ኢትዮጵያ በሞስኮ
በኢያሱ ታዴዎስ
ሁሉም ነገር በአጋጣሚ የሆነ ነው የሚመስለው፡፡ 1 ሜትር ከ67 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ አትሌት የ10 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድሩን ሊያደርግ በተጠንቀቅ ቆሟል፡፡ የጅማሬውን ማብሰሪያ የተኩስ ድምፅ እስከሚሰማ ተጣድፏል፡፡
አትሌቱ በዚያ መድረክ ይገኝ እንጂ የሩጫውን ዓለም እቀላቀላለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡ በቅጡ እንኳን እንደ ሌሎች አትሌቶች ከልጅነቱም በሩጫ ተኮትኩቶ አላደገም፡፡ የተለየ የሚባል ልምድም የለውም። ብቻ የሚያስታውሰው ነገር ቢኖር ከዓመታት በፊት የፋብሪካ ሰራተኛ እንደነበር ነው፡፡
አትሌቱ የፋብሪካ ሥራውን በቀጠለበት ሁኔታ ወደ ድንገተኛ ጥሪው አዘነበለ፡፡ በአውሮፓዊያኑ 1968 ለሚካሄደው የሜክሲኮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅትም አትሌቱ ወደ ቡድኑ አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ቀርቦ “እኔም መሳተፍ እፈልጋለሁ” ሲል ጠየቀ፡፡
የአትሌቱ ድንገተኛ ጥያቄ ያስደነገጠው አሰልጣኙም ቡድኑ ውስጥ ቀላቅሎት ወደ ሜክሲኮ ሊወስደው ቢፈልግም የአትሌቱ ምኞት መሳካት የቻለው ግን ወዲያው አልነበረም፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ በተካሄደው የ1972 የሙኒክ ኦሎምፒክ እንጂ።
በሙኒኩ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ በተሳተፈበት በ10 ሺህ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ማጥለቅ ቻለ፡፡ ለሩጫው ዓለም እንግዳ ቢሆንም ሁሉም ነገር በፍጥነት እየሆነ ነው፡፡ ከዚያም ተራው የ1980ው የሞስኮ ኦሎምፒክ ሆነ፡፡
አትሌቱ በዚያች ታሪካዊ ቀን በሞስኮ ሴንትራል ሌኒን ስቴዲየም የመሮጫ ሜዳ ላይ ተሰየመ፡፡ አትሌቱ አሁንም ቢሆን የተለየ የተመልካች ትኩረት አላገኘም፡፡ አጭር ቁመናው፣ ቀጠን ያለ ተክለ ሰውነቱና ራሰ በራነቱ ደግሞ ትኩረት ላለማግኘቱ ምክንያቶች ነበሩ፡፡
እርሱ ግን የሆዱን በሆዱ ይዞ በሩጫው ሜዳ ተሰየመ፡፡ አብረውት ከሚሮጡ የሀገሩ ልጆች መሃመድ ከድር እና ቶሎሳ ቆቱ ጋር እየተፈራረቀ ዙሩን ለማክረር ሞከረ። 22 ደቂቃ ሮጠው 5 አትሌቶች ለብቻቸው ሲነጠሉ፣ ሶስቱ ኢትዮጵያዊያን አብረው ነበሩ።
በተለይም መሃመድ ከድር ከፊት እየቀደመ ዙሩን በማክረርና ሌሎቹን በማዳከም በኩል የሰራው ሥራ አስደናቂ ነበር፡፡ በመጨረሻም ከመካከል እንደሚዳቋ የተስፈነጠረው ያልተጠበቀው ያ አትሌት ፍጥነቱን ጨምሮ 27፡42.69 በመግባት ቀዳሚ ሆኖ ጨረሰ፡፡
በሞስኮ ኦሎምፒክ የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድርም ኢትዮጵያ ብርቱና ጀግና አትሌት ወለደች፤ ምሩጽ ይፍጠርን፡፡ አትሌቱ ድሉን ተከትሎ የኢትዮጵያን ዝና በመድረኩ ከፍ አድርጎ አስጠራ፡፡ ብዙዎችም በአድናቆት እጃቸውን አነሱለት፡፡
ታዲያ በምሩጽ ይፍጠር ፊት አውራሪነት ወደ ውጤት የመጣው የኢትዮጵያ የስፖርት ልኡክ በተሳተፈባቸው የውድድር ዓይነቶች ፍልሚያውን ቀጠለ፣ በዚሁ በሞስኮ ውድድር፡፡ አስቀድሞ በተካሄደው የ10 ሺህ ሜትር የወንዶች የሩጫ ውድድር ለምሩጽ ድል ትልቅ ሚና የነበራቸው መሃመድ ከድር እና ቶሎሳ ቆቱ እንደየቅደምተከተላቸው 3ኛ እና 4ኛ መውጣት ችለው ነበር፡፡
የ10 ሺህው ግለት በ5 ሺህ ሜትር ውድድርም ቀጠለ፡፡ ምሩጽ ይፍጠር እና መሃመድ ከድር ከሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ዮሃንስ መሃመድ ጋር በመሆን በፍልሚያው ተፋጠጡ፡፡
ከምሩጽ ጋር የተሰለፉት ኢትዮጵያዊያኑ የቡድን ሥራው ላይ በርትተው ቢሰሩም እስከመጨረሻው በመሪነት ሊዘልቁ አልቻሉም፡፡ ይህ ግን ምሩጽን አላደከመውም። እነሱን ሳይጠብቅ ከታንዛኒያዊ እና ከፊንላንዳዊ አትሌት ጋር በብርቱ ተፎካክሮ በቀዳሚነት ጨረሰ፡፡ 13፡21.0 የገባበት ሰዓቱ ነበር፡፡
በዚሁ 5 ሺህ ሜትር ላይ የተወዳደሩት ዮሃንስ መሃመድ እና መሃመድ ከድር እንደየቅደም ተከተላቸው 10ኛ እና 12ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ፡፡
የምሩጽ ድል ለኢትዮጵያዊያን የተለየ ነበር፡፡ አንድ አትሌት በተሳተፈባቸው 2 የሩጫ ውድድሮች በአንደኝነት ሲወጣ በታሪክ የመጀመሪያው ነበር፡፡ ይህንንም ማሳካት የቻለው ምሩጽ ነበር፡፡
ከምሩጽ ድል ሌላ መሃመድ ከድር በ10 ሺህ ሜትር፣ እንዲሁም እሸቱ ቱራ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር ያሳኩት የነሃስ ሜዳሊያ ኢትዮጵያ በጥቅሉ 4 ሜዳሊያዎችን ሃገራችን እንድትሰበስብ አስችሏታል፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያ ለዚሁ ውድድር ባልተለመደ መልኩ የላቀ ትኩረት ሰጥታ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚሁ ደግሞ ማሳያው ያሳተፈቻቸው አትሌቶች ቁጥር መብዛት እና በተለያዩ የውድድር ዓይነቶች መቅረቧ ነው፡፡
39 ወንዶች እና 2 ሴቶች በጥቅሉ 41 ስፖርተኞች በ3 የስፖርት ዓይነቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ አትሌቲክስ፣ ቦክስ እና ብስክሌት የተወዳደሩባቸው የስፖርት ዓይነቶች ነበሩ፡፡
በውድድር ዓይነቶች ስንመለከት ደግሞ በወንዶች 100 ሜትር፣ 200 ፣ 800 ፣ 1 ሺህ 500 ፣ 5 ሺህ ፣ 10 ሺህ ሜትር፣ ማራቶን፣ 400 ሜትር ዱላ ቅብብል፣ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል፣ ከፍታ ዝላይ፣ የምድር ዝላይ፣ የጦር ውርወራ እና 20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድሮች ነበሩ፡፡
በቦክስ ስፖርት በ48 ኪሎ ግራም፣ በ51 ኪሎ ግራም፣ በ54 ኪሎ ግራም፣ በ57 ኪሎ ግራም፣ በ60 ኪሎ ግራም እና በ63 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ስፖርተኞችን አሳትፋለች። በብስክሌት ደግሞ በግል እና በቡድንም እንዲሁ ስፖርተኞችን አሳትፋለች፡፡ በሴቶች ተሳታፊ የሆኑት ፋንታዬ ሲራክ በ800 ሜትር፣ እንዲሁም አምሳለ ወልደ ገብርኤል በ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድሮች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህን ስፖርተኞች በመድረኩ ብታሰልፍም የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት የቻለችው በምሩጽ ይፍጠር ብቻ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ከሞስኮው ኦሎምፒክ ተሳትፎ ብዙ መማር የተቻለ ይመስላል። በተለይም በተሳትፎ ረገድ የኦሎምፒክ ውድድር እንዳሁኑ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ከማስቆጠሩ በፊት ሰፋ ባለ መልኩ መሳተፍ መቻሉ ትልቅ ልምድ የሚወሰድበት ነው፡፡
ይህ ሲታሰብ ደግሞ ከአሁኑ ጋር ለንጽጽር ከቀረበ ወደ ኋላ ሳንጓዝ እንዳልቀረ እንገነዘባለን፡፡ የሞስኮ ኦሎምፒክ ከተካሄደ አሁን 44ተኛ ዓመቱ ላይ ነው፡፡ ከ44 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ተሳትፎዋ ከተወሰኑ የውድድር ዓይነቶች የዘለለ አልሆነም፡፡ ትኩረት የተደረገባቸውም ጥቂት የስፖርት ዓይነቶች ብቻ ናቸው፡፡ ታዲያ ለምን ወደ ፊት መጓዝ አቃተን? ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ነው፡፡
More Stories
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 6ኛ ዙር መርሐግብር 9 ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ
“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
እርቅ