አቅሙ ከእለት ወደ እለት እየቀነሰ የመሄድ አዝማሚያ ሊኖር ይችላል። ይህ ሁኔታም በቀላሉ ወደ ቅጽበታዊ ጎርፍ የመከሰት እድል ስለሚፈጥር ጥንቃቄ እንዲደረግ ይመከራል፡፡
ዓለም አቀፍ የአየር ክስተቶችን መሰረት አድርጎ ትንበያ የሚሰጠው የሜትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በበኩሉ፤ ኤልኒኖ የተባለው የአየር ክስተት (የምስራቅና የመካከለኛው ፓስፊክ ውቅያኖስ ከመደበኛ በላይ መሞቅ) ምክንያት በልግ ዋነኛና ሁለተኛ የዝናብ ምንጫቸው በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት ይገጥማቸዋል፡፡
በዚህም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከባድ ዝናብ አዘውትሮ የሚዘንብ ሲሆን በሰሜን ምስራቅ፤ ስምጥ ሸለቆ፤ ምስራቅ፣ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አከባቢዎች “ቅጽበታዊ ጎርፍ” ሊከሰት እንደሚችል ይጠበቃል ሲል ኢንስቲትዩቱ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በመሆኑም መሰል ጎርፍ እና የመሬት ናዳ ተከስቶ በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የአየር ንብረት መረጃዎችን በመጠቀም አስፈላጊውን የቅድመ መከላከል ሥራ በመሥራት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው