የኣሪ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2018 በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን 62 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

የኣሪ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2018 በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን 62 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

‎የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት በዞኑ ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ በአቶ ካይስ ባንኪማ የቀረበ ሲሆን በምክር ቤቱ አባላት በበጀት አጠቃቀም ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበት 2 ቢሊዮን 62 ሚሊዮን 836 ሺህ 535 ብር ሆኖ ፀድቋል።

‎የኣሪ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ስመኝ ተስፋዬ፤ ህዝቡን ከተረጂነት በማላቀቅ ምርታማነትን ለማሳደግ መረባረብ እንደሚገባ አንስተው ምክር ቤቱ ለተፈፃሚነት ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

‎በዞኑ በግብርናና በኢንቨስትመንት ዘርፍ አመርቂ ዉጤት እየተመዘገበ ነው ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ፤ በበጀት ዓመቱ ለዘመናት ከህዝቡ እየተነሱ ያሉ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

‎የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ በሁሉም ዘርፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲችል ሁሉም አካላት መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

‎የበጀቱ ዝርዝርም ለዞን ማዕከል መስሪያ ቤቶች ለመደበኛና ለካፒታል ወጪዎች 349 ሚሊዮን 176 ሺህ 864 ብር፣ ለወረዳዎችና ለከተማ አስተዳደሮች ጥቅል በጀት 1 ቢሊዮን 651 ሚሊዮን 200 ሺህ 832 ብር፣ ለዞናዊ ካፒታል ፕሮግራሞች 43 ሚሊዮን 956 ሺህ 314 ብር፣ መጠባበቂያ በጀት 17 ሚሊዮን 582 ሺህ 525 ብር በጥቅሉ የዞኑ በጀት 2 ቢሊዮን 62 ሚሊዮን 836 ሺህ 535 ብር ምክር ቤቱ መርምሮ አጽድቋል።

‎የዞኑ ምክር ቤትም የምክትል አፈ ጉባኤና የኣሪ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ሃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ ሹመትን ጨምሮ ሌሎች የካብኔ አባላት ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቋል፡፡

‎ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን