ፊጋ ሰው

በይበልጣል ጫኔ

ሠላም ተወዳጆች እንዴት ናችሁ? በዓል እንዴት አለፈ? ለነገሩ እስከ ዳግም ትንሳኤ ድረስ ከዘመድ መጠያየቁ÷ አክፋይ መውሰዱ እና መሰል ነገሮች ሳምንቱን ሙሉ በበዓል ድባብ ውስጥ እንድንቆይ ያደርጉናል።

አሁን ግን አክፋይ አለ?!÷ የዘንድሮ ነገር እኮ አስቸጋሪ ነው። በዓልን እንደምንም የዋለ ሰው÷ በማግስቱ ዘመድ ጥየቃ ቢሉት የሚሰማ አይመስለኝም። ማጣታችንን እንዳያሳብቁብን÷ አያስፈልጉም ብለን የተውናቸው እሴቶቻችን አንድ እና ሁለት አይደሉም። አሁን ላይ አክፋይም ያንን አይነት ዕጣ ፈንታ እየገጠመው ያለ ይመስለኛል።

ድሮ ድሮ ዳግም ትንሳኤ ሲሆን÷ ወጪ ወራጁ ሁሉ አንዳች ነገር አንጠልጥሎ ቤተሰብ ጥየቃ መንገዱን ይሞላው ነበር። “አንጠልጥሎ” ስል ነገሩን እንዳላቀልባችሁ እሰጋለሁ። በዚያ ጊዜ አክፋይ ተይዞ ሲኬድ ዶሮው ተሰርቶ፣ ዳቦው ተደፍቶ፣ ውስኪው ተይዞ ነበር። የዶሮው ነገር ያልሆነለት አሊያም ስራ የበዛበት ደግሞ÷ ከውስኪው እና ከዳቦው ጋር ሽንጠ ረዥም በጉን ስቦ መሄዱ እንግዳ ነገር አልነበረም። በእርግጥ ዶሮውም እያለ ቢሆን÷ በግ ደርበው የሚወስዱ አይታጡም።

እዚህ ጋ ግን÷ እንደዋዛ ይኼን ሁሉ ነገር ማድረግ የሚችሉ ሰዎች÷በዚያ ዘመን  በኑሮ ውድነት ይማረሩ እንደነበር ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። “ደግሞ ምን እያሉ ይሆን የሚማረሩት?” የሚል ጥያቄ ካላችሁ፦

“አንድ ሊትር ዘይት አምስት ብር እየተሸጠ እንዴት ነው የምንኖረው?”

“በግ 70 ብር አወጣ?!÷ ይኼ’ኮ ጥንድ በሬ የሚገዛበት ዋጋ ነበር”

እና መሰል ነገር ይሉላችኋል።

“ያምናን ቀን አማሁት ላ’ፌ ለከት የለው

የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው”

ያለው ማን ነበር?÷ ማንም ይበለው ግን የዘመናችን መልክ እነዚህ ሁለት ስንኞች ውስጥ አለ።

አንዲት ወዳጃችን ከበዓል ማግስት ስለቅርጫ አንስታ ስታወጋን ነበር። ይህቺ ሰው ኑሮዋ ባህር ማዶ ነው። እንደ ዋዛ የመኪና ዋጋ ስለሚጠራበት የጅሩ ሰንጋ መስማቷ ነው÷ ለጨዋታዋ መነሻ የሆናት።

ድሮ ድሮ የበሬ ስጋ ቅርጫ÷ አቅም ለሌላቸው ሰዎች የተዘየደ መላ ነበር÷ ባይ ናት። አሁን 500 ሺህ አሊያም 600 ሺህ የበሬ ዋጋ ከሆነ÷ ድኃ ምኑን በላው?

“በዚህ ሁኔታ …” ትላለች÷ የባህር ማዶዋ አጫዋቻችን

“በዚህ ሁኔታ በዓልን ፈታ ብላችሁ አሳልፉበት ብዬ ለቤተሰቦቼ የላኩት ገንዘብ÷ አንኳን ፈታ ሊያደርጋቸው ከቅርጫ የሚያልፍ አይመስለኝም”

እንደው ለጨዋታው ድምቀት አነሳሁት እንጂ÷ ድኃው መጀመሪያውኑ  እንዲህ ያለ ቦታ አይሄድም። በስህተት እንኳን ከሄደ÷ እንዳልሰማ ሆኖ፦

“አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው

ታላቅ ችሎታ ነው”

የሚለውን ዘፈን በፉጨት እያንጎራጎረ ወደ ቢጤዎቹ መመለሱ አይቀሬ ነው። በእርግጥ አሁን ላይ እንደ አቅም የሚቆሙበት እና የሚገበያዩበት ሥፍራ ማግኘትም ቀላል ድል አይደለም። ለምን ቢሉ÷ በዘንድሮ ገበያ ሚዛን የአብዛኛው ሰው አቅም÷ ከአቅም በታች መሆኑ እየታየ ነው።

ስለ ገበያ እና ገበያተኛ ካነሳን አይቀር÷ ስለ አንድ አጋጣሚ ላውጋችሁማ። በዘንድሮው ፋሲካ የመጨረሻ ገበያ÷ ሰዉ ነቅሎ ገበያ ተገኝቷል። አንድ በሬ ለመግዛት አምስትም አስርም እየሆኑ የሚመጡ ሰዎች ስላሉ÷ በገበያው መሃል ከከብቱ ቁጥር ይልቅ የሰዉ ቁጥር ልቆ ይታያል።

በዚህ መካከል አንድ በሬ አመል አወጣ። ገበያተኛውን ሁሉ ካልፈጀሁት አለ። ድንገት አይኑን አጉረጥርጦ÷ ቀንዱን አሹሎ መሮጥ ሲጀምር ሰዉ ግርርርር ብሎ ያመልጣል። ተመልሶ መሃል ለመሃል ሲመጣ÷ ሰዉ ለሁለት ይከፈላል። በሬውን እንኳን ሌላው ሰው ባለቤቱ ፈራው።

በዚህ መሃል ገበያ የቀናው እየሸጠ መውጣት ጀመረ። “ፊጋ” በሬ የያዘውን ነጋዴ ግን ለአፍ እንኳን “ዋጋው ስንት ነው?”÷ የሚለው ሰው አላገኘም።

ደግሞ ወደ አንዱ ጥግ÷ የከብት ባህሪ የሚያውቁ ደፋሮች የአቅም ነገር ዳር አቁሟቸው የሚሆነውን ሁሉ እያዩ ነበር። ሄደው ጠየቁት÷ ባለበሬውን። ሰውዬው በመጠየቁ ብቻ የሸጠ ያክል ደስ አለው።

ሰውዬው ከብት እየነዳ መጥቶ÷ አውሬ ይዞ መመለስ ስላልፈለገ÷ ሰዎቹ በገመቱለት ሸጠላቸው። ጤናማ ቢሆን ይሸጥ ከነበረበት ግማሽ ያክል ወርዶ።

ገዢዎቹ አንድም በጥበብ÷ አንድም በድፍረት በሬውን አሰሩት። ለነገሩ አሰሩት ከማለት ይልቅ ተበተቡት ማለት ይቀላል። የበሬውን አራት አግሮች በአራት የተለያዩ ገመዶች አስረው ሊያምኑት ስላልቻሉ÷ ቀንዱ ላይም ሌላ ገመድ አጥልቀዋል። እንዲያ አድርገው ቤት አደረሱት። በዚያው ገመድ ጠልፈው አረዱት።

“መማር ለወደደ አስተማሪ የትም ይገኛል” እንዲሉ÷ እኔም ከዚያ የበዓል ገበያ ትልቅ እውቀት ገብይቼ ተመለስኩ። አንተም መማር ከወደድክ እንዲህ እልሃለሁ፦

ወዳጄ ፊጋ አትሁን። ፊጋ በመሆንህ እንደበሬው ዋጋህን ትሰብር ይኾናል እንጂ÷ ምንም አትፈይድም። በእርግጥ ለጥቂት ጊዜ ትፈራ ይሆናል። በከብቶች መሃል የቆመው ፊጋ በሬ እንደ አንበሳ እንደተፈራው ማለት ነው። ፊጋነት ልዩ ምልክቴ ነው ካልክ ደግሞ÷ ምናልባት ጥቂቶች ላይ ጉዳት ታደርስ ይሆናል። እንደ በሬው አራት እግርህን እና ቀንድህን ከተያዝክ በኋላ ግን ወደ መታረጃህ እየተነዳህ እንደሆነ እያወቅክ እንኳን÷ ምንም አታመጣም። ካራ ሲያርፍብህ ነብስ ይዞህ ብትጮህም÷ የወጋኸው አሊያም ያስበረገግኸው ሰው እሰይ ይል እንደሆን እንጂ÷ ሊረዳህ አይመጣም።