በቤተልሔም አበበ
ጉልበታቸውን እና ገንዘብን ገና በልጅነት የዕድሜ ክልል ውስጥ በመጠቀም ስኬትን የተቀዳጁ ታታሪዎች እና መንፈሰ ጠንካሮች ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ሰዎች ውጤታማ ህይወትን መኖር እንዲችሉ ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ለቆሙለት ዓላማ መፅናት ሲችሉ በህይወታቸው ላይ የለውጥ ሂደትን በማየት ወደ ከፍታ መጓዝ ይጀምራሉ፡፡
በዚህም ሂደት ውስጥ አልፈው የራሳቸውን ኑሮና ህይወት የቀየሩ፥ ለውጥ ማምጣት የቻሉ ብርቱዎች ቀላል አይደሉም፡፡ የዛሬዋ እቱ መለኛችን፣ ሰዎች በልፋታቸው እና በጥረታቸው ልክ የማግኘት ፍላጎት ካላቸው፣ ካሉበት የምቾት ዓለም መላቀቅ ይኖርባቸዋል የሚል አስተሳሰብ ያላት የሰርቶ መለወጥ አብነት ናት፡፡
ምክንያቱም ለበርካታ ጊዜያት በምቾት ህይወት ተሸብበው የሚኖሩ ሰዎች ባላቸው የኢኮኖሚ ደረጃ ተደላድለው ሲኖሩ ባላቸው ላይ ይበልጥ ለመጨመር ሲዳክሩ አይስተዋሉም የሚል የግል ምልከታም ጭምር ይስተዋልባታል፡፡
ስለሆነም ካሉበት የኑሮ ሁኔታ ተመቻችቶ ከመቀመጥ፣ እራስን ዝቅ በማድረግ ነገ ለተሻለ ውጤት በማጨት ጥረት ማድረግ የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል ባይ ናት፡፡ እኛም ሥራ የለም ምን ልስራ? ለሚሉ እና ወጣትነታቸውን እያባከኑ ላሉ ወገኖች ምሳሌ ትሆናለች ስንል ተሞክሮዋን ልናካፍላች ወደናል፡፡
እቱ መለኛችን ረሂማ አለሙ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በወልቂጤ ከተማ ነው። ትምህርቷን ከወልቂጤ ከተማ በአስር ኪሎ ሜትር ራቅ ብላ በምትገኘው፣ ገራባ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ አስረኛ ክፍል ተከታትላለች፡፡
አስረኛ ክፍል ላይ የመጣላት ውጤት ኮሌጅ ገብታ ቴክኒክ እና ሙያ እንድትማር የሚጋብዛት ቢሆንም በወቅቱ ለዚህ ዝግጁ እና ፍቃደኛ ልትሆን እንዳልቻለች ተናግራለች።፡ ለወላጆቿ አምስተኛ ልጅ የሆነችው ረሂማ እንደማንኛውም የኢትዮጵያዊ ልጅ ጭቃ አብኩታ እና አፈር ፈጭታ ያደገች እንስት ናት፡፡ ምናልባት ለየት የሚያደርጋት በመስራት ማግኘት እንደሚቻል በልጅነት ዕድሜዋ ያረጋገጠች መሆኗ ነው፡፡
ለትምህርቷ የሚያስፈልጋትን ነገር ቤተሰቦቿን ጠይቃ ሳይሆን የምታሟላው ረጅም ርቀትን በጫካ ውስጥ በመጓዝ እንጨት ለቅማ ገበያ በመውሰድና በመሸጥ ደብተርም ሆነ ልብስ በእራሷ ታሟላ እንደነበር ትገልጻለች፡፡
ከዚህም ባሻገር ለወላጅ እናቷ አንዳንድ ጊዜ የማህበራዊ ህይወት ተሳትፎ ሲኖር በገንዘብ ትደግፍ እንደነበርም ትናገራለቸ።
በልጅነቷ የስራ ፍቅር ያደረባት ረሂማ ታላቅ ወንድሟ ወደ ሚኖርበት ሀዋሳ ከተማ በመምጣት ወንድሟ በሚሰራው የንግድ ስራ ትደግፈው ስለነበር የንግድ ሁኔታው፣ የደንበኛ አያያዝ ዘዴን በመቅሰም ወደ ንግዱ ዓለም ተሳበች፡፡
በዚህም ወጣት ረሂማ በ2009 ዓ.ም በአንድ መቶ ሀምሳ ብር መነሻ በመንገድ ዳር የጀበና ቡና በመሸጥ አሀዱ ብላ የእራሷን ንግድ ጀመረች፡፡ ከቡናው ንግድ ጎን ለጎን አቮካዶ እና ማንጎ ትሸጥም ነበር፡፡
ከምታገኘው ገቢ በቀን አምስት ብር መቆጠብ ጀመረች፡፡ በልጅነቷ መንፈሰ ብርቱ የሆነችው ይህቺ ወጣት ሰዎች ስራን ሳይንቁ ከትንሽ ንግድ ተነስተው እራሳቸውን መለወጥ እንደሚችሉ ያስመሰከረ ስራ ሰርታለች፡፡ ተሞክሮዋን አስመልክቶ ስትናገርም፡-
“እንዳንዶች ትንሽ ስራ እኔን አይቀይረኝም በሚል ግምት ሽንፈት ስለሚቀድማቸው ውጤታማ የማይሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ይሁንእንጂ ለወደፊት ህልማቸው ትልቅ ግምት በመስጠት ሊሰሩ ይገባል”፡፡
“በንግድ ዓለም ማትረፍ ብቻ ሳይሆን መክሰርም ሊገጥም ይችላል፡፡ ነገር ግን ደንበኞችን በማፍራት ውጤትን ማስቀጠል የሚቻልበት አማራጭ መንገዶችን መፍጠር በትኛውም አይነት ንግድ ላይ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ኑሮን ማሻሻል ይቻላል” ስትል ምክረ ሃሳቧን ትለግሳለች።
ከሞከረቻቸው ሌሎች የንግድ ስራዎች መካከል የጀበና ቡና ተመራጭ በመሆኑ እሱ ላይ ትኩረት በማድረግ ንግዷን በስፋት ማስቀጠልም ችላለች፡፡
ረሂማን የንግድ ዓለም ምን ይፈልጋል? ብለን ላቀረብንላት ጥያቄ፡- “ስዎች ውድ ነገር ለመሸጥ እድል ቢኖራቸው እንኳን መልካም የሆነ ተግባቦት ከሌሎች ጋር መፍጠር ካልቻሉ ውጤታማ መሆን አይችሉም፡፡ ለሰዎች ያለን አክብሮት በንግዱ ዓለም ተመራጭ እና ተወዳጅ እንድንሆን ያደርጋል፡፡ የንግድ ዓለም ማህበራዊ ተሳትፎን ስለሚጠይቅ እነዚህን በሟሟላት ውጤታማ እንድንሆን ያደርጋል” ስትል ትናገራለች፡፡
በአንዳንድ ወጣቶች ላይ የስንፍና እና የተስፋ የመቁረጥ ስሜቶች ሊታይባቸው ስለሚችል በአቋራጭ ለመበልጸግ ይፈልጋ። ከዚያ ይልቅ በላብ የሚገኝ ውጤት ሲበሉት ስለሚያስደስት በእራስ ጥረት መለወጡ ከምንም በላይ አስደሳች ያደርገዋልም ትላለች ረሂማ፡፡
ትላንትና በመቶ ሀምሳ ብር የጀበና ቡና መንገድ ዳር መነገድ የጀመረችው ረሂማ ዛሬ ላይ ንግዷን አስፋፍታ ለሌሎች የሥራ ዕድል ፈጥራለች፡፡ በስሯ ላሉት ሁለት አጋዦቿ በወር ሁለት ሺህ ብር በመክፈል ከእራሷ አልፋ ለሌሎችም የተረፈች እንስት ሆናለች፡፡
ረሂማ በስራ የምታምን በመሆኗ ሁሌም ስኬት ከጠንካሮች፣ ከጎበዞች እና የዓላማ ጽናት ካላቸው ሰዎች በስተጀርባ እንደምትገኝ ታነሳለች፡፡ በመሆኑም ማንኛውም መለወጥ የሚፈልግ ሰው በተሰማራበት መስክ ውጤታማ መሆን ካልተቻለ ሌላውን ዘርፍ ቀይሮ በመመልከት ወደፊት በሚያሻግር መስመር ላይ መሳተፍ ተገቢነት እንዳለውም ነው የምትናገረው፡፡
እንደ ረሂማ ገልጻ ከሆነ በህይወታችን ተስፋ እንድንቆርጥ የሚሰሙንን የድካም ስሜቶች ባለማድመጥ ውጤታማ ለመሆን መጣር አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ የወጣቷ ተሞክሮ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ትላንት በትንሽ ገቢ እራሷን ትመራ የነበረው ረሂማ ዛሬ ላይ ቁጠባዋን በሂደት በማሳደግ በሳምንት ከሶስት ሺህ ብር በላይ እንድትቆጥብ ያስቻላት ሥራ መስራቷ እንደሆነም ታነሳለች፡፡
ረሂማ ከስራዋ ጎንለጎን የሚያግዛት እና የሚደግፋት ባለቤት አላት፡፡ የአንድ ልጅ እናትም ሆናለች፡፡ በመስራቷ እና በመቆጠቧ ከመቶ ሀምሳ ብር ተነስታ ስምንት መቶ ሺህ ብር መድረስም የቻለች ክንደ ብርቱ እንስት ናት፡፡
ሰዎች ከህይወት ተሞክሮዋ እንዲማሩ የምትፈልገው ለመለወጥ እራስን ዝቅ በማድረግ መስራት፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ አስፍቶ ማሰብ እና ሁሌም ሰዎችን በአዎንታዊ ጎን መረዳት ለመለወጥ የሚያስችል ዘዴ ነው ስትል የግል ተሞክሮዋን በማንሳት ትመክራለች፡፡
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ