በአለምሸት ግርማ
መምህርት አይናለም ወልደ አማኑኤል ይባላሉ። ትውልድና ዕድገታቸው አዲስ አበባ ከተማ ነው። ከመደበኛ ትምህርታቸው እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ እዚያው አዲስ አበባ የተማሩ ሲሆን በመምህርነት የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል።
ትዳር መስርተው ኑሯቸውን ደብረ ዘይት ከተማ አደረጉ። በደብረ ዘይት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በፊዚክስ መምህርነት ለ30 ዓመታት አገልግለዋል። ከትዳራቸው 6 ልጆችን ማፍራት ችለዋል። ልጆቻቸውም በትምህርታቸው ጎበዞች ስለነበሩ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በስራ ላይ ይገኛሉ።
መምህርት አይናለም በ1997 ዓ.ም ነበር ወደ ሃዋሳ የሚመጡበት አጋጣሚ የተፈጠረው። ልጃቸው የጀመረችውን የሆቴል ስራ ለማየት ነበር የመጡት። በወቅቱ ከመጡበት አላማ ውጭ የሆነ ነገር በህይወታቸው ተከሰተ።
የመጀመሪያውን አጋጣሚ እንዲህ በማለት ነበር ያጫወቱን፦
“ጠዋት ጠዋት ሆቴል በረንዳ ላይ ተቀምጬ ስመለከት አንድ ትንሽዬ ልጅ ወደ ሃይቅ ሲወርድ አየሁ። አመሻሽ ላይ ደግሞ ወደ ላይ ይመለሳል። ስከታተል ገብርኤል አካባቢ እንደሚኖር ተረዳሁ። እኔም ገብርኤል እሔድ ነበር። ትኩረቴን የሳበው ትንሽነቱ እና ጥንቃቄው ነበር። በዚህ ሁኔታ እሱን መከታተል ቀጠልኩ፤ አቅርቤ ለማነጋገርም ወሰንኩ። አንድ ቀን “ቤተሰብ የለህም?” ስል ጠየኩት። አሉ አለኝ። እንዲያገናኘኝ ጠየኩት። ለማገናኘት ፈቃደኛ ነበር። በዚህ ተስማምተን ቤተሰቡን ልተዋወቅ ስሄድ የገጠመኝ ነገር ከገመትኩት በላይ ሆነብኝ። በጎዳና የሚኖሩ ይሆናሉ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ያጋጠመኝ ግን ወላጆቹ በጎዳና በሸራ ዳስ ውስጥ ሆነው ነው። ይህም ለልጁም ይበልጥ እንድሳሳ አደረገኝ። ከዚያም ወደ ቤቴ አመጣሁት ከእኔም ጋር አሳደርኩት። ቤተሰቦቹን በሽማግሌ አግባብቼ ልጁን እንዲሰጡኝና እንዳስተምረው ተነጋግረን ተስማማን። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ልጄ ሆነ። አሁን ላይ በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት ተማሪ ነው። እረፍቱን እኔ ጋር ነው የሚያሳልፈው።”
ከዚህ ነበር የጀመረው አዲሱ የህይወታቸው ምዕራፍ። ቀሪ ህይወታቸውን በሃዋሳ ከተማ ፈጣሪ በአደራ ከሰጣቸው ልጆቻቸው ጋር ለማድረግ ወሰኑ። ከዚያም በተመሳሳይ መንገድ በትክክል የተቸገሩና አማራጭ የሌላቸውን ልጆች አንድ፣ ሁለት እያሉ ቁጥራቸውን ጨምረው ማሳደግ ጀመሩ። ልጆቻቸውን ለማሳደግ ቤት ተከራዩ።
ስራቸው እየሰፋ ሲሄድ እውቅና ማግኘት እንዳለባቸው ተነገራቸው። በዚህም መሰረት የአካባቢው ሰዎች ባደረጉላቸው መልካም ድጋፍ በ2003 ዓ.ም “ቤተሰብ በጎ አድራጎት ማህበር” በሚል ስያሜ ህጋዊ እውቅና ተሰጣቸው።
በአሁኑ ወቅት ራሳቸው ከሚኖሩበት ቤት በተጨማሪ አራት መኖሪያ ቤቶችን ተከራይተው ልጆችን እያሳደጉ ይገኛሉ።
በስራ ላይ የገጠመዎት አሳዛኝ ገጠመኝ ካለ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ እንዲህ ሲሉ መልሰውልናል፦
“በስራ ላይ ትልቁ ፈተና ብዬ የምለው የልጆች ህመም ነው። ልጆች ሲታመሙ ይጨንቀኛል። በተለይ በአንድ ወቅት የተጣለች ልጅ ወደ እኛ ሲያመጡልን ልጅቷ በእጅጉ ታማ ነበር። ከነህመሟ ነበር የተቀበልናት። ትድን ይሆን? ወይስ? የሚለው ጥያቄ በወቅቱ በእጅጉ ፈትኖኝ ነበር። ነገር ግን እዚህ ሃዋሳ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ጭምር ወስጄ አሳክሜያታለሁ። ፈጣሪ እረድቶኝ ድናልኛለች። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ከዚህ ውጭ የከፋ ገጠመኝ የለኝም።”
በአሁኑ ሰዓት 92 ልጆችን በማሳደግ ላይ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 7ቱ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል። በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ደጋግመው ይናገራሉ። በተለይም አንዳንዶቹ ልጆች በከፍተኛ ውጤት ነው ከክፍል ወደ ክፍል የሚያልፉት። በልጆቹ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸውም አጫውተውናል።
እነዚህ ልጆች ይህንን ዕድል በማግኘታቸው ከነበሩበት ህይወት በመውጣት ወደ ተሻለ ህይወት መግባት የቻሉት በእኚህ ልበ ቀና ሴት አማካኝነት ነው። ይህም ለብዙዎች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው።
ልጆቹን ለማሳደግ ሲነሱ አንዳንዶች ይቅርብሽ፣ ስራው አድካሚ ነው ብለዋቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ። ነገር ግን “ወደ ልቤ የመጣውን እውነት እንዴት እምቢ እላለሁ” በማለት ወደ ስራቸው ጠልቀው ገብተዋል። ዛሬ ላይ ባሳደጓቸው ልጆች ለውጥ የሚያገኙትን ደስታ በምንም እንደማያገኙት ይናገራሉ።
ልጆቹን የሚያስተዳድሩበት የገቢ ምንጫቸው ምን እንደሆነም ጠይቀናቸው እንዲህ ሲሉ መልሰውልናል፦
“የጀመርኩት በዝግጅት አልነበረም። ስለዚህ እንደ ልጆቼ ባለኝ ነገር ላሳድግ ነው የጀመርኩት። በሂደት ስራው እየሰፋ ሲሔድ ግን ለልጆቹ የሚያስፈልገው ወጪም እየጨመረ መጣ። የሚያስፈልገኝን ወጪ ለመሸፈን ደብረ ዘይት የሚገኘውን የራሴን ቤት አከራይቻለሁ። ልጆቼም፣ መጥተው የምሰራውን የሚያዩ ሰዎችም ይደግፉኛል። በተለይም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎችም በተለያየ መንገድ ድጋፍ ያደርጉልኛል። ለምሳሌ፦ የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ከነሙሉ ዕቃው ከውጭ ሀገር ተበርክቶልኛል። በዚህም ከዳቦ ሽያጭ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ማግኘት ችለናል። እንጀራም በማስጋገር ለሽያጭ እናቀርባለን። የከብት እርባታም እየሰራን ነው፤ የወተት ሽያጭም ጀምረናል። እንዲሁም የሽመና ስራ በመስራት ለገበያ እናቀርባለን። በተለይም ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ወዳጆቼ ምርቶቹን ወስደው በመሸጥ ዶላሩን በመላክ ያግዙኛል። በልጄ ሆቴል ውስጥ የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ አለን። ማንኛውም ሰው የባህል አልባሳቱን በመግዛት ድርጅቱን መደገፍ ይችላል። በነዚህ ነው ወጪያችንን የምንሸፍነው።”
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለልጆች መኖሪያ ቤት የፅዳት ስራ፣ የምግብ ዝግጅትና መሰል ስራዎች የሚያከናውኑትም ከጎዳናና ከልመና ህይወት የወጡ እናቶች መሆናቸውንም አጫውተውናል። በዚህም ለብዙዎች የስራ ዕድልን መፍጠር ችለዋል። ነገር ግን ከጎዳና በቀላሉ ወደ ስራ ማምጣት አይቻልምና አልከበድዎትም ወይ? ስንል ጥያቄ አንስተንላቸዋል፦
“እነዚህ ሴቶች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት ሁልጊዜ በቤተክርስቲያንና በሚገኙበት ስፍራ በመሔድ ከእነሱ ጋር ቁጭ ብዬ ቆይታ አደርጋለሁ። ያሉበት ህይወት አስከፊ መሆኑን እነግራቸዋለሁ። መቀመጤን ያዩ አንዳንድ ሰዎች ለእኔም ጭምር ብር ይጥሉልኝ ነበረ። ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ ሃሳቤን ተቀብለው ወደ ስራ መግባት ችለዋል። በአሁኑ ሰዓት ህይወታቸው ተለውጦ አዲስ ህይወትን እየመሩ ይገኛሉ።”
በቀጣይም የጀመሩትን የሽመና ስራ ወደ ኢንደስትሪ የማሳደግ ዕቅድ አላቸው። እንዲሁም ወጣት ሴቶች አጫጭር የሙያ ስልጠና የሚያገኙበትንና ወደ ስራ የሚሰማሩበትን መንገድ ማመቻቸትም ሌላኛው የዕቅዳቸው አካል ነው።
ለዚህ ዕቅዳቸው ስኬት ትልቁ እንቅፋት የሆነባቸው የቦታ ችግር ነው። ከውጭ ሀገር ድጋፍ የሚያደርጉላቸው አካላት ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው። ነገር ግን ለስራው የሚሆን ቦታ ስለሌላቸው ሊፈፀምላቸው አልቻለም። “የሚመለከታቸው አካላት ስራዬንና ዓላማዬን በማየት የስራ ቦታ የማገኝበትን ድጋፍ ቢያደርጉልኝ መልካም ነው” ብለዋል።
መምህርት አይናለም በስራቸው ደስተኛ መሆናቸውንና የመንፈስ እርካታን እንደሚያገኙ ይናገራሉ። መተጋገዘ ካለ ሁሉም ነገር ቀላል ነው የሚል እምነት አላቸው። ከሚያሳድጓቸው 60 የሚሆኑት ቤተሰባቸውን የማያውቁ ከተወለዱ በቀናት ውስጥ ተጥለው የተገኙ ልጆች ናቸው። በስራቸው ለብዙ ልጆች እናት ሆነዋል። ጥቂት ለማይባሉ እናቶችና ጎልማሶች ደግሞ የስራ ዕድል በመፍጠር ከልመናና ከጎዳና ህይወት መታደግ ችለዋል።
ታታሪና የስራ ሰው ናቸው። በሚኖሩበት ጊቢም አትክልቶች ያለማሉ፣ የዶሮ እና የከብት እርባታ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የሽመና ስራ ይከናወናል። እስከ አሁን የሰሩት ወገናዊ ስራ ሊያስመሰግናቸው የሚገባ በመሆኑ ከዚህ መልካም ተግባር ብዙዎች ሊማሩበት ይገባል!
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው