በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ እየተሳተፉ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስራ አጥነትን ለመቅረፍ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ አስታወቀ
በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በማመን ተደራጅተው ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ ለመሆን ጠንክረው እየሰሩ እንደሚገኙ በዞኑ ያነጋገርናቸው የኢንተርፕራይዞች አባላት ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙራድ ያሲን በዞኑ የኢንተርፕራይዝ ዘርፍን በገጠርና በከተማ ደረጃ በዘላቂነት ውጤታማ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ለበርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የአደይ ፕሮግራም በዞኑ በ3 ወረዳዎች ለ3ሺህ ያህል በሰብል ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንሰሳት ዘርፍ ለተሰማሩ ወጣቶች የስልጠናና የግብዓት ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።
በዚህም በዘርፉ ለውጥ እየተመዘገበ መምጣቱን የጠቆሙት ሀላፊው በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ እየተሳተፉ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እያደረጉት ያለውን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዞኑ ለኢንተርፕራይዞቹ የገበያ ትስስርን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው እንደሚገኝና ተግባሩ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያመላከቱት።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የገጠር ወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ባለሙያና በቢሮው የአደይ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ደምስ ስርበሞ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ከ2016 ዓ/ም ጀምሮ በክልሉ በ7 ዞኖችና በ1 ልዩ ወረዳ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ ለ7 ሺህ 324 ስራ አጥ ዜጎች የክህሎት ስልጠና በመስጠት ስራ መጀመሩን በማውሳት በዚህም በዘርፉ ለተለዩ ስራ አጥ ወጣቶች የክህሎት ስልጠናና ግብዓትን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ፕሮግራሙ በጉራጌ ዞን በቸሃ፣ በእኖርና በእንደጋኝ ወረዳዎች ለተደራጁ ወጣቶች እያከናወነ የሚገኘው የስልጠናና የግብዓት ድጋፍ የዚሁ አካል እንደሆነም አመላክተዋል።
በክልሉ በአደይ ፕሮግራም በተለይም በሰብል ልማት፣ በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በእንስሣት ሀብት ልማት ተደራጅተው ወደ ስራ ለገቡ ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ እና ማምረቻ 450 ሔክታር መሬት፤ የብድር አቅርቦት እንዲሁም የገበያ ትስስር እና ልዩልዩ መንግስታዊ ደጋፍና ክትትል በማድረግ ፕሮግራሙ ባቀፋቸው 15 ወረዳዎች ላቀረበው 590 ያህል ኩንታል የበቆሎ፤ የስንዴና የድንች ምርጥ ዘር እንዲሁም 562 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞች በአግባቡ ተደራሽ ማድረጉን አስተባባሪው ተናግረዋል።
በጉራጌ ዞንም ለወጣቶቹ እየተደረገ ያለውን የመሬትና መሠል ድጋፎች አበረታች መሆናቸውን በመጠቆም ፕሮግራሙ እያደረገ ያለው ድጋፍም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በዞኑ በቸሃና እኖር ወረዳዎች ከተጎበኙ ኢንተርፕራይዞች አባላት መካከል በሰጡት አስተያየትም በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በማመን ተደራጅተው ወደ ስራ መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።
ከመንግስት በኩል የመስሪያና መሸጫ ቦታ፣ የገበያ ትስስር እንዲሁም ሌሎችም ድጋፎች እንደተደረገላቸው በመጥቀስ ከዚህ ጎን ለጎንም የአደይ ፕሮግራም የክህሎት ስልጠናና የግብአት አቅርቦት ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል።
በቀጣይ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር ጠንክረው እየሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፣ መሀመድ ሽሁር

More Stories
በሩብ ዓመቱ 3.7 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወሰነች ቶማስ ገለጹ
የማር ምርት እጅግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በጎምቦራ ወረዳ በንብ ማነብ ስራ የተሠማሩ አርሶአደሮች ተናገሩ
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ የግብርና ልማት ላይ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተገለጸ