የፋሲካ ድምቀቶች
በፈረኦን ደበበ
ስሙ እንደሚያመለክተው ፋሲካ ማለት ደስታና ፌሽታ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከሠፈር እስከ ዓለም ዙሪያ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል፡፡
በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ በሚያዚያ ወር አካባቢ የሚከበረው በዓል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤን ያበስራል፡፡ ትንሳኤው የሰው ልጆች በፈጸሙት ኃጢአት ወደ ዘለዓለማዊ ሞት እንዳይወርዱም ታድጓቸዋል።
ሀገራችንን ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ክርስቲያኖች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው በዓል ለሁለት ወራት ያህል ከምግብና ሌሎች ሥጋዊ ፍላጎቶች ታቅበው ለቆዩ አማኞች የደስታ ብሥራት ሲሆን ይህም በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይገለጻል፡፡
በዓለም ዙሪያ ባሉ ማህበረሰቦች ዘንድ በኃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች የሚከበረው በዓል ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ገጽታ ሲኖረው አንዱን ከሌላው ጋር ለማስተዋወቅ፣ ለማቀራረብና በሠላም አብሮ የመኖር ጠቀሜታንም ያስገነዝባል፡፡
እነዚህ ጭብጦችን በማንሳት ነው አንዳንድ ድረ-ገጾች በተለያዩ ሀገራት ያለውን የአከባበር ገጽታ ያስታወቁት፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሀገራት በምን ዓይነት መልክ ፋሲካን ያከብራሉ በሚል ርዕስ ሥር የአከባበር ሥነ-ሥርዓቶችን ሲገልጽ ጥቂት የዓለም ሀገራትንም ለማሳያነት አንስቷል፡፡
በተለያዩ መልኮች የሚገለጹ የደስታ ስሜቶች በዓለም ዙሪያ በሚታዩበት በዚህ በዓል አብሮ መብላትና ዘመዳሞች እርስ በርስ መጠያየቅ፣ በተለይ ከእንቁላል፣ ሥጋና ሌሎች ለበዓሉ የተዘጋጁ ምግቦችን መመገባቸው በሀገራችን ካለው ሥነ-ሥርዓት ጋርም የተቆራኘ ነው፡፡
የካቶሊክ ክርስትና እምነት ተከታዮች ካሉባት ሀገረ-ፈረንሳይ በመጀመር ሥነ-ሥርዓቱን እንደዳሰሰው ከሆነ በፋሲካ ዕለት ማለዳ ልጆች አሻንጉሊቶችን ከተለመደው ቦታ ሳይሆን ከቤተክርስቲያን ደወሎች ማግኘታቸውን ነው ያስታወቀው፡፡
የጌታን ስቅለት የሚያወሱት እነዚህ ደወሎች ከሆሳዕና በዓል ጀምሮ እስከ ፋሲካ ድረስ ድምጽ ሳይሰጡ /ለመብል የሚሆኑ ጣፋጭ ነገሮችን ለመውሰድ/ ወደ ሮም መሄዳቸውን አስታውቆ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ድባብም እንደዚሁ ደማቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከበዓል ግብይት ጋር በተያያዘ አልሳስ የተባለችውን የሀገሪቱን ከተማ ባወሳበት አጋጣሚም ገበያ ቦታዎች እጅግ የተዋቡና የደመቁ መሆናቸውን ገልጾ በጥንቸሎች፣ ፍየሎችና ዳኪዬዎች ተሞልተዋል ብሏል። ቶለሎሰ ከተባለችው ከተማ ግማሽ ሰዓት በምትፈጀው ቤሲሪስ ከተማም ከ15 ሺህ በላይ እንቁላሎች መጠበሳቸውን አስታውቋል፡፡ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላም በብዙ ቦታዎች ተቆራርሶ ለነዋሪዎች ከዳቦ ጋር ይከፋፈላል፡፡
ከፍተኛና በጣም የተቀማጠለ ግብዣ ከሚደረግባቸው ሀገራት መካከል የደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ጓተሟላ አንዷ ስትሆን የሚደረገው ዝግጅትም ብዙ ሰዎችን ያሳተፈ የጎዳና ላይ ሰልፍን ያካትታል። በስቅለት ዕለት መንገዶች ምንጣፍ በሚለብሱበት በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ ቃሪያ የመርጨት ሥነ-ስርዓት የሚከናወን ሲሆን በአረብኛ ቋንቋ አልፎምብራስ የተሰኙ የአሸዋ ንድፎችም ይሠራሉ በአበባ ቅርጽ፡፡
ኋላ ላይ ለአገልግሎት መዋል የሚችሉት እነዚህ ቅርጻ ቅርጾች በመንገዶች ላይ በሚደረግ ጉዞና ርግጫ እንዲወድቁ እንደሚደረግም ነው የጠቆመው ስቅለቱን ለማስታወስ በሚል፡፡
ባላት የአሸዋ ቁልል፣ የባህር ሞገድ፣ ላይ ላይዋን ደግሞ ካለበሱት ዳመናዎቿና ሌሎች ተፈጥሮ ገጽታዎቿ ለትንሳኤው አመቺ ማሳያ የተባለችው ሀገር በርሙዳ ስትሆን በተለይ በስቅሌት ዕለት ሆርስ ሹ( የፈረስ ኮቴ) በተባለችው የባህር ወሽመጥ ላይ ፍኛዎችን ወደ ሰማይ በማብረር የሚደረገው ትሪትም እንዲሁ ቀልብ ሳቢ እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡
በተለያዩ መልኮች የተዘጋጁ ምሥሎችን ወደ ሰማይ በማብረር ዜጎች እንደሚያከብሩ የተገለጸበት ይህ ሥነ-ሥርዓት የጌታ ትንሳኤ ማብሰሪያ ሆኖ የሚታይ ሲሆን በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ እንቁላሎችና ከንጹህ ውኃ የተወሰዱ ዓሳዎችንም ያካትታል ለምሳ ጊዜ መመገቢያነት፡፡
በተጨማሪ ደሴቲቱ የፋሲካ አበቦችና ለስጦታ የሚሆኑ ነጭ አበቦችን የምታዘጋጅ ሲሆን የጥሩምባ ቅርጽ ያላቸው እነዚህ ዕቃዎች በየዓመቱ በኪንግሀም ለተባለው የሀገራቸው ቤተ-መንግሥትም ይበረከታሉ፡፡
ብዙ ህዝቧ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆነችው ፖላንድ ያለው ድባብም በተመሳሳይ መልክ ሲገለጽ በዋናነትም ከዋዜማ ይጀምራል ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱት የደረቀ አበባ እና የዘንባባ ዝንጣፊዎችን በስጦታ መልክ ስለሚያገኙ።
ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ቀለም የተቀቡ እንቁላሎች አዘገጃጀት የተለየ ነው በተባለባት በዚህች ሀገር የእንቁላሎች ቅብም በአበባ ቅርጽ የተደረገ ነው፡፡ “እርጥብ ሰኞ” ተብሎ በሚታወቀው የፋሲካ ሰኞ እለትም ወንዶች በሴቶች ላይ ውኃ የመርጨት ተግባር ያከናውናሉ ሁሉ አቀፍ የውኃ ትግል የሚባለውን ውድድር ሁሉ እስከሚያስነሳ ድረስ፡፡
የሀገሪቱ ዋና ከተማ ዋርሳውን ጨምሮ ቤቶቭን የፋሲካ ድግስ የተባለውን ዝግጅት በሚያከናውኑባት ሀገር የክላሲካል ሙዚቃዎች ድምጾችም ይሰማሉ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ፡፡
በዓለም ታዋቂና ድንቅ የሆኑ የካቶሊክ ቤተክሪስቲያናት በሚገኙባት ኢጣሊያም ሥነ-ሥርዓቱ በድምቀት እንደሚከበር ያስታወቀው ድረ-ገጹ በተለይ በፍሎሬንስ ከተማ ላይ ስኮፒዮ ደል ካሮ የተባለው ሥነ-ሥርዓት መካሄዱንም ነው ያስታወቀው ለረጅም ዘመናት ነጭ በሬዎች ይጎትቱት የነበረውን ባሲሊካ ዲ ሳነታ ማሪያ ደል ፊዮረ የተባለውን ሠረገላ በማንሳት፡፡
ቀጥሎ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ጳጳስ ሰው ሠራሽ እርግብን ወደ ሰረገላው የሚልኩ ሲሆን ይህም በሚነደው እሳት እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡ ቀጥሎ ከተማዋን የሚያካልል ሠልፍ የሚካሄድ ሲሆን ይህ እስከ ሌሊቱ መጨረሻ ቀጥሎ መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡
ኋላ የፋሲካ ሰኞ ሲደርስ ፓስካታ ወይም ትንሹ ፋሲካ የሚባለው ሥነ-ሥርዓት ቦታውን ሲይዝ በዚህ ወቅት የተራረፉ ምግቦችን በመያዝ ወደ መዝናኛ ይወጣል ወይም 4 ኪሎ ግራም የሚመዝን አይብን ከጠመዝማዛማ ዳገት የማንከባለል ተግባር የሚፈጸም ይሆናል፡፡
በኤሲያ አህጉር በምትገኘው ፍሊፕንስ ስለሚካሄደው ክብረ-በዓል ባወሳበት ጊዜም በተለይ ማሪንዱክ ሞሪየንስ በተባለችው ደሴት ሰሞነ-ህመማት በየዓመቱ እንደሚከበር ገልጾ ተግባራቱም ኢየሱስ በሮማዊን እጅ መገደሉን ለማውሳት የሚደረጉ ናቸው ብሏል፡፡
በኢየሱስ ስቅለት የተፈጸሙ ድርጊቶችን ለማስታወስ ሲባል ብዙዎች እራሳቸውን በመስቀል ላይ በሚሰቅሉባት ሀገረ ፍሊፕኒስ ወንዶችና ሴቶች የሮማ ወታደሮችን ለመምሰል እራሳቸውን ማስክ ይለብሳሉ፣ ሄልሜት ያደርጋሉ፣ በየጎዳናዎች በመንጎራደድ በህጻናት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውም ነው የተነገረው፡፡
ሜክስኮን ጨምሮ በሌሎች ላቲን አሜሪካ ሀገራትም ፋሲካ አንድ ሰው እራሱን ከቆሻሻ ለማንጻት እንደ ዕድል የሚያይበት ሲሆን ከዋዜማው ጀምሮ የይሁዳን ምሥል ለማቃጠል አደባባይ ይዘጋጃል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1843 የቆመውን የኮሌራ ወረርሽ ለማስታወስ በሚል እዝታፖላፓ የሚባል ትሪኢት በሜክስኮ ከተማ አደባባይ የሚደረግ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ 5 ሺህ ተሳታፊዎች መገኘታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በግሪክ እና አሜሪካም ተመሳሳይ ድምቀቶችን ይዞ መከበሩ ፋሲካ ምን ያህል ለምዕመናን ደስታ አፈንጣቂ እንደሆነም ያሳያል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው