በሴራ ታላላቅ ፕሮጀክቶቿን ለመገንባት ያልታደለችው አፍሪካ

በሴራ ታላላቅ ፕሮጀክቶቿን ለመገንባት ያልታደለችው አፍሪካ

በኢያሱ ታዴዎስ

..ክፍል አራት

ምዕራባዊያን ዛሬ ላይ ዓለም የሚደመምበትን ሥልጣኔና ዕድገት በራሳቸው አላመጡትም። እነሱ “የአዲስ ዓለም አሰሳ ወይም ግኝት” ሲሉ ከሚጠሩት ሂደት ጀምሮ ሀገራትን በመውረርና ሃብታቸውን በመዝረፍ ያሳኩት የቅኝ ግዛት ዘመቻ ከበርቴ አድርጓቸዋል፡፡

በ15ኛው እና 16ኛው ክፍለ ዘመን በአሳሾቻቸው የጀመረው አሰሳ ዓላማው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አፍሪካን፣ እስያን እና አሜሪካን በባህር መንገድ ማገናኘት የሚል ነበር፡፡ ክርስትናን፣ ሃብትን እና የራስን ክብር (የአውሮፓዊያኑን) ማላቅ ደግሞ የአሰሳው መጠቀሚያ መሳሪያ ነበር፡፡

እዚህ ጋር ውድ አንባቢያን ልብ እንድትሉልኝ የምፈልገው! አውሮፓዊያን ‹‹አስሰን አዲስ ምድር አገኘን›› የሚሉት ከቅድመ ታሪክ ጀምሮ ጥንተ ሥልጣኔን አጣጥመው እስከ ዘመናዊው ዓለም ድረስ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉትን አፍሪካን፣ እስያን እና ደቡብ አሜሪካን ነው፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን አፍሪካን የሚያክል ግዙፍ አህጉር ከነበረበት የጨለማ ዓለም ብርሃን አጎናጽፈነዋል የሚል ድምዳሜ አላቸው፡፡ እዚህ ጋር ያላስተዋሉት እንደ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ያሉ የ3 ሺህ ዓመታት ታሪክ እና የሥልጣኔ መሰረት ያላቸውን ሀገራትን መዘንጋታቸው ነው፡፡

ብቻ ይህ አሰሳ ብለው የሚጠሩት ፈሊጥ በኋላ ላይ ቅኝ ግዛትን ወልዶ አውሮፓዊያኑ ሃብት መዝረፍን ዋነኛ ዓላማ አድርገው መነሳታቸውን የታሪክ ድርሳናት ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡ በደቡባዊ የአፍሪካ ባህር ዳርቻ በአውሮፓዊያኑ 1488፣ እንዲሁም በአሜሪካ ደግሞ በ1492 እንደከተሙ ቀጥታ ወደ ቅኝ ግዛት ነበር የገቡት፡፡

የወቅቱ ኃያላን ስፔን እና ፖርቱጋልን ጨምሮ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድስ እንዲሁም እንግሊዝ የአውሮፓዊያኑን እሳቤ፣ ባህል እና ተቋማትን በሚከትሙባቸው አህጉራት እያስፋፉ ቀስ በቀስ በኃይል ወደ መቆጣጠር ተሸጋገሩ፡፡

በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘውን ፈርጣማ ጡጫቸውን በማሳረፍና በባርነት በመግዛትም የተቆጣጠሯቸውን ሀገራት ማዕድናትና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶችን ወደ አውሮፓ ማጋዙን አጠናከሩ፡፡

ይህን ጊዜ ከገዛ አህጉራቸው እና ሰው ከማይኖርበት አንታርክቲካ ውጪ ሁሉንም አህጉራት በቅኝ ግዛት አዳረሱ፡፡ በይበልጥ ተጠቂ የነበሩት ደግሞ አፍሪካ፣ እስያ፣ ኦሺኒያ (አውስትራሊያን ጨምሮ)፣ ደቡብ አሜሪካ እና ሰሜን አሜሪካ ነበሩ፡፡

እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በዘለቀው በዚህ ግፍ በተሞላው ጭቆና፤ አውሮፓዊያኑ ለቀጣይ ትውልዶቻቸው የሚተርፍ ሃብት ማካበት ችለዋል፡፡ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ አሜሪካም የእነሱን ዱካ ተከትላ አብራ ዘራፊ በመሆን በሂደት ወደ ልዕልና መምጣት ችላለች፡፡

ይህ አካሄድ ምዕራባዊያኑ የራሳቸውን ባህል እንዲያሰርጹባቸው ከማድረጉም ባሻገር ጥሪታቸውን እንዳሻቸው እንዲጠቀሙ እና ጭቁኖቹ ሀገራት ከመጠን ያለፈ ድህነት ውስጥ እንዲዘፈቁ በጽኑ ሰርተዋል፡፡

ከቅኝ ግዛት ዘመን በኋላ ከየሀገራቱ የዘረፉት ማዕድናትና የተፈጥሮ ሃብቶች ክምችታቸው በቂ በመሆኑ የምጣኔ ሃብት ዕድገታቸው ስጋት ውስጥ እንዳይገባ ትኩረት አድርገው የሰሩት ታዳሽ የሆኑ ኃይሎች (Renewable energies) ላይ ነበር፡፡

ከታዳሽ ኃይሎችም ግዙፍ ሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን መገንባት ቀዳሚው ተግባር ሆነ፡፡ በእርግጥ ውሃን ለኃይል ማመንጫነት የመጠቀም ቴክኖሎጂ በጥንተ ቻይናዊያን ዘንድ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሃን ስርወ መንግስት እንደተጀመረ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ በሂደት በይዘቱና በባህርይው እየዘመነ፤ በተለይም በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በምዕራባዊያን ዘንድ መስፋፋት ቻለ፡፡ በዚህም ከ1940 እስከ 1970ዎቹ ድረስ እንደ ውጥናቸው ዓለምን የተቆጣጠሩት ምዕራባዊያኑ፣ የሕዝብ ብዛት እና የምጣኔ ሃብት ዕድገታቸውን ተከትሎ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ ላይ የሙጥኝ አሉ፡፡

በእርግጥ በእነዚህ ጊዜያት ቻይና፣ ብራዚል እና ሩስያን የመሳሰሉ ሀገራት ከምዕራባዊያኑ በላይ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን ገንብተው የምጣኔ ሃብታቸውን በአስገራሚ ሁኔታ አሳድገው ነበር፡፡

ይህ ደግሞ ዓለም በወቅቱ ጊዜውን ከዋጀ ቴክኖሎጂ ጋር ማዋሃዱ ምን ያህል ጠቃሚ እንደነበር አመላካች ነው፡፡ ከአፍሪካ እና ከሌሎች አህጉራት ዘርፈው ያከማቹትን ማዕድናትና የተፈጥሮ ሃብት ጥቅም ላይ ከማዋል ባለፈ ኢንደስትሪዎቻቸውን እንደሚደግፍ የተማመኑት ምዕራባዊያኑ በስፋት ግድቦችን መገንባቱን አጠናከሩ፡፡

የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ ማድረግ፣ ለሌሎችም መሸጥና የገቢ ምንጭን ማሳደግ፣ የቱሪዝም አቅምን ከፍ ማድረግ፣ እንዲሁም ስጋት የደቀነውን የአየር ንብረት ለመከላከል ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን መገንባት ትልቁ መፍትሄ ሆኖም ብቅ ብሏል፡፡

የተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚሰራው ወርልድ ዋይድ ፈንድ (WWF) በ2019 ባወጣው መረጃ መሰረት በመላው አውሮፓ 21 ሺህ 387 የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች ነበሩ፡፡ 8 ሺህ 785 የሚጠጉት ደግሞ ለመገንባት የታቀዱ ወይም በግንባታ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

በአሜሪካ (ዩናይትድ ስቴትስ) ደግሞ የሀገሪቱ የኃይል መረጃ አስተዳደር ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ እንዳደረገው 1 ሺህ 400 የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች፣ እንዲሁም 40 ከጸሃይ ብርሃንና ከነፋስ የሚገኙ ማመንጫዎች ይገኛሉ፡፡

አፍሪካም ብትሆን የታዳሽ ኃይልን ጥቅም ዛሬ ሳይሆን ገና ያኔ በቅኝ ግዛት ዘመን ነበር የተረዳችው፡፡ በትንሹ 55 ዓለም አቀፍ ወንዞች እና ከ10 ስኩዌር ማይል የበለጠ ስፋት ያላቸው 150 ሃይቆች ባለቤት ናት አህጉሪቱ፡፡

ናይል፣ ኮንጎ፣ ኒጀር፣ ዛምቤዚ፣ ኦሬንጅ፣ ሉዋላባ፣ ኦካቫንጎ፣ ቮልታ፣ ቫር የመሳሰሉት የአፍሪካ ኩራት የሆኑና ተትረፍርፈው የሚፈሱ ታላላቅ ወንዞች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ አፍሪካ ከማንም ያልተናነሰ የውሃ ሃብት እንዳላት ያሳያል፡፡

ለዚህም ነው ኃያላኑ ነቅተው በትጋት ግንባታ ባካሄዱበት ዘመን አፍሪካም ጅማሮዋን ያደረገችው፡፡ ለዚህም በ1938 ግንባታው የተጠናቀቀውና በወቅቱ 108 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የጀመረው የደቡብ አፍሪካውን ቫል ግድብ ማንሳት በቂ ነው። በ1955 ግንባታው ተጀምሮ በ1959 ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የዛምቢያው ካሪባ ግድብ ሌላኛው ነው፡፡ ግድቡ 2 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችልና በአፍሪካ ግዙፍ የነበረ ነው፡፡

ከዚያም በ1950ዎቹ መጀመሪያ ተነድፎ በ1960ዎቹ ግንባታው ተካሂዶ በ1970 ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የግብጹ አስዋን ግድብ፣ እንዲሁም በ1961 ግንባታው ተጀምሮ በ1965 አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጋናው አኮሶምቦ ግድቦችም እንዲሁ ይነሳሉ፡፡

በ1979 ግንባታው ተጠናቆ ስራ የጀመረውና 2 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችለው የሞዛምቢኩ ካሆራ ባሳ ግድብም መዘንጋት የሌለበት ነው፡፡ እንዲህ እንዲያ እየተባለ እስካለንበት ዓመት ድረስ በርካታ የተገነቡና በግንባታ ላይ የሚገኙ ግድቦችን መጥቀስ ይቻላል።

ይህ ግን የውሃ ሃብት ለተትረፈረፈላት አፍሪካ በቂ አይደለም፡፡ አህጉሪቱ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከምትችለው አቅም 90 በመቶ የሚሆነውን እንዳልተጠቀመች ዓለም አቀፉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማህበር በ2023 ያወጣው ጥናት ያመላክታል፡፡

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኃይል የማመንጨት አቅም ብቻውን አሁን አፍሪካ ከምታመነጨው በሶስት እጥፍ ማሳደግ የሚችል ነው፡፡ ኮንጎ ግን ለራሷም መትረፍ ተስኗታል። ይህ የሆነበትም ምክንያት አሜሪካዊያኑ እና አውሮፓዊያኑ እጅ እየጠመዘዙ ግዙፎቹ ፕሮጀክቶች እውን እንዳይሆኑ ያለማቋረጥ በመስራታቸው ነው፡፡

አፍሪካ በራሷ መልማት እንደምትችል ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተሻለ ማሳያ ሊገኝ አይችልም፡፡ ግድቡ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ሽፋን በእጅጉ ከማሳደግ ባለፈ፣ በቱሪዝምም ሆነ በአጠቃላይ ምጣኔ ሃብቷን በማበልጸጉ ረገድ ከፍተኛ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡

ከ6 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው ግድቡ ግንባታው እንዲስተጓጎል የውጪ ኃይሎች ያልሸረቡት ሴራ አልነበረም። ግብጽ እና ሱዳን ከፊት ተሰልፈው የመብት ጥያቄያቸውን ያነሱ ይምሰል እንጂ የሴራው ዋነኛ ጠንሳሽ እንግሊዝ ስለመሆኗ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

በ1902 (እ.አ.አ) በአጼ ምንሊክ ዘመነ መንግስት ኢትዮጵያ በጣና ሃይቅ፣ በአባይ እና ገባር ወንዞች ላይ ያለ እንግሊዝ ፈቃድ ግድብ እንዳትገነባ የሚያስገድድ ጨቋኝ ስምምነት አድርጋ ነበር፡፡ ስምምነቱም ኢትዮጵያ በገዛ የውሃ ሃብቷ እንዳትጠቀም እንቅፋት ሆነባት፡፡ ኢትዮጵያ በወቅቱ ነጻነቷን ያስጠበቀች አፍሪካዊት ሀገር ነበረችና ሌላ ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃዎችን እንዳትራመድ በእንግሊዝ ተፈረደባት፡፡

በ1929 ደግሞ ሌላ ስምምነት ተከተለ፡፡ ስምምነቱ የአባይ ወንዝ ባለቤቷን ኢትዮጵያን ያገለለ፣ በአንጻሩ ግብጽ እና ሱዳን የአባይ ወንዝን ለልማት እንዲጠቀሙ የፈቀደ ነበር፡፡ የዚህም ስምምነት ፈላጭ ቆራጭ እንግሊዝ ነበረች፡፡

የ1959ኙም ስምምነት በተመሳሳይ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያን አግልሎ ግብጽ እና ሱዳንን አትራፊ ያደረገ ነበር፡፡ በእነዚህ ስምምነቶች የታሰረችው ኢትዮጵያም እጅና እግሯን ታስራ እንዳትለማ የመደረግ ያህል በደል ተፈጽሞባት ቆይታለች፡፡

በተለያየ ጊዜ የሃገሪቱን የሥልጣን መንበር የተቆጣጠሩ መንግስታት በአባይ ወንዝ የመጠቀም ፍላጎት እያየለ ቢመጣም በስተመጨረሻ እውን የሆነው ግን በዘመነ ኢህአዴግ ነበር፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፡፡

… ይቀጥላል