ወፍራም የሚባሉ ሰዎች ክብደታቸው ስንት ነው?
በፈረኦን ደበበ
አሁን አሁን ከህጻናት ጀምሮ በበርካቶች ላይ የሚታየው ውፍረት በአብዛኛው ሰው ዘንድ ከኑሮ መደላደልና መመቻቸት ጋር የተያያዘ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ በተለይ ጥሩ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች የአመጋገብ ሁኔታውን በማሻሻላቸው ምክንያት በሰውነት ቅርጻቸው ላይ ለውጥ ስለሚያሳዩ፡፡
ከማህበራዊ ጠቀሜታ አንጻርም ሲታይ ጥሩ የሰውነት ቅርጽ እንደ ጸጋ ሲታይ በብዙዎች ዘንድ የውበት መገለጫም ሆኖም ይታያል፡፡ ምንም እንኳን ይዞ የሚያመጣቸው በሽታዎችና የጤና ችግሮች አሁን አሁን ቢበዙም፡፡
ምክንያቱም ከሰዎች የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ተነስቶ በርካታ የጤና ችግሮችንም ስለሚያመጣ፡፡ ወፍራም ሰዎች ለመራመድ፣ ለመተንፈስና ለመሥራት መቸገራቸውም የሚያስከትላቸው ውጣ ውረዶችን ያሳያል፡፡
እንደ ስኳርና ሌሎች የበሽታ ዓይነቶችን ስለሚያመጣ አይመከርም፡፡
ሰዎች በአይን አይተውና በእጃቸው ዳስሰው መረዳት የሚችሉት የዚህ የጤና ችግር ሌላው ማሳያ መጠኑን ማወቅ ሲሆን ይህንን በተመለከተ ሰሞኑን ቢቢሲ ዜና ይፋ ባወጣው ዘገባ ይፋ ተደርጓል፡፡ ወፍራም ሰዎች የሚኖራቸው የክብደት መጠን መገለጹም ግንዛቤን በማሳደግ ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
በኢጣሊያ ሀገር የተካሄደውን ጥናት ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ እንዳስታወቀው ከሆነ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶችና አረጋዊያን በስህተት እራሳቸውን ወፍራም እንዳልሆኑ እንደሚገልጹ የተብራራ ሲሆን ይህንንም የሚሉት የሰውነታቸውን የስበት ክምችት እንጂ ክብደትና ቁመታቸውን ከግንዛቤ ባለማስገባት እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡
እንደ ባህልም ቢታይ አንድ ሰው ወፍራም ወይም ቀጭን እንደሆነ በማየት ብቻ መለየት የሚቻል ቢሆንም ቁመትና ክብደትን ጨምሮ መለካት እንደሚገባም ነው የተጠቆመው። ምክንያቱም ውፍረት አንድ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሰውነት ቅርጾችን የሚያካትት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፡፡
ገለጻውን ሲቀጥል ዕድሜ በጨመረ ቁጥር የጡንቻ ዝለት የሚከሰትና ስበትም በወገብ አካባቢ ባሉ የሰውነት ክፍሎች ይከማቻል ያለው የመረጃ ምንጫችን ክብደት ደግሞ ባለበት ይቀጥላል ብሏል ይህንን ለመለካት ተመራጭ የሆነውን ዘዴ ሁሉ በመጠቆም፡፡
የአንድን ሰው ትክክለኛ ክብደት ማወቅ የሚቻለው ክብደቱን ለሰውነቱ ቁመት በማካፈል እንደሆነ ያወሳው ጥናቱ በዚህ ተገቢ የሚባለውን የሰውነት ክብደት ማግኘት መቻሉንም ጠቁሟል፡፡ ከ18.5 እስከ 25 ኪሎ ግራም ጤናማ፣ ከ25 እስከ 29 ኪሎ ግራም ከመጠን ያለፈ ክብደትና እንዲሁም 30 ኪሎ ግራምና ከዚያ በላይ ውፍረት መሆኑን በማስታወቅ፡፡
ይህ መለኪያ በዓለም ጤና ድርጅት የጸደቀና ትክክለኛ የተባለለት ሲሆን ያለበት ክፍተትም ደግሞ የስበት፣ ጡንቻና የአጥንትን ተጽዕኖ መለየት አላስቻለም የሚለው ነው፡፡ በጣሊያን ሮም ከተማ በሚገኘው ቶራ ቫርጌታ ዩኒቨርስቲ የተደረገው ይህ ጥናት ከ40 እስከ 80 ዓመት በሆኑ ጎልማሶች ላይ የተካሄደ ሲሆን ጠቅላላ 4 ሺህ 800 ከሚሆኑ ሰዎችም የቃለ መጠይቅ መረጃ ወስዷል፡፡
የዓለም ህዝብ ከፍተኛ ትኩረት በሆነው የጤና ችግር ላይ የተደረገው ጥናት በመጨረሻ ወደ አውሮፓ ፓርላማ የቀረበ ሲሆን ከዚያ በፊት 38 በመቶ የሚሆኑ ወንዶችና 41 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በመለኪያው ከ30 በመቶ በላይ ሆነውም ተገኝተዋል፡፡ በተከታታይ 71 እና 64 በመቶ ወፍራም መሆናቸው ስለተረጋገጠ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትን መለኪያ ተግባራዊ ማድረግ ሊያስከትል የሚችለውንም ችግር የጥናቱ ተባባሪ አዘጋጅ የሆኑት ፕሮፌሰር አንቲኒዮ ደ ላሬንዞ ገልጸዋል፤ በቀጣይ ልንገባ እንችላለን ያሏቸው ችግሮችን ሁሉ በመጠቆም፡፡
በመስፈርቱ አጠቃቀም የምንቀጥል ከሆነ በርካታ ጎልማሶችና አዛውንቶችን እናጣለን ብለው ትችት ያቀረቡት ፕሮፌሰሩ ከውፍረት ጋር ለተያያዙና እንደ ስኳር አይነት- እንዲሁም ለልብ ህመምና ካንሰሮችም ተጋላጭ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
የሰውነት ክብደት መለኪያ የሆነው 27 ኪሎ ግራም ለወደፊት የሚሰጠው ጠቀሜታ በተመለከተም ማሳሰቢያቸውን ሲሰጡ ለክሊኒካዊ አገልግሎትና ለውፍረት መለኪያነትም ያገለግላል ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሎሬንዞ ወደፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎልማሶች ህይወት መታደግ መቻሉንም በማስታወቅ፡፡
ተመራማሪዎች አሁን ይፋ ባደረጉት የሰውነት ክብደት መለኪያና በነባሩ አስተሳሰብ ሰፊ ልዩነት እንደሚታይ በሚገለጽበት በአሁኑ ጊዜ “ቦዲ ማስ ኢንደክስ” የተባለው የክብደት መለኪያ ከሌሎች ዘዴዎች እርካሽና ያረጀ ተብሎ እንደማይጣልም ነው የተነገረው፡፡
የተገኘውን ውጤት ለማጽናት ከዚህ ከፍ ያሉ ጥናቶች በሌሎች ሀገራትም መካሄድ እንዳለባቸው የገለጹት ተመራማሪዎቹ ጥናቱ በኢጣሊያ አንድ አካባቢ የተካሄደና በሰዎች አካላት ላይ ያለ የስበት መጠን ያለመዳሰሱም እንደ ውስንነት ተነስቷል፡፡
በዓለም ላይ ብዙ ሰዎችን ለጉዳት እየዳረገና ለመለካት አስቸጋሪ በሆነው የጤና ችግር ጥናት ላይ የሚነሳው ሌላ ትችት የሰዎችን ዕለታዊ አመጋገብ ልማድ ያለመዳሰሱና ስለ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለማንሳቱ ሲሆን የሰውነት የስበት መጠንም ትክክለኛ መለኪያ እንደሆነ ያለማስቀመጡ አወዛጋቢ አድርጎታል፡፡
እነዚህ ችግሮችን በማንሳት ነው የጥናቱ ተባባሪና የሞደና እና ሪጎ ኢሚሊያ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ማርዋን ኤል ጎቺ የተናገሩት። በገለጻቸው ውፍረትን ለመለካት ቀላልና ማንም ሊያገኝ የሚችል ዘዴ መጠቀም አስፈላጊ ነው ሲሉም ነው ያስታወቁት፡፡
የሰዎች ጤናማ አኗኗር ጠንቅ የሆነውን ውፍረት ለመለካት የሚደረገው ጥረት ትኩረት ማስፈለጉን ያወሱት ሌላው ባለሙያ የግላስጎ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ነቫዲ ሳታር ሲሆኑ ከላይ የተገለጸውንና የዓለም ጤና ድርጅት አጽድቆታል የተባለውን መሥፈርት ለማሻሻል ማሰባቸው ልዩ ያደርጋል፡፡
የውፍረት መጠን የመጨረሻ መለኪያ 27 ኪሎ ግራም አድርጎ መወሰኑ ችግር እንዳለበትና ይህም በእንግሊዝ ወፍራም ተብለው የሚታወቁ ግማሽ ጎልማሶችን ብቻ እንደሚይዝ ጠቁመው ሌሎች ተመራጭ መሥፈርቶችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም ነው ያስቀመጡት፡፡
ትክክለኛ መለኪያ መሥፈርት የማግኘቱ ጥረት ባልተቋጨበት በአሁኑ ጊዜ ላይ ሆነው ሲናገሩ እንደ ወገብና ዳሌ ስፋት፣ አንዳንድ ከመጠን ያለፉ የክብደት ምልክቶችና ሌሎች መሥፈርቶችን ማካተት ጠቃሚ ይሆናል በማለትም ነው ሀሳባቸውን የሚያጠቃልሉት።
በእርግጥ ውፍረት በርካታ ማህበራዊና ባህላዊ ገጽዎችን ያካተተ የጤና ችግር ቢሆንም በዓለም ላይ ብዙ ሰዎችን ለስቃይ እየዳረገ መሆኑ አንገብጋቢ ያደርገዋል፡፡ አሁን አሁን ከህጻናት ጀምሮ ሰለባ ማድረጉም አሳሳቢነቱ ምን ያህል እንዳደገ ያመለክታል፡፡
በዓይን ታይቶ በእጅ ከሚዳሰሰው ውጭ ችግሩን ለመለየት እንዲቻል ከላይ ተመራማሪዎች ያቀረቡት የጥናት ውጤትም በርካታ ጥቅሞችን ያካተተ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም መንስኤውን ለማወቅ ከማገዝ ባለፈ ትክክለኛ የሆነ መለኪያ ለማወቅና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግም ስለሚረዳ፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው